የሉቃስ ወንጌል 9

AMHNIVአማርኛ62 ጥቅሶች10:21 አዳምጥ
አዳምጥ 10:21 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ኢየሱስም ዐሥራ ሁለቱን ሐዋርያት በአንድነት ጠርቶ አጋንንትን ሁሉ እንዲያወጡ፣ ደዌንም እንዲፈውሱ ኀይልና ሥልጣን ሰጣቸው፤

2ደግሞም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዲሰብኩና የታመሙትን እንዲፈውሱ ላካቸው፤

3እንዲህም አላቸው፤ “ለመንገዳችሁ በትር ቢሆን፣ ከረጢትም ቢሆን፣ እንጀራም ቢሆን፣ ገንዘብም ቢሆን፣ ሁለት ሁለት እጀ ጠባብም መያዝ አያስፈልጋችሁም።

4ከዚያ ከተማ እስከምትወጡ ድረስ መጀመሪያ በገባችሁበት በማንኛውም ቤት ቈዩ።

5የከተማው ሰዎች ሳይቀበሏችሁ ቀርተው ከተማቸውን ለቃችሁ ስትሄዱ፣ ምስክር እንዲሆንባቸው የእግራችሁን ትቢያ አራግፋችሁ ውጡ።”

6እነርሱም በዚሁ መሠረት ወጥተው ወንጌልን እየሰበኩ በየቦታው ሁሉ ሕመምተኞችን እየፈወሱ በየመንደሩ ያልፉ ነበር።

7የአራተኛው ክፍል ገዥ ሄሮድስም፣ በዚህ ጊዜ የሆነውን ነገር ሁሉ ሰምቶ በሁኔታው ተደናገረ፤ ምክንያቱም አንዳንድ ሰዎች ዮሐንስ ከሙታን እንደ ተነሣ ያወሩ ነበር፤

8ሌሎች ኤልያስ እንደ ተገለጠ፣ ሌሎች ደግሞ ከቀድሞዎቹ ነቢያት አንዱ ከሙታን እንደ ተነሣ ይናገሩ ነበር።

9ሄሮድስም፣ “መጥምቁ ዮሐንስን እኔው ራሴ ዐንገቱን አስቈርጬው ሞቶአል፤ ታዲያ፣ ስለ እርሱ እንዲህ ሲወራ የምሰማው ይህ ሰው ማነው?” አለ፤ በዐይኑም ሊያየው ይሻ ነበር።

10ሐዋርያትም ተመልሰው በመጡ ጊዜ ያደረጉትን ሁሉ ነገሩት፤ እርሱም ይዞአቸው ቤተ ሳይዳ ወደምትባል ከተማ በመሄድ ለብቻው ገለል አለ።

11ሕዝቡም ይህንኑ ዐውቀው ተከተሉት፤ እርሱም ተቀብሎአቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ይነግራቸው ነበር፤ ፈውስ የሚያስፈልጋቸውንም ፈወሳቸው።

12ቀኑም ሊመሽ ሲል፣ ዐሥራ ሁለቱ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “ያለ ነው በምድረ በዳ ስለ ሆነ፣ ሕዝቡ ወደ አካባቢው መንደርና ገጠር ሄደው ማደሪያና ምግብ እንዲፈልጉ አሰናብታቸው” አሉት።

13እርሱ ግን፣ “የሚበሉትን እናንተው ስጧቸው” አላቸው። እነርሱም፣ “ለዚህ ሁሉ ሕዝብ የሚበቃ ምግብ ሄደን ካልገዛን በስተቀር፣ እኛ ያለን ከአምስት እንጀራና ከሁለት ዓሣ አይበልጥም” አሉት፤

14አምስት ሺህ ያህል ወንዶች በዚያ ነበሩና። ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱን፣ “ሕዝቡን በአምሳ በአምሳ ሰው መድባችሁ አስቀምጧቸው” አላቸው።

15ደቀ መዛሙርቱም በታዘዙት መሠረት ሰዎቹ እንዲቀመጡ አደረጉ።

16እርሱም አምስቱን እንጀራና ሁለቱን ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ እያየ ባረካቸው፤ ቈርሶም ለሕዝቡ እንዲያቀርቡ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ።

17ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ደቀ መዛሙርቱም ከእነርሱ የተረፈውን ቊርስራሽ እንጀራ ዐሥራ ሁለት መሶብ አነሡ።

18ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ይጸልይ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ፤ እርሱም፣ “ሕዝቡ እኔን ማን ነው ይሉኛል?” ብሎ ጠየቃቸው።

19እነርሱም፣ “አንዳንዶች መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ከቀድሞ ነቢያት አንዱ ከሙታን ተነሥቶአል ይላሉ” አሉት።

20እርሱም፣ “እናንተስ ማን ነው ትሉኛላችሁ?” አላቸው። ጴጥሮስም፣ “አንተ የእግዚአብሔር መሲሕ ነህ” ሲል መለሰለት።

21ኢየሱስም ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አጥብቆ አስጠነቀቃቸው፤

22ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ብዙ መከራ መቀበል ይገባዋል፤ እንዲሁም በሽማግሌዎች፣ በካህናት አለቆችና በጸሓፍት ዘንድ መናቅ፣ መገደልና በሦስተኛውም ቀን ከሙታን መነሣት አለበት” አላቸው።

23ከዚያም ለሁሉም እንዲህ አላቸው፤ “በኋላዬ ሊመጣ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም በየዕለቱ ተሸክሞ ይከተለኝ፤

24ምክንያቱም ነፍሱን ሊያድናት የሚፈልግ ሁሉ ያጠፋታል፤ ነፍሱን ስለ እኔ ብሎ የሚያጠፋት ግን ያድናታል።

25ሰው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ግን ቢያጠፋ ወይም ቢያጐድል ጥቅሙ ምንድን ነው?

26ማንም በእኔና በቃሌ ቢያፍር፣ የሰው ልጅ በራሱ ክብር እንዲሁም በአብና በቅዱሳን መላእክት ክብር ሲመጣ ያፍርበታል።

27እውነት እላችኋለሁ፤ እዚህ ከቆሙት መካከል የእግዚአብሔርን መንግሥት ሳያዩ ሞትን የማይቀምሱ ሰዎች አሉ።”

28ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ሊጸልይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ።

29በመጸለይ ላይ እንዳለም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ የሚያንጸባርቅ ነጭ ሆነ።

30እነሆ፤ ሁለት ሰዎች፣ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤

31በክብርም ተገልጠው፣ በኢየሩሳሌም ይፈጸም ዘንድ ስላለው ከዚህ ዓለም ስለ መለየቱ ይናገሩ ነበር።

32ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት ግን እንቅልፍ ተጭኖአቸው ነበር፤ ሲነቁ ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር የቆሙትን ሁለት ሰዎች አዩ።

33ሰዎቹም ከኢየሱስ ተለይተው ሲሄዱ፣ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ እዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ሦስት ዳስ እንሥራ፤ አንዱ ለአንተ፣ አንዱ ለሙሴ፣ አንዱም ለኤልያስ ይሆናል” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር።

34ይህንም እየተናገረ ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ፈሩ።

35ከደመናውም ውስጥ፣ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ።

36ድምፁም በተሰማ ጊዜ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ፤ ደቀ መዛሙርቱም ነገሩን በልባቸው ያዙ እንጂ ስላዩት ነገር በዚያን ወቅት ለማንም አልተናገሩም።

37በማግሥቱ ከተራራው ከወረዱ በኋላ፣ ብዙ ሕዝብ መጥቶ ኢየሱስን አገኘው።

38በዚህ ጊዜ ከሕዝቡ መካከል አንድ ሰው ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ “መምህር ሆይ፤ ያለኝ ልጅ እርሱ ብቻ ስለ ሆነ ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ።

39መንፈስ ሲይዘው በድንገት ይጮኻል፤ አረፋ እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፤ ጒዳትም ካደረሰበት በኋላ በስንት መከራ ይተወዋል፤

40ደቀ መዛሙርትህ እንዲያወጡለት ለመንኋቸው፤ ነገር ግን አልቻሉም።”

41ኢየሱስም “እምነት የለሽ ጠማማ ትውልድ፤ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? በል ልጅህን ወደዚህ አምጣው” አለ።

42ልጁ በመምጣት ላይ ሳለም ጋኔኑ መሬት ላይ ጥሎ አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኩሱን መንፈስ ገሥጾ ልጁን ፈወሰው፤ ለአባቱም መልሶ ሰጠው።

43ሰዎቹም ሁሉ በእግዚአብሔር ታላቅነት ተገረሙ። እርሱ ባደረገው ሁሉ ሰዎች ሁሉ እየተገረሙ ሳሉ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን፣

44“ይህን የምነግራችሁን ነገር ከቶ እንዳትዘነጉ፤ የሰው ልጅ አልፎ በሰዎች እጅ ይሰጣልና” አለ።

45እነርሱ ግን ይህን አባባል አልተረዱም፤ እንዳያስተውሉ ነገሩ ተሰውሮባቸው ነበር፤ መልሰው እንዳይጠይቁትም ፈሩ።

46ከእነርሱ ማን እንደሚበልጥ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ክርክር ተነሣ።

47ኢየሱስም የልባቸውን ሐሳብ ተረድቶ፣ አንድ ሕፃን ይዞ በአጠገቡ አቆመ፤

48እንዲህም አላቸው፤ “ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል ማንም ቢኖር እኔን ይቀበላል፤ እኔን የሚቀበል ደግሞ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ከሁሉ ይበልጣልና።”

49ዮሐንስም፣ “ጌታ ሆይ፤ አንድ ሰው በስምህ አጋንንት ሲያወጣ አየን፤ ከእኛ ጋር ሆኖ ስለማይከተል ልንከለክለው ሞከርን” አለው።

50ኢየሱስም፣ አትከልክሉት “የማይቃወማችሁ ሁሉ እርሱ ከእናንተ ጋር ነውና” አለው።

51ኢየሱስ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ጊዜ በመቃረቡ፣ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ቈርጦ ተነሣ፤

52አስቀድሞም መልእክተኞችን ወደዚያ ላከ። እነርሱም ሁኔታዎችን አስቀድመው ሊያመቻቹለት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር ገቡ።

53ሕዝቡ ግን ወደ ኢየሩሳሌም እያመራ መሆኑን ስላወቁ አልተቀበሉትም።

54ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ ይህን ሲያዩ፣ “ጌታ ሆይ፤ ኤልያስ እንዳደረገው ሁሉ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው እንድናዝ ትፈቅዳለህን?” አሉት።

55ኢየሱስ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና “እናንተ ከምን ዐይነት መንፈስ እንደሆናችሁ አታውቁም፤ የሰው ልጅ የመጣው የሰውን ሕይወት ለማዳን ነው እንጂ ለማጥፋት አይደለምና” አላቸው፤

56ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።

57በመንገድ ሲሄዱም አንድ ሰው ቀርቦ፣ “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ” አለው።

58ኢየሱስም፣ “ቀበሮዎች ጒድጓድ፣ የሰማይ ወፎችም ጎጆ አላቸው፤ የሰው ልጅ ግን ዐንገቱን እንኳ የሚያስገባበት የለውም” አለው።

59ሌላውን ሰው ግን፣ “ተከተለኝ” አለው። ሰውየውም፣ “ጌታ ሆይ፤ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን ልቅበር” አለው።

60ኢየሱስም፣ “ሙታን ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ተዋቸው፤ አንተ ግን ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ” አለው።

61ሌላ ሰው ደግሞ፣ “ጌታ ሆይ፤ መከተልስ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን ልመለስና መጀመሪያ የቤቴን ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ” አለ።

62ኢየሱስ ግን፣ “ዕርፍ ጨብጦ ወደ ኋላ የሚመለከት ሰው ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም” አለው።

ማብራሪያ

፱፥፩-፱ ክርስቶስ አስራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርቱን ወደ ውጭ ላካቸው፤ እነርሱም በዚያን ጊዜ ከጌታ የተቀበሉትን ለሌሎች ለማስተማር ብቁ ሆነው ነበር። በውጫዊ አኳኋን የሰዎችን ክብርና አድናቆት ለማግኘት መጣር የለባቸውም ነበር። እንዳሉ ሆነው መሄድ ነበረባቸው። ጌታ ኢየሱስ የኃይልና የስልጣን ምንጭ ነውና፣ ፍጥረታት ሁሉ በማንኛውም መንገድ ለእርሱ ሊገዙ ይገባቸዋል። እርሱም የአገልጋዮቹን ቃል በኃይል አስከትሎ፣ ኃጢአተኞችን ከሰይጣን እስራት ነጻ ለማውጣት ከሄደ፣ የእነርሱን ፍላጎት እንደሚንከባከብ እርግጠኛ መሆን ይችላሉ።

እውነትና ፍቅር በዚህ መልኩ አንድ ላይ ሲጓዙ፣ ሆኖም የእግዚአብሔር መልእክት ውድቅ ሲደረግና ሲናቅ፣ ሰዎችን ያለ ይቅርታ ይተዋቸዋል፣ እንዲሁም በእነርሱ ላይ ምስክርነት ይሆናል። የሄሮድስ የጥፋተኝነት ህሊናው ዮሐንስ ከሞት እንደተነሳ ለመደምደም ተዘጋጅቶ ነበር። ኢየሱስን ለማየት ፈለገ፤ ታዲያ ለምን ሄዶ አላየውም? ምናልባትም ለእርሱ እንደማይገባው ስለገመተ፣ ወይም ደግሞ የበደሉ ተግሳጮች እንዲበዙበት ስላልፈለገ ሊሆን ይችላል። አሁን በማዘግየቱ ልቡ ጠነከረ፤ ኢየሱስንም ባየ ጊዜ፣ እንደሌሎች ሰዎች ሁሉ በእርሱ ላይ የጠነከረ ጭፍን ጥላቻ ነበረው፣ ሉቃስ ፳፫፥፲፩።

9:10-17 ሕዝቡ ኢየሱስን ተከተሉት፤ ምንም እንኳ ባልተመቸ ሰዓት ቢመጡም፣ የፈለጉትን ሰጣቸው። እርሱም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ተናገራቸው፤ መፈወስ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ፈወሰ። በአምስት እንጀራና በሁለት ዓሣም ክርስቶስ አምስት ሺህ ወንዶችን መገበ። እርሱን የሚፈሩትንና በታማኝነትም የሚያገለግሉትን ምንም መልካም ነገር አያሳጣቸውም። ከፍጥረት የሚመጡ ምቾቶችን ስንቀበል፣ ከእግዚአብሔር እንደተቀበልናቸውና እነርሱንም ለመቀበል እንደማይገባን መቀበል አለብን፤ እነዚህ ሁሉ፣ በእነርሱም ውስጥ ያለን መጽናናት ሁሉ፣ እርግማኑ በእርሱ በተወገደው በክርስቶስ አማላጅነት የተገኙ እንደሆኑ ልናውቅ ይገባል። የክርስቶስ በረከት ትንሽ ነገርን ታላቅ ያደርገዋል። እርሱም የተራበችን ነፍስ ሁሉ በቤቱ በጎነት አብዝቶ ያጠግባታል። እዚህ የቀሩ ፍርፋሪዎች ተሰብስበው ነበር፤ በአባታችንም ቤት የሚበቃ እንጀራ አለ፣ ከሚተርፍም ጋር። በክርስቶስ አንጠበብም፤ አትጎድልብንምም።

9:18-27 ጌታችን ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቅቡዕ መሆኑ ሊነገር ከማይችል በላይ መጽናናት ነው። ይህ እርሱ መሲሕ እንዲሆን እንደተሾመ እና ለዚያም ብቁ እንደሆነ ያመለክታል። ኢየሱስ ስለራሱ መከራና ሞት ተናገረ። ደቀ መዛሙርቱም መከራውን እንዴት መከላከል እንደሚችሉ ከማሰብ ይልቅ፣ ለራሳቸው መዘጋጀት አለባቸው። የግዴታችንን መንገድ ስንሄድ ብዙውን ጊዜ መስቀሎችን እናገኛለን፤ እነርሱን በራሳችን ላይ መጎተት ባይገባንም፣ ነገር ግን ለእኛ ሲቀመጡልን፣ ልናነሳቸውና ክርስቶስን ተከትለን ልንሸከማቸው ይገባል። ከእኛ ጋር መልካም የሚሆነው ወይም መጥፎ የሚሆነው ከነፍሳችን ጋር መልካም ወይም መጥፎ እንደሆነ ነው። ነፍስ በሌላው ዓለም ደስተኛ ካልሆነች ሥጋ ደስተኛ መሆን አይችልም፤ ነገር ግን በዚህ ዓለም ሥጋ እጅግ ቢሰቃይም እና ቢጨነቅም፣ ነፍስ ደስተኛ ልትሆን ትችላለች። በክርስቶስና በወንጌሉ በፍጹም ማፈር የለብንም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6