1አምላኬና ንጉሤ ሆይ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህን ከዘላለም እስከ ዘላለም እባርካለሁ።
2በየቀኑ እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ከዘላለም እስከ ዘላለም አመሰግናለሁ።
3እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ እጅግ ሊመሰገንም ይገባዋል፤ ታላቅነቱም አይመረመርም።
4ሥራህን አንዱ ትውልድ ለሌላው ትውልድ ያስተጋባል፤ ብርቱ ሥራህን ያውጃል።
5ስለ ግርማህ ውበትና ክብር ይናገራሉ፤ ስለ ድንቅ ሥራህም ያወራሉ።
6ስለ ድንቅ ሥራህ ብርታት ይነጋገራሉ፤ እኔም ስለ ታላቅነትህ ዐውጃለሁ።
7የበጎነትህን ብዛት በደስታ ያወሳሉ፤ ስለ ጽድቅህም በእልልታ ይዘምራሉ።
8እግዚአብሔር ቸር ነው፤ ርኅሩኅም ነው፤ ለቍጣ የዘገየ፣ ምሕረቱ የበዛ።
9እግዚአብሔር ለሁሉ ቸር ነው፤ ምሕረቱም በፍጥረቱ ሁሉ ላይ ነው።
10እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍጥረትህ ሁሉ ያመሰግንሃል፤ ቅዱሳንህም ይባርኩሃል።
11ስለ መንግሥትህ ክብር ይናገራሉ፤ ስለ ኀይልህም ይነጋገራሉ፤
12በዚህም ብርቱ ሥራህን፣ የመንግሥትህንም ግርማ ክብር ያስታውቃሉ።
13መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፤ ግዛትህም ለትውልድ ሁሉ ጸንቶ ይኖራል። እግዚአብሔር ቃሉን ሁሉ ይጠብቃል፤ በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።
14እግዚአብሔር የሚንገዳገዱትን ሁሉ ይደግፋል፤ የወደቁትንም ሁሉ ያነሣል።
15የሁሉ ዐይን አንተን በተስፋ ይጠብቃል፤ አንተም ምግባቸውን በወቅቱ ትሰጣቸዋለህ።
16አንተ እጅህን ትዘረጋለህ፤ የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት ታረካለህ።
17እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ፣ በሥራውም ሁሉ ቸር ነው።
18እግዚአብሔር ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።
19ለሚፈሩት ፍላጎታቸውን ይፈጽማል፤ ጩኸታቸውን ይሰማል፤ ያድናቸዋልም።
20እግዚአብሔር የሚወዱትን ሁሉ ይጠብቃል፤ ክፉዎችን ሁሉ ግን ያጠፋል።
21አፌ የእግዚአብሔርን ምስጋና ይናገራል፤ ፍጡር ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ ቅዱስ ስሙን ይባርክ።