1ባሕሩን ተሻግረው ጌርሴኖን ወደተባለ አገር መጡ።
2ኢየሱስ ከጀልባ እንደ ወረደ፣ ርኩስ መንፈስ ያደረበት ሰው ከመቃብር ቦታ ወጥቶ ሊገናኘው ወደ እርሱ መጣ።
3ይህ ሰው በመቃብር ቦታ ውስጥ የሚኖርና ማንም በሰንሰለት እንኳ ሊያስረው የማይችል ነበር።
4ብዙ ጊዜ በእግር ብረትና በሰንሰለት ይታሰር ነበር፤ ነገር ግን የእጅ ሰንሰለቱን ይበጥስ፣ የእግር ብረቱንም ይሰብር ነበር። ማንም ይዞ ሊያቈየው የሚችል አልነበረም።
5በመቃብሮቹና በተራራዎቹ መካከል ቀንና ሌሊት እየተዘዋወረ በመጮኽ ሰውነቱን በድንጋይ ይቈራርጥ ነበር።
6ይህም ሰው ኢየሱስን ከሩቅ ባየው ጊዜ ወደ እርሱ ሮጦ ከፊቱ ተንበርክኮ ሰገደለት፤
7በታላቅ ድምፅ ጮኾም፣ “አንተ የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፤ ከእኔ ምን አለህ? እንዳታሠቃየኝ በእግዚአብሔር ይዤሃለሁ” አለው።
8ይህንንም ያለው ኢየሱስ፣ “አንተ ርኩስ መንፈስ ከዚህ ሰው ውጣ!” ብሎት ስለ ነበር ነው።
9ከዚያም ኢየሱስ፣ “ስምህ ማን ነው?” ብሎ ጠየቀው። “ብዙ ነንና ስሜ ሌጌዎን ነው” አለው።
10ከአገር እንዳያስወጣቸውም አጥብቆ ለመነው።
11በአቅራቢያውም በሚገኝ ኰረብታ ላይ ትልቅ የዐሣማ መንጋ ተሰማርቶ ነበር።
12ርኵሳን መናፍስቱም ኢየሱስን፣ “ወደ ዐሣማዎቹ ስደደን፤ እንድንገባባቸውም ፍቀድልን” ብለው ለመኑት።
13እርሱም ፈቀደላቸው። ርኵሳን መናፍስቱም ወጥተው በዐሣማዎቹ ገቡባቸው፤ ሁለት ሺህ ያህል ዐሣማዎችም በገደሉ አፋፍ በመንደርደር ቊልቊል ወርደው በባሕር ውስጥ ሰጠሙ።
14እረኞቹ ሸሽተው ሄዱ፤ ወሬውን በከተማና በገጠር አዳረሱት፤ ሕዝቡም የሆነውን ለማየት ካለበት ወጣ።
15ወደ ኢየሱስም በመጡ ጊዜ፣ የአጋንንት ሰራዊት አድረውበት የነበረው ሰው፣ ልብስ ለብሶና አእምሮው ተመልሶለት በዚያ ተቀምጦ አዩት፤ ፈሩም።
16ይህን ያዩ ሰዎችም አጋንንት ስላደረበት ሰው የተደረገውንና ስለ ዐሣማዎቹም ለሕዝቡ አወሩ።
17ከዚያም ሕዝቡ አገራቸውን ለቆ እንዲሄድላቸው ኢየሱስን ይለምኑት ጀመር።
18ኢየሱስ ወደ ጀልባዪቱ በሚገባበት ጊዜ፣ አጋንንት አድሮበት የነበረው ሰው አብሮት ለመሄድ ለመነው።
19ኢየሱስ አልፈቀደለትም፤ ነገር ግን፣ “ወደ ቤትህ ሂድ፣ ለዘመዶችህም ጌታ ምን ያህል ታላቅ ነገር እንዳደረገልህና ያሳየህን ምሕረት ንገራቸው” አለው።
20ሰውየውም ሄደ፤ ኢየሱስ ያደረገለትን ነገር ሁሉ ዐሥር ከተማ በተባለው አገር ያወራ ጀመር፤ የሰሙትም ሁሉ ተደነቁ።
21ኢየሱስ እንደ ገና በጀልባ ወደ ማዶ በተሻገረ ጊዜ፣ ብዙ ሕዝብ በዙሪያው ተሰባሰበ፤ በባሕሩ ዳርቻም እንዳለ፣
22ከምኵራብ አለቆች አንዱ ኢያኢሮስ የተባለው ወደዚያ መጥቶ ስለ ነበር፣ ኢየሱስን ባየው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቆ፣
23“ትንሿ ልጄ በሞት አፋፍ ላይ ናትና ድና በሕይወት እንድትኖር መጥተህ እጅህን ጫንባት” በማለት አጥብቆ ለመነው።
24ኢየሱስም አብሮት ሄደ። ብዙ ሕዝብም ዙሪያውን እያጨናነቀው ተከተለው።
25ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የኖረችም ሴት በዚያ ነበረች፤
26በብዙ ባለ መድኀኒቶች ዘንድ በመንከራተት ያላትን ሁሉ ብትጨርስም፣ ሕመሙ ባሰባት እንጂ አልተሻላትም ነበር።
27ስለ ኢየሱስም በሰማች ጊዜ፣ ከበስተ ኋላው በሰዎች መካከል መጥታ ልብሱን ነካች፤
28ምክንያቱም፣ “እንደምንም ብዬ ልብሱን ብቻ እንኳ ብነካ እፈወሳለሁ” የሚል እምነት ነበራት።
29የሚፈሰው ደሟ ወዲያውኑ ቆመ፤ ከሥቃይዋ መገላገሏም በሰውነቷ ታወቃት።
30ወዲያውኑ ኢየሱስ፣ ኀይል ከእርሱ እንደ ወጣ ዐውቆ፤ ወደ ሕዝቡ ዘወር በማለት፣ “ልብሴን የነካው ማን ነው?” አለ።
31ደቀ መዛሙርቱም፣ “ሕዝቡ ተጨናንቆ ሲጋፋህ እያየህ፣ ‘ማን ነው የነካኝ?’ እንዴት ትላለህ?” አሉት።
32ኢየሱስ ግን ይህንን ያደረገው ማን እንደሆነ ለማየት ዙሪያውን ተመለከተ።
33ሴትየዋም ምን እንደ ተደረገላት ባወቀች ጊዜ እየፈራችና እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፤ እውነቱንም ሁሉ ነገረችው።
34እርሱም፣ “ልጄ ሆይ፤ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ፤ ከሥቃይሽም ዕረፊ” አላት።
35ኢየሱስም በመነጋገር ላይ እያለ፣ ሰዎች ከምኵራቡ አለቃ ከኢያኢሮስ ቤት መጥተው፣ “ልጅህ ሞታለች፤ ከእንግዲህ መምህሩን ለምን ታደክመዋለህ?” አሉት።
36ኢየሱስ ግን ሰዎቹ የተናገሩትን ችላ በማለት የምኵራቡን አለቃ፣ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ፤” አለው።
37ከጴጥሮስና ከያዕቆብ እንዲሁም ከያዕቆብ ወንድም ከዮሐንስ በቀር ማንም እንዲከተለው አልፈቀደም።
38ወደ ምኵራቡ አለቃ ቤት እንደ ደረሱ፣ ኢየሱስ ግርግሩንና ሰዎቹም ዋይ ዋይ እያሉ አምርረው ሲያለቅሱ ተመለከተ።
39ወደ ቤትም ገብቶ፣ “ይህ ሁሉ ግርግርና ልቅሶ ምንድን ነው? ብላቴናዪቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” አላቸው።
40ሰዎቹ ግን ሣቁበት። ሰዎቹን ሁሉ ከቤት ካስወጣ በኋላ፣ የብላቴናዪቱን አባትና እናት እንዲሁም አብረውት የመጡትን ደቀ መዛሙርት አስከትሎ ብላቴናዪቱ ወዳለችበት ገባ።
41ከዚያም የብላቴናዪቱን እጅ ይዞ፣ “ጣሊታ ቁሚ!” አላት፤ ትርጒሙም፣ “አንቺ ልጅ ተነሺ” ማለት ነው።
42ብላቴናዪቱም ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ ወዲያ ወዲህም ሄደች። ዕድሜዋም ዐሥራ ሁለት ዓመት ነበር። ሰዎቹም በሁኔታው እጅግ ተደነቁ።
43እርሱም ይህን ነገር ማንም እንዳያውቅ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤ የሚበላ ነገር እንዲሰጧትም ነገራቸው።