1እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ፦
2“ያለ እውቀት በሚነገር ቃል፡ ምክርን የሚያጨልም ይህ ማነው?
3እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ።
4“ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ? ታስተውል እንደ ሆንህ ተናገር።
5ብታውቅስ መሠፈሪያዋን የወሰነ፥ በላይዋስ የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው?
6አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፥ የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፥ መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው?
8“ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ፡ ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው?
9ደመናውን ለልብሱ፥ ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፤
10ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፥ መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ፦
11‘እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ አትለፊ፤ በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን፡’ አልሁ።
12“የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥ ከእርስዋም በደለኞች ይናወጡ ዘንድ፥ በውኑ ከተወለድህ ጀምሮ ማለዳን አዝዘሃልን? ለወገግታም ስፍራውን አስታወቀኸዋልን?
14ጭቃ ከማኅተም በታች እንደሚለወጥ እንዲሁ እርስዋ ትለወጣለች፤ ነገርም ሁሉ እንደ ልብስ ተቀልሞአል።
15ከበደለኞች ብርሃናቸው ተከልክሎአል፥ ከፍ ያለውም ክንድ ተሰብሮአል።
16“ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገብተሃልን? በቀላዩስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን?
17የሞት በሮች ተገልጠውልሃልን? የሞትንስ ጥላ ደጆች አይተሃልን?
18ምድርንስ በስፋትዋ አስተውለሃታልን? ሁሉን አውቀህ እንደ ሆነ ተናገር።
19“ወደ ዳርቻው ትነዳው ዘንድ፥ ወደ ቤቱም የሚያደርሰውን ጐዳና ታውቅ ዘንድ፥ የብርሃን መኖሪያ መንገድ የት ነው? የጨለማውስ ቦታ ወዴት አለ?
21በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥ የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፤ በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም።
22“በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን? የበረዶውንስ ቅንጣት ቤተ መዛግብት አይተሃልን?
23ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለሰልፍና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው።
24ብርሃንስ በምን መንገድ ይከፈላል? የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ እንዴት ይበተናል?
25ባድማውንና ውድማውን እንዲያጠግብ፥ ሣሩንም እንዲያበቅል፤ ማንም በሌለባት ምድር ላይ፥ ሰውም በሌለባት ምድረ በዳ ላይ ዝናብን ያዘንብ ዘንድ፥ ለፈሳሹ ውኃ መንዶልዶያውን፥ ወይስ ለሚያንጐደጕድ መብረቅ መንገድን ያበጀ ማን ነው?
28በውኑ ለዝናብ አባት አለውን? ወይስ የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው?
29በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ? የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው?
30ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥ የቀላዩም ፊት ረግቶአል።
31“በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥ ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን?
32ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥ ወይስ ድብ የሚባለውን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን?
33የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን? በምድርስ ለይ እንዲሠለጥን ልታደርግ ትችላለህን?
34“የውኆች ብዛት ይሸፍንህ ዘንድ፡ ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን?
35መብረቆች ሄደው፦ ‘እነሆ፥ እዚህ አለን፡’ ይሉህ ዘንድ፡ ልትልካቸው ትችላለህን?
36በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥ ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው?
37የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው? ትቢያ በተበጠበጠ ጊዜ፥ ጓሎቹም በተጣበቁ ጊዜ፥ የሰማይን ረዋት ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው?
39“በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው፥ በጫካም ውስጥ አድብተው ሳሉ፥ ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን? የልጆችዋንስ ነፍስ ታጠግብ ዘንድ ትችላለህን?
41ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፥ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፥ ለቍራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?