1በቊጣው በትር፣ መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ።
2ከፊቱ አስወጣኝ፤ በብርሃን ሳይሆን በጨለማ እንድሄድ አደረገኝ።
3በእርግጥ ቀኑን ሁሉ በመደጋገም፣ እጁን በላዬ ላይ መለሰ።
4እርሱ ሥጋዬንና ቈዳዬን አስረጀ፤ ዐጥንቶቼንም ሰባበረ።
5በምሬትና በድካም፣ ቅጥር ሠራብኝ፤ ዙሪያዬንም ከበበኝ።
6ከሞቱ ብዙ ጊዜ እንደሆናቸው፣ በጨለማ እንድኖር አደረገኝ።
7በቅጥር ውስጥ ዘጋብኝ፤ ስለዚህ ማምለጥ አልቻልሁም፤ የእስር ሰንሰለቴንም አከበደብኝ።
8ርዳታ ፈልጌ ብጣራና ብጮኽ እንኳ፣ ጸሎቴን መስማት አልፈለገም።
9መንገዴን በተጠረቡ ድንጋዮች ዘጋ፤ ጐዳናዬንም አጣመመ።
10አሸምቆ እንደ ተኛ ድብ፣ እንደ አደባም አንበሳ፣
11ከመንገድ ጐትቶ አስወጣኝ፤ ቈራረጠኝም፤ ያለ ረዳትም ተወኝ።
12ቀስቱን ገተረ፤ ለፍላጻዎቹም ዒላማ አደረገኝ።
13ፍላጻዎችን ከሰገባው አውጥቶ፣ ልቤን ወጋው።
14ለሕዝቤ ሁሉ ማላገጫ ሆንሁኝ፤ ቀኑን ሙሉ በመሣለቅ ያዜሙብኛል።
15መራራ ሥር አበላኝ፤ ሐሞትም አጠገበኝ።
16ጥርሴን በድንጋይ ሰበረ፤ በትቢያ ውስጥ ረጋገጠኝ።
17ነፍሴ ሰላምን አጣች፤ ደስታ ምን እንደሆነ ረሳሁ።
18ስለዚህ፣ “ክብሬ፣ ከእግዚአብሔርም ተስፋ ያደረግሁት ሁሉ ሄዶአል” አልሁ።
19የጭንቀቴንና የመንከራተቴን፣ ምሬትንና ሐሞትን አስባለሁ።
20ዘወትር አስበዋለሁ፤ ነፍሴም በውስጤ ተዋርዳለች።
21ሆኖም ይህን አስባለሁ እንግዲያስ ተስፋ አለኝ፤
22ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ታላቅ ፍቅር የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና።
23ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህም ብዙ ነው።
24ራሴን እንዲህ አልሁት፤ “እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ።
25እርሱን ተስፋ ለሚያደርጉት፣ ለሚፈልገውም ሰው እግዚአብሔር መልካም ነው።
26ሰው የእግዚአብሔርን ማዳን፣ ዝም ብሎ ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው።
27ሰው በወጣትነቱ፣ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው።
28ብቻውን ዝም ብሎ ይቀመጥ፤ እግዚአብሔር አሸክሞታልና።
29ፊቱን በዐቧራ ውስጥ ይቅበር፤ ተስፋ ሊኖር ይችላልና።
30ጒንጩን ለሚመታው ሰው ይስጥ፤ ውርደትንም ይጥገብ።
31እግዚአብሔር ሰውን፣ ለዘላለም አይጥልምና፤
32መከራን ቢያመጣ እንኳ ይራራል፤ ታላቅ ፍቅሩ አይለወጥምና
33ሆን ብሎ ችግርን፣ ወይም መከራን በሰው ልጆች ላይ አያመጣምና።
34የምድሪቱ እስረኞች ሁሉ፣ በእግር ሲረገጡ፣
35በልዑል ፊት፣ ሰው መብቱ ሲነፈገው፣
36ሰው ፍትሕ ሲጓደልበት፣ ጌታ እንዲህ ዐይነቱን ነገር አያይምን?
37እግዚአብሔር ካላዘዘ በቀር፤ ተናግሮ መፈጸም የሚችል ማን ነው?
38ክፉም ሆነ መልካም ነገር፣ ከልዑል አፍ የሚወጣ አይደለምን?
39ታዲያ ሕያው ሰው በኀጢአቱ ሲቀጣ፣ ስለ ምን ያጒረመርማል?
40መንገዳችንን እንመርምር፤ እንፈትን፤ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ።
41ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ አምላካችን እናንሣ፤ እንዲህም እንበል፤
42“ዐምፀናል፤ ኀጢአትም ሠርተናል፤ አንተም ይቅር አላልኸንም።
43“ራስህን በቊጣ ከደንህ፤ አሳደድኸንም፤ ያለ ርኅራኄም ገደልኸን።
44ጸሎት እንዳያልፍ፣ ራስህን በደመና ሸፈንህ።
45በአሕዛብ መካከል፣ አተላና ጥራጊ አደረግኸን።
46“ጠላቶቻችን ሁሉ፣ አፋቸውን በእኛ ላይ ከፈቱ።
47በጥፋትና በመፈራረስ፣ በችግርና በሽብር ተሠቃየን።
48የእንባ ጐርፍ ከዐይኔ ፈሰሰ፤ ሕዝቤ አልቋልና።
49ያለ ዕረፍት፣ ያለ ማቋረጥ ዐይኖቼ እንባ ያፈሳሉ፤
50እግዚአብሔር ከላይ፣ ከሰማይ እስኪያይ ድረስ።
51በከተማዬ ባሉት ሴቶች ሁሉ ላይ የደረሰውን ማየቴ፣ ነፍሴን አስጨነቃት።
52ያለ ምክንያት ጠላቶቼ የሆኑ፣ እንደ ወፍ አደኑኝ።
53ሕይወቴን በጒድጓድ ውስጥ ሊያጠፉ ሞከሩ፣ ድንጋይም በላዬ አደረጉ።
54ውሃ ሞልቶ በዐናቴ ላይ ፈሰሰ፤ ጠፍቻለሁ ብዬ አሰብሁ።
55በጥልቁ ጒድጓድ ውስጥ ሳለሁ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ የአንተን ስም ጠራሁ።
56ልመናዬን ሰምተሃል፤ “ርዳታም ፈልጌ ስጮኽ፣ ከመስማት ጆሮህን አትከልክል።”
57በጠራሁህ ጊዜ ቀረብኸኝ፣ እንዲሁም፣ “አትፍራ” አልኸኝ።
58ጌታ ሆይ፤ ለእኔ ተሟገትኽልኝ፤ ሕይወቴንም ተቤዠህ።
59እግዚአብሔር ሆይ፤ በእኔ ላይ የተደረገውን ግፍ አየህ፤ ፍርዴን ፍረድልኝ!
60በቀላቸውን ሁሉ፣ በእኔም ላይ ያሰቡትን ዐድማ አየህ።
61እግዚአብሔር ሆይ፤ ስድባቸውን ሁሉ፣ በእኔ ላይ ያሰቡትን ዐድማ ሁሉ ሰማህ፤
62ይህም ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ፣ ጠላቶቼ የሚያውጠነጥኑትና የሚያንሾካሹኩት ነው።
63ተመልከታቸው! ቆመውም ሆነ ተቀምጠው፣ በዘፈናቸው ይሣለቁብኛል።
64እግዚአብሔር ሆይ፤ እጆቻቸው ላደረጉት፣ የሚገባውን መልሰህ ክፈላቸው።
65በልባቸው ላይ መጋረጃን ዘርጋ፤ ርግማንህም በላያቸው ይሁን!
66ከእግዚአብሔር ሰማያት በታች፣ በቊጣህ አሳድዳቸው፤ አጥፋቸውም።