1እግዚአብሔር በጭንቅ ቀን ይስማህ፤ የያዕቆብም አምላክ ስም ይጠብቅህ።
2ከመቅደሱ ረድኤት ይላክልህ፤ ከጽዮንም ደግፎ ይያዝህ።
3ቍርባንህን ሁሉ ያስብልህ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትህን ይቀበልልህ። ሴላ
4የልብህን መሻት ይስጥህ፤ ዕቅድህን ሁሉ ያከናውንልህ።
5በአንተ ድል ደስ ይበለን፤ በአምላካችን ስም አርማችንን ከፍ እናደርጋለን፤ እግዚአብሔር የለመንኸውን ሁሉ ይፈጽምልህ።
6እግዚአብሔር፣ የቀባውን እንደሚያድን አሁን ዐወቅሁ፤ የማዳን ኀይል ባለው ቀኝ እጁ፣ ከተቀደሰው ሰማይ ይመልስለታል።
7እነዚህ በሰረገላ፣ እነዚያ በፈረስ ይመካሉ፤ እኛ ግን ትምክህታችን የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም ነው።
8እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ፤ እኛ ግን ተነሣን፤ ጸንተንም ቆምን።
9እግዚአብሔር ሆይ፤ ንጉሥን አድን፤ እኛም በጠራንህ ቀን ስማን።