1ሕዝቦች ለምን ያሤራሉ? ሰዎችስ ለምን ከንቱ ነገር ያውጠነጥናሉ?
2የምድር ነገሥታት ተነሡ፤ ገዦችም በእግዚአብሔርና በመሢሑ ላይ፣ ሊመክሩ ተሰበሰቡ፤
3“ሰንሰለታቸውን እንበጥስ፣ የእግር ብረታቸውንም አውልቀን እንጣል” አሉ።
4በሰማይ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ይሥቃል፤ ጌታም ይሣለቅባቸዋል።
5ከዚያም በቊጣው ይናገራቸዋል፤ በመዓቱም ያስደነግጣቸዋል፤
6ደግሞም፣ “እኔ ግን በተቀደሰው ተራራዬ፣ በጽዮን ላይ የራሴን ንጉሥ ሾምሁ” ይላል።
7የእግዚአብሔርን ሕግ ዐውጃለሁ፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤
8ለምነኝ፤ መንግሥታትን ርስት አድርጌ፣ የምድርንም ዳርቻ ግዛት እንዲሆንህ እሰጥሃለሁ።
9አንተም በብረት በትር ትቀጠቅጣቸዋለህ፤ እንደ ሸክላ ዕቃ ታደቃቸዋለህ።”
10ስለዚህ እናንት ነገሥታት ልብ በሉ፤ እናንት የምድር ገዦችም፣ ተጠንቀቁ።
11እግዚአብሔርን በፍርሀት አገልግሉት፤ ለእርሱ መራድም ደስ ያሰኛችሁ።
12እንዳይቈጣና በመንገድ እንዳትጠፉ፣ ዝቅ ብላችሁ ልጁን ሳሙት፤ ቍጣው ፈጥኖ ይነዳልና። እርሱን መጠጊያ የሚያደርጉ ሁሉ የተባረኩ ናቸው።