1የጭፍራ አለቆችም ሁሉ የቃሬያም ልጅ ዮሐናን የሆሻያም ልጅ ያእዛንያ ሕዝብም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ቀረቡ፥
2ነብዩንም ኤርምያስን፦ ዓይኖችህ እንዳዩን ከብዙ ጥቂት ቀርተናልና ልመናችን፥ እባክህ፥ በፊትህ ትድረስ፤ አምላክህም እግዚአብሔር የምንሄድበትን መንገድና የምናደርገውን ነገር ያሳየን ዘንድ ስለ እኛ፥ ስለዚህ ቅሬታ ሁሉ፥ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፡ አሉት።
4ነቢዩም ኤርምያስ፦ ሰምቻችኋለሁ፤ እነሆ፥ እንደ ቃላችሁ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ እግዚአብሔርም የሚመልስላችሁን ሁሉ እነግራችኋለሁ፥ ከእናንተም ምንም አልሸሽግም፡ አላቸው።
5ኤርምያስንም፦ አምላክህ እግዚአብሔር በአንተ እጅ ወደ እኛ የላከውን ነገር ሁሉ ባናደርግ፥ እግዚአብሔር በመካከላችን እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁን።
6የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል በመስማታችን መልካም እንዲሆንልን፥ መልካም ወይም ክፉ ቢሆን፥ አንተን ወደ እርሱ የምንልክህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል እንሰማለን፡ አሉት።
7ከአሥር ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ።
8የቃሬያንም ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆች ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡንም ሁሉ ጠራ፥
9እንዲህም አላቸው፦ ጸሎታችሁን በፊቱ አቀርብ ዘንድ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦
10ስላደረግሁባችሁ ክፉ ነገር ተጸጽቻለሁና በዚህች ምድር ብትቀመጡ እሠራችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም።
11ከምትፈሩት ከባቢሎን ንጉሥ አትፍሩ፤ አድናችሁ ዘንድ ከእጁም አስጥላችሁ ዘንድ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና አትፍሩ፥ ይላል እግዚአብሔር።
12እርሱ እንዲምራችሁ ወደ አገራችሁም እንዲመልሳችሁ እኔ እምራችኋለሁ።
13እናንተ ግን፦ በዚህች ምድር አንቀመጥም፡ ብትሉ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥
14እናንተም፦ አይደለም፤ ሰልፍ ወደማናይባት የመለከትም ድምፅ ወደማንሰማባት ወደማንራብባትም ወደ ግብፅ ምድር እንሄዳለን በዚያም እንቀመጣለን፡ ብትሉ፥
15እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፥ አሁን እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ግብፅ ትገቡ ዘንድ በዚያም ትቀመጡ ዘንድ ፊታችሁን ብታቀኑ፥
16የምትፈሩት ሰይፍ በዚያ በግብፅ ምድር ያገኛችኋል፥ ስለ እርሱም የምትደነግጡበት ራብ በዚያ በግብፅ ይደርስባቸኋል፥ በዚያም ትሞታላችሁ።
17ወደ ግብፅም ይገቡ ዘንድ በዚያም ይቀመጡ ዘንድ ፊታቸውን በሚያቀኑ ሰዎች ሁሉ እንዲህ ይሆንባቸዋል፤ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታሉ፤ እኔም ከማመጣባቸው ክፉ ነገር ማንም አይቀርም፥ ማንም አያመልጥም።
18የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ቍጣዬና መዓቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ላይ እንደ ፈሰሰ፥ እንዲሁ ወደ ግብፅ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ ይፈስስባችኋል፤ እናንተም ለጥላቻና ለመደነቂያ ለመረገሚያና ለመሰደቢያ ትሆናላችሁ፥ ይህንም ስፍራ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩትም።
19እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ፥ እግዚአብሔር፦ ወደ ግብፅ አትግቡ፡ ብሎ ተናግሮባችኋልና ዛሬ እንዳስጠነቀቅኋችሁ በእርግጥ እወቁ።
20እናንተ፦ ስለ እኛ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፥ አምላካችንም እግዚአብሔር የሚናገርህን ሁሉ ንገረን እኛም እናደርገዋለን፡ ብላችሁ ወደ እግዚአብሔር ወደ አምላካችሁ ልካችሁኝ ነበርና ራሳችሁን አታልላችኋል።
21እኔም ዛሬ ነግሬአችኋለሁ፥ ወደ እናንተም በላከኝ ነገር ሁሉ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁም።
22አሁንም ሄዳችሁ እንድትቀመጡ በወደዳችሁበት ስፍራ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም እንድትሞቱ በእርግጥ እወቁ።