የማርቆስ ወንጌል 13

AMHEVGአማርኛ37 ጥቅሶች4:57 አዳምጥ
አዳምጥ 4:57 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እርሱም ከመቅደስ ሲወጣ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ “መምህር ሆይ፥ እንዴት ያሉ ድንጋይዎችና እንዴት ያሉ ሕንጻዎች እንደ ሆኑ እይ” አለው።

2ኢየሱስም መልሶ፦ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህን? ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፡” አለው።

3በመቅደስም ትይዩ በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ፥ ጴጥሮስና ያዕቆብ ዮሐንስም እንድርያስም፦

4“ንገረን፥ ይህ መቼ ይሆናል? ይህስ ሁሉ ይፈጸም ዘንድ እንዳለው ምልክቱ ምንድር ነው?” ብለው ለብቻቸው ጠየቁት።

5ኢየሱስም መልሶ እንዲህ ይላቸው ጀመር፦ “ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ።

6ብዙዎች፦ ‘እኔ ነኝ’ እያሉ በስሜ ይመጣሉና፥ ብዙዎችንም ያስታሉ።

7ጦርንም የጦርንም ወሬ በሰማችሁ ጊዜ አትደንግጡ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና፥ ነገር ግን መጨረሻው ገና ነው።

8ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣልና፤ በልዩ ልዩ ስፍራ የምድር መናወጥ ይሆናል፤ ራብ ይሆናል፤ እነዚህ የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው።

9እናንተ ግን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ ወደ ሸንጎ አሳልፈው ይሰጡአችኋል በምኵራብም ትገረፋላችሁ ምስክርም ይሆንባቸው ዘንድ ስለ እኔ በገዥዎችና በነገሥታት ፊት ትቆማላችሁ።

10አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል።

11ሲጐትቱአችሁና አሳልፈው ሲሰጡአችሁም ምን እንድትናገሩ አስቀድማችሁ አትጨነቁ፥ ዳሩ ግን በዚያች ሰዓት የሚሰጣችሁን ተናገሩ፤ የሚነግረው መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።

12ወንድምም ወንድሙን አባትም ልጁን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ ይነሣሉ። ይገድሉአቸውማል፤

13በሁሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።”

14“ነገር ግን በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የጥፋት ርኵሰት በማይገባው ስፍራ ቆሞ ብታዩ፥ አንባቢው ያስተውል፥ በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች ይሽሹ፥

15በሰገነትም ያለ ወደ ቤት አይውረድ ከቤቱም አንዳች ይወስድ ዘንድ አይግባ፥

16በእርሻም ያለ ልብሱን ይወስድ ዘንድ ወደ ኋላው አይመለስ።

17በዚያን ወራትም ለርጉዞችና ለሚያጠቡ ወዮላቸው።

18ነገር ግን ሽሽታችሁ በክረምት እንዳይሆን ጸልዩ፤

19በዚያን ወራት እግዚአብሔር ከፈጠረው ከፍጥረት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልሆነ ደግሞም የማይሆን የመከራ ዓይነት ይሆናልና።

20ጌታስ ወራቶቹን ባያሳጥር፥ ሥጋ የለበሰ ሁሉ ባልዳነም፤ ነገር ግን ስለ መረጣቸው ምርጦች ወራቶቹን አሳጠረ።

21በዚያን ጊዜም ማንም፦ ‘እነሆ፥ ክርስቶስ ከዚህ አለ፥’ ወይም፦ ‘እነሆ፥ ከዚያ አለ፡’ ቢላችሁ አትመኑ፤

22ሐሰተኞች ክርስቶሶችና ሐሰተኞች ነቢያት ይነሣሉና፥ ቢቻላቸውስ የተመረጡትን እንኳ ያስቱ ዘንድ ምልክትና ድንቅ ያደርጋሉ።

23እናንተ ግን ተጠንቀቁ፤ እነሆ፥ አስቀድሜ ሁሉን ነገርኋችሁ።

24“በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፥

25ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፥ የሰማያትም ኃይላት ይናወጣሉ።

26በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል።

27በዚያን ጊዜም መላእክትን ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።”

28“ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቍጥ፥ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤

29እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህን ሁሉ መሆኑን ስታዩ ቀርቦ በደጅ እንደ ሆነ እወቁ።

30እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ እስኪሆን ድረስ ይህ ትውልድ አያልፍም።

31ሰማይና ምድር ያልፋሉ ቃሌ ግን አያልፍም።

32“ስለዚያች ቀን ወይም ስለዚያች ሰዓት ግን የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን ከአባት በቀር የሚያውቅ የለም።

33ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ ጸልዩም።

34ቤቱን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንደ ሄደ ሰው ነው፥ ለባሮቹም ሥልጣን ለእያንዳንዱም ሥራውን ሰጥቶ በረኛውን እንዲተጋ አዘዘ።

35እንግዲህ በማታ ቢሆን ወይም በእኩለ ሌሊት ወይም ዶሮ ሲጮኽ ወይም በማለዳ ቢሆን ባለቤቱ መቼ እንዲመጣ አታውቁምና፤

36ድንገት መጥቶ ተኝታችሁ እንዳያገኛችሁ ስለዚህ ትጉ።

37ለእናንተም የምነግራችሁ ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ።”

ማብራሪያ

13:1-4 ክርስቶስ እውነተኛ የልብ ንጽህና በሌለበት ውጫዊ ገጽታን ምን ያህል ዋጋ እንደማይሰጠው ተመልከት። እርሱ የከበሩ ነፍሳት ጥፋት ላይ ያዝንላቸዋል፣ እነርሱንም ያለቅስላቸዋል፤ ነገር ግን የሚያምር ቤት መፍረስ ላይ ሲያዝን አናገኘውም። እንግዲህ በሰማይ ዘላቂ መኖሪያ እንዲኖረንና፣ ለዚያም ደግሞ ሁሉንም የጸጋ መንገዶች በትጋት በመጠቀም በሚገኘው በመንፈስ ቅዱስ ተጽዕኖ እንድንዘጋጅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስታውሰን።

፲፫፥፭-፲፫ ጌታችን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ፣ የጉጉታቸውን ፍላጎት ከማርካት ይልቅ ህሊናቸውን አቅንቶአል። ብዙዎች ሲታለሉ፣ እኛም ከዚህ ተነስተን ራሳችንን እንድንመረምር መንቃት አለብን። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትም፣ የራሳቸው ጥፋት ካልሆነ፣ በዙሪያቸው ያለው ሁሉ ትርምስ ውስጥ ሲሆን እንኳን፣ ቅዱስ የሆነ ደህንነትንና የአእምሮ ሰላምን ሊያገኙ ይችላሉ። ነገር ግን፣ ስለ እርሱ በሚደርስባቸው መከራ ምክንያት፣ ከክርስቶስና ለእርሱ ካላቸው ግዴታ እንዳይሳቡ መጠንቀቅ አለባቸው። በሁሉም ሰው ይጠላሉ፤ ይህ በራሱ በቂ መከራ ነው! ሆኖም ግን፣ የተጠሩበት ሥራ ሊቀጥልና ሊያብብ ይገባል። እነርሱ ሊሰባበሩና ሊጨቆኑ ቢችሉም፣ ወንጌሉ ግን ሊሰበር አይችልም። የተስፋው ድነት ከክፉ መዳን ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም የዘላለም በረከት ነው።

13:14-23 አይሁድ ሮማውያንን በመቃወም እና ክርስቲያኖችንም በማሳደድ የራሳቸውን ጥፋት አፋጠኑ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6