1“ነፍሴ ሕይወቴን ሰለቸቻት፤ የኀዘን እንጕርጕሮዬን እለቅቀዋለሁ፤ በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ።
2እግዚአብሔርን እንዲህ እለዋለሁ፦ አትፍረድብኝ፤ የምትከራከረኝ ለምን እንደ ሆነ ንገረኝ።
3ልታስጨንቅና የእጅህን ሥራ ልትንቅ፡ የኃጥአንንስ ምክር ልታበራ፡ በአንተ ዘንድ መልካም ነውን?
4በውኑ የሥጋ ዓይን አለህን? ወይስ ሰው እንደሚያይ ታያለህን?
5ወይስ ክፋቴን ትፈላለግ ዘንድ፥ ኃጢአቴንም ትመረምር ዘንድ፥ ዘመንህ እንደ ሰው ዘመን ነውን? ወይስ ዓመታትህ እንደ ሰው ዓመታት ናቸውን?
7ከዚህም በላይ በደለኛ እንዳልሆንሁ፥ ከእጅህም የሚያድን እንደሌለ አንተ ታውቃለህ።
8“እጅህ ለወሰችኝ ሠራችኝም፤ ከዚያም በኋላ ዞረህ ታጠፋኝ ዘንድ ፈለግህ።
9እንደ ጭቃ አድርገህ እንደ ለወስኸኝ አስብ፤ ወደ ትቢያም ትመልሰኛለህን?
10በውኑ እንደ ወተት አላፈሰስኸኝምን? እንደ እርጎስ አላረጋኸኝምን?
11ቁርበትና ሥጋ አለበስኸኝ፥ በአጥንትና በጅማትም አጠነከርኸኝ።
12ሕይወትና ቸርነት አደረግህልኝ፤ መጐብኘትህም መንፈሴን ጠበቀች።
13“እነዚህንም ነገሮች በልብህ ውስጥ ሰወርህ። ይህ ሁሉ በአሳብህ እንዳለ አውቃለሁ።
14‘ኃጢአት ብሠራ አንተ ትመለከተኛለህ፤ ከኃጢአቴም ንጹሕ አታደርገኝም።
15በደለኛ ብሆን ወዮልኝ፤ ጻድቅም ብሆን ራሴን አላነሣም፤ ጕስቍልናን ተሞልቻለሁ፥ መከራዬንም ተመልክቻለሁ።
16ራሴም ከፍ ከፍ ቢል እንደ አንበሳ ታድነኛለህ፤ ተመልሰህም ድንቅ ነገር ታድርግብኛለህ።
17ምስክሮችህን ታድስብኛለህ፤ ቍጣህንም ታበዛብኛለህ፤ ጭፍራ በጭፍራ ላይ ትጨምርብኛለህ።
18“ስለ ምን ከማኅፀን አወጣኸኝ? ዓይን ሳያየኝ ምነው በሞትሁ።
19እንዳልነበረ በሆንሁ፤ ከማኅፀንም ወደ መቃብር በወሰዱኝ።
20የሕይወቴ ዘመን ጥቂት አይደለምን?
21ወደማልመለስበት ስፍራ፥ ወደ ጨለማና ወደ ሞት ጥላ ምድር፥
22እንደ ጨለማም ወደ ጨለመች፥ ሥርዓትም ወደሌለባት ወደ ሞት ጥላ፥ ብርሃንዋም እንደ ጨለማ ወደ ሆነ ምድር ሳልሄድ፥ ጥቂት እጽናና ዘንድ ተወኝ፥ ልቀቀኝም።”