1ፈርዖን ጋዛን ድል ከማድረጉ በፊት፣ ስለ ፍልስጥኤማውያን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤
2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ በሰሜን በኩል ውሃ እየሞላ ነው፣ ኀይለኛ ጐርፍ ይሆናል፤ አገሪቷንና በውስጧ ያሉትንም ሁሉ፣ ከተሞቿንና ነዋሪዎቻቸውን ያጥለቀልቃል። ሕዝቡም ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፤ የምድሪቱ ነዋሪ ሁሉ ዋይ ዋይ ይላል፤
3ከፈረስ ኮቴ ድምፅ፣ ከጠላት ሠረገላ ጩኸትና፣ ከሠረገላው ሽክርክሪት ፍትጊያ ድምፅ የተነሣ፣ አባቶች ልጆቻቸውን ለመርዳት ወደ ኋላ መለስ አይሉም፤ እጃቸውም ስንኩል ይሆናል።
4ፍልስጥኤማውያንን ሁሉ ለማጥፋት፣ ተርፈውም የሚረዷቸውን ሁሉ፣ ከጢሮስና ከሲዶና ለመቍረጥ፣ ቀኑ ደርሶአልና። እግዚአብሔር በከፍቶር ዳርቻ የቀሩትን፣ ፍልስጥኤማውያንን ሊያጠፋ ተነሥቶአል።
5ጋዛ በማዘን ራሷን ትላጫለች፣ አስቀሎና አፏን ትይዛለች። በሜዳማ ስፍራ የምትገኙ ትሩፋን ሆይ፤ እስከ መቼ ሰውነታችሁን ትቧጥጣላችሁ?
6“ ‘የእግዚአብሔር ሰይፍ ሆይ፤ የማታርፈው እስከ መቼ ነው? ወደ ሰገባህ ተመልሰህ ግባ፤ ጸጥ ብለህ ተቀመጥ’ ትላላችሁ።
7ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀሎናንና የባሕሩን ዳርቻ፣ እንዲወጋ ሲያዝዘው፣ እንዲፈጽመውም ትእዛዝ ሲሰጠው፣ እንዴት ማረፍ ይችላል?”