1ሃሌ ሉያ። ነፍሴ ሆይ፤ እግዚአብሔርን ባርኪ።
2በምኖርበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በሕይወትም እስካለሁ ለአምላኬ እዘምራለሁ።
3በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ።
4መንፈሳቸው ትወጣለች፤ ወደ መሬታቸውም ይመለሳሉ፤ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል።
5ረዳቱ የያዕቆብ አምላክ የሆነ፣ ተስፋውንም በአምላኩ በእግዚአብሔር ላይ የጣለ ሰው ምስጉን ነው፤
6እርሱ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንም፣ በእነዚህም ውስጥ ያለውን ሁሉ የፈጠረ፣ ታማኝነቱንም ለዘላለም የሚጠብቅ ነው፤
7ለተበደሉት የሚፈርድ፣ ለተራቡት ምግብን የሚሰጥ እርሱ ነው፤ እግዚአብሔር እስረኞችን ከእስራት ያወጣል፤
8እግዚአብሔር የዕዉራንን ዐይን ያበራል፤ እግዚአብሔር የተዋረዱትን ከፍ ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይወዳል፤
9እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድኻ ዐደጎችንና መበለቶችን ይደግፋል፤ የክፉዎችን መንገድ ግን ያጠፋል።
10እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል፤ ጽዮን ሆይ፤ አምላክሽ ለትውልድ ሁሉ ንጉሥ ነው። ሃሌ ሉያ።