1እግዚአብሔር ሆይ፤ ጠላቶቼ ምንኛ በዙ ስንቱስ በእኔ ላይ ተነሣ!
2ብዙዎች ነፍሴን፣ “እግዚአብሔር አይታደግሽም” አሏት። ሴላ
3እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ግን ዙሪያዬን የምትከልል ጋሻ ነህ፤ ክብሬና፣ ራሴንም ቀና ቀና የምታደርግ አንተ ነህ።
4ወደ እግዚአብሔር ድምፄን ከፍ አድርጌ እጮሃለሁ፤ እርሱም ከተቀደሰ ተራራው ይመልስልኛል። ሴላ
5እተኛለሁ፤ አንቀላፋለሁ፤ እግዚአብሔር ደግፎ ይዞኛልና እነቃለሁ።
6በየአቅጣጫው የከበበኝን፣ አእላፍ ሕዝብ አልፈራም።
7እግዚአብሔር ሆይ ተነሥ! አምላኬ ሆይ፤ ታደገኝ፤ የጠላቶቼን ሁሉ መንጋጋ ትመታለህ፤ የክፉዎችንም ጥርስ ትሰባብራለህ።
8ማዳን የእግዚአብሔር ነው፤ በረከትህ በሕዝብህ ላይ ይሁን። ሴላ