1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦
2“የእስራኤል ልጆች ለእኔ ከሚቀድሱአቸው ከቅዱሳን ነገሮች ራሳቸውን እንዲለዩ፥ የተቀደሰውንም ስሜን እንዳያረክሱ ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
3“እንዲህ በላቸው፦ ‘ማናቸውም ሰው ከዘራችሁ በትውልዳችሁ ርኵሰት እያለበት የእስራኤል ልጆች ለእግዚአብሔር ወደሚቀድሱት ወደ ቅዱስ ነገር ቢቀርብ፥ ያ ሰው ከፊቴ ተለይቶ ይጥፋ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
4“ ‘ከአሮን ዘር ለምጽ ወይም ፈሳሽ ነገር ያለበት ሁሉ ንጹሕ እስኪሆን ድረስ ከተቀደሰው አይብላ። ከበድንም የተነሣ ርኩስ የሆነውን፥ ወይም ዘሩ ከእርሱ የሚፈስስበትን የሚነካ፥
5ወይም የሚያረክሰውን ተንቀሳቃሽ፥ ወይም በሁሉ ዓይነት የረከሰውን ሰው የሚነካ፥
6እነዚህን ሁሉ የሚነካ ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ገላውን በውኃ ካልታጠበ ከተቀደሰው አይብላ።
7ፀሐይም በገባች ጊዜ ንጹሕ ይሆናል፤ ከዚያም በኋላ እንጀራው ነውና ከተቀደሰው ይብላ።
8በእርሱም እንዳይረክስ፥ የሞተውን አውሬም የሰበረውን አይብላ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
9“ ‘ቢያረክሱአት እንዳይሞቱ ስለ እርስዋም ኃጢአትን እንዳይሸከሙ፥ ሕግን ይጠብቁ፤ የምቀድሳቸው እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
10“ ‘ልዩ ሰው ከተቀደሰው አይብላ የካህኑም እንግዳ ደመወዘኛውም ከተቀደሰው አይብላ።
11ካህኑ ግን በገንዘቡ ባሪያ ቢገዛ እርሱ ይብላው፤ በቤቱም የተወለዱት ከእንጀራው ይብሉ።
12የካህንም ልጅ ከልዩ ሰው ጋር ብትጋባ፥ እርስዋ ከተቀደሰው ቍርባን አትብላ።
13የካህን ልጅ ግን ባልዋ ቢሞት፥ ወይም ብትፋታ፥ ልጅም ባይኖራት፥ በብላቴንነትዋ እንደ ነበረች ወደ አባትዋ ቤት ብትመለስ፥ ከአባትዋ እንጀራ ትብላ፤ ልዩ ሰው ግን ከእርሱ አይብላ።
14“ ‘ማናቸውም ሰው ሳያውቅ ከተቀደሰው ቢበላ አምስተኛ እጅ ጨምሮ የተቀደሰውን ለካህኑ ይስጥ።
15የምቀድሳቸውም እግዚአብሔር እኔ ነኝና ከተቀደሰው በበሉ ጊዜ ኃጢአትንና በደልን እንዳይሸከሙ ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርቡትን በእስራኤል ልጆች ዘንድ የተቀደሰውን ነገር አያርክሱ።’ ”
17እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦
18“ለአሮንና ለልጆቹ ለእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘ከእስራኤል ቤት ወይም ከእናንተ መካከል ከሚቀመጡት እንግዶች ማናቸውም ሰው ስእለቱን ሁሉ፥ በፈቃዱም የሚያቀርበውን ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያቀርበውን ቍርባን ቢያቀርብ፥
19ይሠምርላችሁ ዘንድ ከበሬ ወይም ከበግ ወይም ከፍየል ነውር የሌለበትን ተባቱን አቅርቡ።
20ነገር ግን አይሠምርላችሁምና ነውር ያለበትን አታቅርቡ።
21ማናቸውም ሰው ስእለቱን ለመፈጸም ወይም በፈቃዱ ለማቅረብ የደኅንነትን መሥዋዕት፥ ወይም በሬን ወይም በግን፥ ለእግዚአብሔር ቢያቀርብ፥ ይሠምርለት ዘንድ ፍጹም ይሁን፥ ነውርም አይሁንበት።
22ዕውር ወይም ሰባራ ወይም ጕንድሽ ወይም የሚመግል ቍስል ያለበት ወይም እከካም ወይም ቋቍቻም ቢሆን፥ እነዚህን ሁሉ ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ እነዚህም ለእሳት ቍርባን በመሠዊያው ላይ ለእግዚአብሔር አታሳርጉ።
23በሬው ወይም በጉ የተጨመረበት ወይም የጐደለበት ነገር ቢሆን፥ ለፈቃድ መሥዋዕት ማቅረብ ትችላለህ፤ ለስእለት ግን አይሠምርም።
24የተሰነጋውን ወይም የተቀጠቀጠውን ወይም የተሰበረውን ወይም የተቈረጠውን ለእግዚአብሔር አታቅርቡ፤ በምድራችሁም እነዚህን አትሠዉ።
25ከእነዚህም ከእንግዳ ሰው እጅ ለአምላካችሁ እንጀራ አታቅርቡ፤ ርኵሰትም ነውርም አለባቸውና አይሠምሩላችሁም።’ ”
26እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦
27“በሬ ወይም በግ ወይም ፍየል ሲወለድ ሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቀመጥ፤ በስምንተኛውም ቀን ከዚያም በላይ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን የሠመረ ይሆናል።
28ላም ወይም በግ ብትሆን እርስዋንና ልጅዋን በአንድ ቀን አትረዱ።
29“የምስጋናንም መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ስትሠዉ እንዲሠምርላችሁ ሠዉለት።
30በዚያው ቀን ይበላል፤ ከእርሱ እስከ ነገ ምንም አትተዉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
31“ትእዛዛቴን ጠብቁ፥ አድርጉትም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
32የተቀደሰውንም ስሜን አታርክሱ፤ እኔ ግን በእስራኤል ልጆች መካከል እቀደሳለሁ፤
33የምቀድሳችሁ፥ አምላካችሁም እሆን ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር ነኝ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”