የማርቆስ ወንጌል 12

AMHNIVአማርኛ44 ጥቅሶች7:39 አዳምጥ
አዳምጥ 7:39 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ከዚያም እንዲህ እያለ በምሳሌ ይነግራቸው ጀመር፤ “አንድ ሰው ወይን ተከለ፤ ዙሪያውን ዐጠረ፤ ለመጭመቂያው ጒድጓድ ቈፈረ፤ የመጠበቂያም ማማ ሠራለት፤ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።

2በመከር ጊዜም ከወይኑ ፍሬ እንዲያመጣለት ከአገልጋዮቹ አንዱን ወደ ገበሬዎቹ ላከ።

3እነርሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት።

4እንደ ገናም ሌላ አገልጋይ ላከ። እነርሱም ራሱን ፈንክተውና አዋርደው መለሱት”፤

5አሁንም እንደ ገና ሌላ ላከ፤ ይህኛውንም ገደሉት፤ ከሌሎች ከብዙዎቹ መካከል አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹንም ገደሉ።

6“አሁንም የሚላክ ሌላ ነበረው፤ እርሱም የሚወደው ልጁ ነበረ፤ ‘ልጄንስ ያከብሩታል’ በማለት ከሁሉ በኋላ ላከው።

7“ገበሬዎቹ ግን እርስ በርሳቸው፣ ‘ይህማ ዋናው ወራሹ ነው፤ ኑ እንግደለው፤ ርስቱ የእኛ ይሆናል’ ተባባሉ፤

8ከዚያም ይዘው ገደሉት፤ ከወይኑ ስፍራም አውጥተው ጣሉት።

9“እንግዲህ የወይኑ አትክልት ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል? ይመጣል፤ ገበሬዎቹን ይገድላል፤ የወይኑንም አትክልት ለሌሎች ይሰጣል።

10እንዲህ የሚለውን የመጽሐፍ ቃል አላነበባችሁምን፤ “ ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ፤

11ጌታ ይህን አድርጎአል፣ ይህም ለዐይናችን ድንቅ ነው’?”

12ምሳሌውን የተናገረው ስለ እነርሱ መሆኑን ስላወቁ፣ ሊይዙት ፈለጉ፤ ነገር ግን ሕዝቡን ስለ ፈሩ ትተውት ሄዱ።

13ከዚያም በነገር እንዲያጠምዱት ከፈሪሳውያንና ከሄሮድስ ወገን ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ።

14እነርሱም መጥተው እንዲህ አሉት፤ “መምህር ሆይ፤ አንተ ትክክለኛ ሰው መሆንህን እናውቃለን፤ የሰዎች ማንነት ስለማይገድህም አታዳላም፤ የእግዚአብሔርን መንገድ ብቻ በእውነት ታስተምራለህ፤ ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?

15እኛስ እንክፈል ወይስ አንክፈል?” ኢየሱስ ግን ግብዝነታቸውን ዐውቆ፣ “ለምን ልታጠምዱኝ ትፈልጋላችሁ? እስቲ አንድ ዲናር አምጡልኝና ልየው” አላቸው።

16እነርሱም አመጡለት፣ “ይህ የማን መልክ ነው? ጽሕፈቱስ የማን ነው?” አላቸው፤ እነርሱም፣ “የቄሳር ነው” አሉት።

17ኢየሱስም፣ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጡ” አላቸው። እነርሱም በእርሱ ተደነቁ።

18ከዚህ በኋላ የሙታን ትንሣኤ የለም የሚሉ ሰዱቃውያን ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፤

19“መምህር ሆይ፤ የአንድ ሰው ወንድም ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ ቢሞት፣ ይህ ሰው ሴትየዋን አግብቶ ለወንድሙ ዘር እንዲተካ ሙሴ ጽፎልናል።

20ታዲያ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ፤ የመጀመሪያው አግብቷት ዘር ሳይተካ ሞተ፤

21ሁለተኛውም ሴትየዋን አገባት፤ እርሱም ዘር ሳይተካ ሞተ፤ ሦስተኛውም እንዲሁ፤

22ሰባቱም አገቧት፤ ዘር ግን አልተኩም፤ በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች።

23እንግዲህ፣ ሰባቱም አግብተዋታልና በትንሣኤ ለማናቸው ሚስት ልትሆን ነው?” አሉት።

24ኢየሱስም፣ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “የምትስቱት እኮ ቅዱሳት መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኀይል ስለማታውቁ ነው!

25ሙታን በሚነሡበት ጊዜ እንደ ሰማይ መላእክት ይሆናሉ እንጂ አያገቡም፤ አይጋቡም።

26ስለ ሙታን መነሣት ግን፣ በሙሴ መጽሐፍ ይኸውም ስለ ቍጥቋጦው በተነገረው ክፍል፣ እግዚአብሔር ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ያለውን አላነበባችሁምን?

27እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ ስለዚህ እጅግ ተሳስታችኋል።”

28ከጸሐፍትም አንዱ መጥቶ ሲከራከሩ ሰማቸው፤ ኢየሱስ ለቀረበለት ጥያቄ ተገቢውን መልስ መስጠቱን አስተውሎ፣ “ለመሆኑ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው።

29ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ከሁሉ የሚበልጠው ይህ ነው፤ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው፤

30አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።’

31ሁለተኛውም ይህ ነው፤ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።’ ከእነዚህም የሚበልጥ ትእዛዝ የለም።”

32ጸሓፊውም እንዲህ አለው፤ “መምህር ሆይ፤ መልካም ብለሃል፤ እርሱ አንድ መሆኑን፣ ከእርሱም ሌላ አለመኖሩን መናገርህ ትክክል ነው፤

33እርሱን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ኀይልህ መውደድ፣ እንዲሁም ባልንጀራህን እንደ ራስህ መውደድ ከሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉና ከሌሎችም መሥዋዕቶች ይበልጣል።”

34ኢየሱስም በማስተዋል እንደ መለሰለት አይቶ፣ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” አለው። ከዚህ በኋላ ሊጠይቀው የደፈረ ማንም አልነበረም።

35ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ አደባባይ በሚያስተምርበት ጊዜ እንዲህ ሲል ጥያቄ አቀረበ፤ “ጸሐፍት እንዴት ክርስቶስ የዳዊት ልጅ ነው ይላሉ?

36ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ሲናገር፣ “ጌታ ጌታዬን፣ ‘ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርጋቸው ድረስ በቀኜ ተቀመጥ’ አለው።” ይላል፤

37ታዲያ ዳዊት ራሱ ‘ጌታ’ ካለው፣ እንዴት ተመልሶ ልጁ ይሆናል?” ብዙ ሕዝብም በደስታ ይሰማው ነበር።

38በሚያስተምርበትም ጊዜ እንዲህ አለ፤ “ከጸሐፍት ተጠንቀቁ፤ የተንዘረፈፈ ቀሚስ ለብሰው መዞርን ይወዳሉ፤ በየአደባባዩም የአክብሮት ሰላምታ ይሻሉ፤

39በምኵራብ ከፍተኛውን ወንበር፣ በግብዣም ቦታ የከበሬታን ስፍራ ይፈልጋሉ፤

40በረጅም ጸሎታቸው እያሳበቡ የመበለቶችን ቤት ያራቍታሉ፤ እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ።”

41ኢየሱስ በገንዘብ ማስቀመጫው አንጻር ተቀምጦ ብዙ ሰዎች ስጦታቸውን ወደ ቤተ መቅደሱ ገንዘብ ማስቀመጫ ሣጥን ሲያስገቡ ይመለከት ነበር። ብዙ ሀብታሞች ብዙ ገንዘብ አስገቡ፤

42አንዲት ምስኪን መበለት ግን ከአንድ ሳንቲም የማይበልጡ ሁለት የናስ ቤሳዎች አስገባች።

43ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ፣ እንዲህ አላቸው፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ይህቺ ድኻ መበለት ሣጥኑ ውስጥ ከጣሉት ከሌሎቹ የበለጠ አስገባች።

44እነዚህ ሁሉ ከተረፈው ሀብታቸው ሰጡ፤ እርሷ ግን በድኽነት ዐቅሟ ያላትን ሁሉ አውጥታ ለመኖሪያ የሚሆናትን እንዳለ ሰጠች።”

ማብራሪያ

12:1-12 ክርስቶስ በምሳሌዎች የአይሁድን ቤተ ክርስቲያን እንደሚያስወግድ አሳየ። የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋዮች በዘመናት ሁሉ ከቤተ ክርስቲያን መብቶችን ከቀመሱት ነገር ግን የሚገባውን ፍሬ ካላፈሩት ምንኛ ነውር ያለበት አያያዝ እንደገጠማቸው ማሰቡ ያሳዝናል፡፡ በመጨረሻም እግዚአብሔር ልጁን፣ ወዳጁን ላከ፤ ጌታቸው የወደደውን እነርሱም ሊያከብሩትና ሊወዱት እንደሚገባ ተጠብቆ ነበር፤ ነገር ግን እርሱ ልጅና ወራሽ ስለነበር ከማክበር ይልቅ በዚህ ምክንያት ጠሉት። ነገር ግን የክርስቶስ ከፍ ከፍ ማለት የጌታ ሥራ ነበር፤ በልባችንም ከፍ ከፍ ማድረግና ዙፋኑን በዚያ መትከል የእርሱ ሥራ ነው። ይህ ከተደረገ በዓይኖቻችን ድንቅ መሆን አይቀርም። ቅዱሳት መጻሕፍት፣ የታመኑ ሰባኪዎችም፣ እንዲሁም የክርስቶስ በሥጋ መምጣት በሕይወታችን ለእግዚአብሔር የተገባውን ምስጋና እንድናቀርብ ይጠይቁናል። ኃጢአተኞች ከትዕቢተኛ፣ ከሥጋዊ መንፈስ ይጠንቀቁ፤ የክርስቶስን ሰባኪዎች የሚሰድቡ ወይም የሚንቁ ከሆነ፣ እርሱ በምድር በነበረበት ጊዜ ቢኖሩ ኖሮ ጌታቸውንም እንደዚሁ ያደርጉ ነበር።

፲፪፥፲፫-፲፯ የክርስቶስ ጠላቶች ግዴታቸውን ለማወቅ የሚፈልጉ መስለው ሊታሰቡ ይችሉ ነበር፤ በእርግጥ ግን እርሱ በዚያ ጥያቄ ላይ የትኛውንም ወገን ቢወስድ፣ እሱን ለመክሰስ ምክንያት ያገኛሉ ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። የክርስቶስን ተከታዮች ለማጥመድ ከዓለማዊ ፖለቲካ ጋር በተያያዙ ክርክሮች ውስጥ እንዲገቡ ከማድረግ የበለጠ ምንም ነገር የለም። ኢየሱስ እንደ ሕዝብ አስቀድመው ያቀረቡትን እጅ መስጠት በመጥቀስ ወጥመዱን አመለጣት፤ የሰሙትም ሁሉ መልሱ ባለው ታላቅ ጥበብ ተገረሙ። ብዙዎች የስብከትን ቃል ያወድሳሉ፣ የዚያን ስብከት ትምህርቶች ግን የማይታዘዙ ናቸው።

ቍ. ፲፪፥፲፰-፳፯ የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት፣ ዛሬ የተገለጠው ሃይማኖት ሁሉ የሚፈስስበት ምንጭ እና የተመሠረተበት መሠረት እንደመሆኑ መጠን፣ ከስህተት የሚጠብቅ ምርጥ መከላከያ ነው። ክርስቶስ የሰዱቃውያንን፣ በዚያ ዘመን ይሳለቁ የነበሩ ከሓዲዎችን፣ ተቃውሞ አስወገደ፤ ይህም ስለ ወደፊቱ ሁኔታ ትምህርትን በትክክለኛው ብርሃን በማስቀመጥ ነበር።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

AMHEVG በምሳሌም ይነግራቸው ጀመር፦ “አንድ ሰው የወይን አትክልት ተከለ፥ ቅጥርም ቀጠረለት፥ መጥመቂያም ማሰለት፥ ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። አማርኛ ENGNIV He then began to speak to them in parables: “A man planted a vineyard. He put a wall around it, dug a pit for the winep… English BCV ኢየሱስ ብምስላ ኽነግሮም ጀመረ፤ “ሓደ ሰብኣይ ወይኒ ተኸለ፤ ሓፁር ሓፀሮ፤ መፅመቚውን ኰዓተሉ፤ መሐለዊ መንደቕውን ሰርሐሉ፤ ንሓረስቶት ድማ ብብላዕ ሂብዎም፥ ናብ ካልእ ዓዲ ኸደ። ትግርኛ GAZBIB Yesus fakkeenyaan isaanitti dubbachuutti ka'e; ?Namni tokko mukeetii waynii baay'ee lafa isaa irra dhaabe. Naannoo isaa… Afaan Oromoo BCV GIZ ወአኀዘ ይመስል ሎሙ ወይቤሎሙ፦ “ብእሲ ተከለ ወይነ ወፀቈኖ ወአክረየ ምክያደ ወሐነጸ ማኅፈደ ውስቴቱ ወሤመ ሎቱ ገባረ ወዐቀብተ ወይን ወነገደ። giz GAZGAZ Yesus fakkeenyaan isaanitti dubbachuutti ka'e; ?Namni tokko mukeetii waynii baay'ee lafa isaa irra dhaabe. Naannoo isaa… Afaan Oromoo BCV aksum ኢየሱስ ብምስላ ኽነግሮም ጀመረ፤ “ሓደ ሰብኣይ ወይኒ ተኸለ፤ ሓፁር ሓፀሮ፤ መፅመቚውን ኰዓተሉ፤ መሐለዊ መንደቕውን ሰርሐሉ፤ ንሓረስቶት ድማ ብብላዕ ሂብዎም፥ ናብ ካልእ ዓዲ ኸደ። ትግርኛ SWAHSUV Akaanza kusema nao kwa mifano; Mtu mmoja alipanda shamba la mizabibu, akazungusha ugo, akachimba shimo la shinikizo, ak… Kiswahili