የማቴዎስ ወንጌል 10

AMHNIVአማርኛ42 ጥቅሶች5:52 አዳምጥ
አዳምጥ 5:52 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ኢየሱስ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ወደ እርሱ ጠርቶ ርኵሳን መናፍስትን እንዲያወጡ፣ ደዌንና ሕማምን ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣንን ሰጣቸው።

2የዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ስም የሚከተለው ነው፦ መጀመሪያ ጴጥሮስ የተባለው ስምዖንና ወንድሙ እንድርያስ፣ የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብና ወንድሙ ዮሐንስ፣

3ፊልጶስና በርተሎሜዎስ፣ ቶማስና ቀረጥ ሰብሳቢው ማቴዎስ፣ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብና ታዴዎስ የተባለው ልብድዮስ፣

4ቀነናዊው ስምዖንና በኋላ ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው አስቆሮቱ ይሁዳ።

5እነዚህን ዐሥራ ሁለቱን ኢየሱስ እንዲህ ከሚል ትእዛዝ ጋር ላካቸው፤ “ወደ አሕዛብ አትሂዱ፤ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ።

6ይልቁንስ የእስራኤል ቤት ወደሆኑት ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ።

7ሄዳችሁም፣ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ ብላችሁ ስበኩ።

8በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤ በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ።

9በመቀነታችሁ ወርቅም ሆነ ብር ወይም መዳብ አትያዙ።

10ለመንገዳችሁም ከረጢት፣ ትርፍ እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አትያዙ፤ ለሠራተኛ የዕለት ጕርሱ ይገባዋልና።

11“ወደ አንድ ከተማ ወይም መንደር ስትገቡ ሊቀበላችሁ ፈቃደኛ የሆነ ሰው ፈልጋችሁ በቤቱ ዕረፉ፤ እስክትወጡም ድረስ በዚያው ቈዩ።

12ወደ ማንኛውም ሰው ቤት ስትገቡ ሰላምታ አቅርቡ።

13ቤቱም የሚገባው ሆኖ ከተገኘ፣ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስላችሁ።

14ማንም ሰው ሊያስተናግዳችሁ ወይም የምትናገሩትን ሊሰማ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ከቤቱ ወይም ከከተማው ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ።

15እውነት እላችኋለሁ፤ በፍርድ ቀን በዚያች ከተማ ከሚደርሰው ቅጣት ይልቅ በሰዶምና በገሞራ የሚደርሰው ይቀላል።

16“እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል እልካችኋለሁ፤ ስለዚህ እንደ እባብ ብልኆች እንደ ርግብ የዋሃን ሁኑ።

17ሰዎች ይዘው ለፍርድ ወደ ሸንጎ ያቀርቧችኋል፤ በምኵራቦቻቸውም ይገርፏችኋል፤ ስለዚህ ከእነርሱ ተጠንቀቁ።

18በእኔ ምክንያት ወደ ገዦችና ወደ ነገሥታት ትወሰዳላችሁ፤ በእነርሱና በአሕዛብም ፊት ምስክር ትሆናላችሁ።

19በምትያዙበትም ጊዜ ምን እንናገራለን፣ ምንስ እንመልሳለን ብላችሁ አትጨነቁ፤ በዚያን ጊዜ የምትናገሩት ይሰጣችኋል፤

20በእናንተ የሚናገረው የሰማዩ አባታችሁ መንፈስ እንጂ እናንተ አይደላችሁምና።

21“ወንድም ወንድሙን ለሞት አሳልፎ ይሰጣል፤ አባትም ልጁን፤ ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ያምፃሉ፤ ያስገድሏቸዋልም።

22ስለ ስሜ ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ ነገር ግን እስከ መጨረሻ የሚጸና እርሱ ይድናል።

23በአንድ ስፍራ ሲያሳድዷችሁ ወደ ሌላ ሽሹ፤ እውነት እላችኋለሁ፣ የእስራኤልን ከተሞች ሳታዳርሱ የሰው ልጅ ይመጣል።

24“ደቀ መዝሙር ከመምህሩ፣ ሎሌም ከጌታው አይበልጥም፤

25ደቀ መዝሙር መምህሩን፣ ሎሌም ጌታውን ከመሰለ ይበቃዋል። ባለቤቱን ‘ብዔልዜቡል’ ካሉት ቤተ ሰዎቹንማ እንዴት አብልጠው አይሏቸውም!

26“ስለዚህ አትፍሯቸው፤ የተሸፈነ መገለጡ፣ የተደበቀ መውጣቱ አይቀርምና።

27በጨለማ የምነግራችሁን በብርሃን አውሩት፤ በጆሮአችሁ የሰማችሁትን በአደባባይ አውጁት፤

28ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ።

29በአንድ ሳንቲም ከሚሸጡት ሁለት ድንቢጦች አንዲቷ እንኳ ያለ አባታችሁ ፈቃድ ምድር ላይ አትወድቅም።

30የራስ ጠጕራችሁ እንኳ አንድ ሳይቀር የተቈጠረ ነው።

31ስለዚህ አትፍሩ፤ ከብዙ ድንቢጦች ይልቅ ዋጋችሁ የከበረ ነው።

32“በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ፣ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤

33ነገር ግን በሰው ፊት የሚክደኝን፣ እኔም በሰማይ ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ።

34“እኔ የመጣሁት ሰላምን በምድር ለማስፈን አይምሰላችሁ፤ ሰይፍን እንጂ ሰላምን ለማውረድ አልመጣሁም።

35እኔ የመጣሁት “ ‘ልጅን ከአባት፣ ሴት ልጅን ከእናቷ ምራትንም ከዐማቷ ለመለያየት ነው፤

36የሰው ጠላቶቹ፣ የገዛ ቤተ ሰዎቹ ይሆናሉ።’

37“ከእኔ ይልቅ እናቱን ወይም አባቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባም፤ ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባም።

38መስቀሉን ተሸክሞ የማይከተለኝ የእኔ ሊሆን አይገባውም።

39ሕይወቱን ሊያድን የሚፈልግ ያጠፋታል፤ ሕይወቱን ስለ እኔ አሳልፎ የሚሰጥ ግን ያገኛታል።

40“እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።

41ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ያገኛል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ያገኛል።

42ስለዚህ እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም ሰው ከእነዚህ ከታናናሾች ለአንዱ ደቀ መዝሙሬ በመሆኑ አንድ ጽዋ ቀዝቃዛ ውሃ ቢሰጠው ዋጋውን አያጣም።”

ማብራሪያ

ማቴዎስ 10:1-4

ሐዋርያ የሚለው ቃል መልእክተኛን ያመለክታል፤ እነርሱም መንግሥቱን እንዲሰብኩ የተላኩ የክርስቶስ መልእክተኞች ነበሩ። ክርስቶስም ልዩ ልዩ ደዌንና ሕመምን ሁሉ እንዲፈውሱ ኃይልን አጎናጸፋቸው። በወንጌል ጸጋ ውስጥ ለእያንዳንዱ ደዌ መድኃኒት፣ ለማንኛውም ሕመም ፈውስ አለ። ለማንኛውም መንፈሳዊ ደዌ፣ በክርስቶስ ዘንድ የፈውስ ኃይል አለ። ስማቸው ተመዝግቦአል፤ ይህም ክብራቸው ነው። ይሁን እንጂ ስማቸው በሰማይ ተጽፎአልና የበለጠ ደስ ሊላቸው ይገባ ነበር። በዚህ መካከል ግን የምድር ታላላቅና ኃያል ስሞች በዐፈር ውስጥ ይቀበራሉ።

ማቴዎስ 10:5-15

አሕዛብ ወንጌል እንዲቀርብላቸው አይገባም ነበር፣ አይሁድ እስከሚከለክሉት ድረስ። በሐዋርያት ላይ ይህ እገዳ የተጣለው በመጀመሪያው ተልዕኳቸው ጊዜ ብቻ ነበር። በሄዱበት ሁሉ፡- “የሰማያት መንግሥት ቀርባለች” ብለው ማወጅ ነበረባቸው። እምነትን ለማጽናት ሰበኩ፤ መንግሥቱን ደግሞ ተስፋን ለማነቃቃት፤ የሰማዩን ነገር፣ የሰማያዊ ነገሮችን ፍቅር ለማነሳሳትና የምድራዊ ነገሮችንም ንቀት ለመፍጠር ሰበኩ፤ ቀርባለችና ሰዎች ያለመዘግየት እንዲዘጋጁባት። ክርስቶስም ትምህርታቸውን ለማረጋገጥ ተአምራት እንዲሠሩ ኃይል ሰጣቸው። አሁን ግን የእግዚአብሔር መንግሥት መጥታለችና ይህ አስፈላጊ አይደለም። ይህ የሚያሳየው የሰበኩት ትምህርት ዓላማ የታመሙ ነፍሳትን መፈወስና በኃጢአት የሞቱትንም ማስነሳት እንደነበር ነው። የሰዎችን ነፍስ ለመፈወስና ለማዳን የነጻውን ጸጋ ወንጌል በማወጅ፣ ከሁሉም በላይ በቅጥረኛ መንፈስ ከመታየት መራቅ አለብን።

በማያውቁአቸው ከተሞችና መንደሮች ምን ማድረግ እንዳለባቸውም መመሪያ ተሰጣቸው። የክርስቶስ አገልጋይ ወደ ተላከበት ስፍራ ሁሉ የሰላም መልዕክተኛ ነው። መልዕክቱ እጅግ ለከፉ ኃጢአተኞች እንኳ ቢሆንም፣ በየስፍራው ያሉትን ምርጥ ሰዎችን መፈለግ ይገባዋል። ለሁሉም በቅንነት መጸለይ ይገባናል፣ ከሁሉም ጋርም በትህትና መመላለስ ይገባናል። እነሱንም የከለከሉአቸውን ሰዎች በተመለከተ እንዴት ማድረግ እንዳለባቸው መመሪያ ተሰጣቸው። የእግዚአብሔር ሙሉ ምክር መታወቅ አለበት፤ ጸጋ የተሞላውን መልዕክት የማያዳምጡም ሰዎች፣ ሁኔታቸው አደገኛ እንደሆነ መታየት አለበት። ይህም ወንጌልን በሚሰሙ ሁሉ በቁም ነገር በልብ ሊያዝ ይገባዋል፣ መብቶቻቸውም የፍርዳቸውን ብዛት ለመጨመር ብቻ እንዳይሆን።

10:16-42 ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ስደት እንዲጠብቁ አስጠንቅቋቸዋል። ጠላቶቻቸውን የሚያስመች ነገር ሁሉ፣ ከዓለማዊና ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር መወራረድን ሁሉ፣ የክፋትና የራስ ወዳድነትን መልክ ሁሉ፣ እንዲሁም ተንኮለኛ ዘዴዎችን ሁሉ እንዲርቁ ነግሯቸዋል። ክርስቶስ መከራዎችን አስቀድሞ የተናገረው መከራዎቹ አስደንጋጭ እንዳይሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ እምነታቸውን እንዲያጸኑም ጭምር ነበር።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

AMHEVG አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ፥ እንዲያወጡአቸው በርኩሳን መናፍስት ላይ ደዌንና ሕማምንም ሁሉ እንዲፈውሱ ሥልጣን ሰጣቸው። አማርኛ ENGNIV He called his twelve disciples to him and gave them authority to drive out evil spirits and to heal every disease and s… English BCV ኢየሱስ ነቶም ዓሰርተ ኽልተ ደቀ መዛሙርቱ ፀዊዑ፥ ንርኹሳት መናፍስቲ ኸውፅእዎም፥ ንዝኾነ ደዌን ሕማምን ድማ፥ ከሕውዩ ስልጣን ሃቦም። ትግርኛ GAZBIB Yesus bartoota isaa kudha lamaan ofitti waamee, hafuurota xuraa'ota akka baasaniif, dhukkubaa fi dhibee hundumaas akka … Afaan Oromoo BCV GIZ ወጸውዖሙ ለዐሠርቱ ወክልኤቱ አርዳኢሁ ወወሀቦሙ ሥልጣነ ዲበ መናፍስት ርኩሳን ከመ ያውፅእዎሙ ወይፈውሱ ኵሎ ድዉያነ ወሕሙማነ። giz GAZGAZ Yesus bartoota isaa kudha lamaan ofitti waamee, hafuurota xuraa'ota akka baasaniif, dhukkubaa fi dhibee hundumaas akka … Afaan Oromoo BCV aksum ኢየሱስ ነቶም ዓሰርተ ኽልተ ደቀ መዛሙርቱ ፀዊዑ፥ ንርኹሳት መናፍስቲ ኸውፅእዎም፥ ንዝኾነ ደዌን ሕማምን ድማ፥ ከሕውዩ ስልጣን ሃቦም። ትግርኛ SWAHSUV Akawaita wanafunzi wake kumi na wawili, akawapa amri juu ya pepo wachafu, wawatoe, na kupoza magonjwa yote na udhaifu w… Kiswahili