1እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
2“እስራኤላውያንን እዘዛቸው፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ወደምትካፈሏት ወደ ከነዓን ምድር በምትገቡበት ጊዜ አዋሳኞቿ እነዚህ ይሆናሉ፤
3“ ‘የደቡብ ድንበራችሁ በኤዶም ወሰን ላይ ካለው ከጺን ምድረ በዳ ጥቂቱን ይጨምራል፤ በምሥራቅም በኩል የደቡብ ድንበራችሁ ከጨው ባሕር ጫፍ ይጀምርና
4በአቅረቢም መተላለፊያ አቋርጦ እስከ ጺን ይሄድና በስተ ደቡብ እስከ ቃዴስ በርኔ ይዘልቃል፤ ከዚያም በሐጸር አዳር ዐልፎ እስከ ዓጽሞን ይደርስና
5ዞሮ ከግብፅ ወንዝ ደረቅ መደብ ጋር በመገናኘት መጨረሻው ባሕሩ ይሆናል።
6የምዕራቡ ድንበራችሁ ደግሞ የታላቁ ባሕር ዳርቻ ይሆናል። በምዕራቡ በኩል ያለው ወሰናችሁም ይኸው ነው።
7“ ‘የሰሜን ድንበራችሁን ከታላቁ ባሕር እስከ ሖር ተራራ ምልክት አድርጉበት፤
8ከሖር ተራራ እስከ ሌቦ ሐማት እንደዚሁ አድርጉ፤ ከዚያም ወሰኑ እስከ ጽዳድ ይሄድና
9እስከ ዚፍሮን በመቀጠል መጨረሻው ሐጻርዔናን ይሆናል፤ በሰሜን በኩል ያለው ወሰናችሁ ይኸው ነው።
10“ ‘ለምሥራቁ ድንበራችሁም እንደዚሁ ከሐጸርዔናን እስከ ሴፋማ ምልክት አድርጉበት።
11ወሰኑም ከሴፋማ አንሥቶ ከዓይን በስተ ምሥራቅ እስካለው እስከ ሪብላ ቊልቊል ይወርድና ከኪኔሬት ባሕርሀ በስተ ምሥራቅ እስካሉት ሸንተረሮች ድረስ ይዘልቃል።
12ከዚያም ወሰኑ የዮርዳኖስን ወንዝ ተከትሎ መጨረሻው የጨው ባሕር ይሆናል። “ ‘እንግዲህ በዙሪያዋ ካሉት ወሰኖቿ ጋር ምድራችሁ ይህች ናት።’ ”
13ሙሴ እስራኤላውያንን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “ይህችን ምድር ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ደልድሉ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ለዘጠኙና ለግማሹ ነገድ እንድትሰጥ አዞአል፤
14የሮቤል ነገድ ቤተ ሰቦች፣ የጋድ ነገድ ቤተ ሰቦች እንዲሁም የምናሴ ነገድ እኩሌታ ርስታቸውን ተቀብለዋልና።
15እነዚህ ሁለቱ ነገዶችና እኩሌታው ነገድ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ፣ ከኢያሪኮ ማዶ በፀሓይ መውጫ በኩል ርስታቸውን ተቀብለዋል።”
16እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤
17“ምድሪቱን ርስት አድርገው የሚያከፋፍሏችሁ ካህኑ አልዓዛርና የነዌ ልጅ ኢያሱ ናቸው፤
18ምድሪቱን በማከፋፈሉ እንዲረዱም ከየነገዱ አንዳንድ መሪ ውሰዱ።
19ስማቸውም ይህ ነው፤ ከይሁዳ ነገድ፣ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤
20ከስምዖን ነገድ፣ የዓሚሁድ ልጅ ሰላሚኤል፤
21ከብንያም ነገድ፣ የኪስሎን ልጅ ኤልዳድ፤
22የዳን ነገድ መሪ፣ የዩግሊ ልጅ ቡቂ፤
23የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ነገድ መሪ፣ የሱፊድ ልጅ አኒኤል፤
24የዮሴፍ ልጅ የኤፍሬም ነገድ መሪ፣ የሺፍጣን ልጅ ቀሙኤል፤
25የዛብሎን ነገድ መሪ፣ የፈርናክ ልጅ ኤሊሳፈን፤
26የይሳኮር ነገድ መሪ፣ የሖዛ ልጅ ፈልጢኤል፤
27የአሴር ነገድ መሪ፣ የሴሌሚ ልጅ አሒሁድ፤
28የንፍታሌም ነገድ መሪ፣ የዓሚሁድ ልጅ ፈዳሄል።”
29እነዚህ በከነዓን ምድር ለእስራኤላውያን ርስት እንዲያከፋፍሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዛቸው ሰዎች ናቸው።