ትንቢተ ኤርምያስ 1

AMHNIVአማርኛ19 ጥቅሶች3:27 አዳምጥ
አዳምጥ 3:27 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የኬልቅያስ ልጅ፣ ኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው፤ አባቱ በብንያም አገር በዓናቶት ከሚገኙት ካህናት አንዱ ነበረ።

2የእግዚአብሔር ቃል የይሁዳ ንጉሥ፣ የአሞን ልጅ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ወደ ኤርምያስ መጣ፤

3ደግሞም በይሁዳ ንጉሥ፣ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም ንግሠ ዘመን፤ እንዲሁም በይሁዳ ንጉሥ፣ በኢዮስያስ ልጅ በሴዴቅያስ ንግሠ ዘመን፤ እስከ ዐሥራ አንደኛው ዓመት መጨረሻ ድረስ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ተማርኮ እስከ ሄደበት እስከ አምስተኛው ወር ድረስ ወደ እርሱ ይመጣ ነበር።

4የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፤

5“በማሕፀን ሳልሠራህ ዐወቅሁህ፤ ከመወለድህ በፊት ለየሁህ፤ ለሕዝቦችም ነቢይ እንድትሆን ሾምሁህ።”

6እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዴት እንደምናገር አላውቅም፤ ገና ሕፃን ልጅ ነኝና” አልሁ።

7እግዚአብሔር ግን እንዲህ አለኝ፤ “ ‘ገና ሕፃን ልጅ ነኝ’ አትበል፤ ወደምልክህ ሁሉ ሄደህ፣ ያዘዝሁን ሁሉ ትናገራለህ፤

8እኔ አድንህ ዘንድ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራቸው” ይላል እግዚአብሔር።

9እግዚአብሔርም እጁን ዘርግቶ አፌን ዳሰሰና እንዲህ አለኝ፤ “እነሆ፤ ቃሌን በአፍህ አኑሬአለሁ፤

10እንግዲህ፣ እንድትነቅልና እንድታፈርስ፣ እንድታጠፋና እንድትገለብጥ፣ እንድታንጽና እንድትተክል በአሕዛብና በመንግሥታት ላይ ዛሬ ሾምሁህ።”

11የእግዚአብሔር ቃል፣ “ኤርምያስ ሆይ፣ ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ። እኔም፣ “የለውዝ በትር አያለሁ” አልሁ።

12እግዚአብሔርም፣ “ትክክል አይተሃል፤ ቃሌን እፈጽመው ዘንድ እተጋለሁና” አለኝ።

13ዳግመኛም የእግዚአብሔር ቃል፣ “ምን ታያለህ?” ሲል ወደ እኔ መጣ። እኔም፣ “አንድ የሚፈላ ማሰሮ አያለሁ፤ አፉም ከሰሜን ወደዚህ ያዘነበለ ነው” አልሁ።

14እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ከሰሜን በምድሪቱ በሚኖሩ ሁሉ ላይ ድንገት መዓት ይወርድባቸዋል።

15እነሆ፤ የሰሜን መንግሥታትን ሕዝቦች ሁሉ እጠራለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ንጉሦቻቸው ይመጣሉ፤ ዙፋናቸውን በኢየሩሳሌም መግቢያ በሮች፣ በቅጥሮቿ ዙሪያ ሁሉ፣ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ይዘረጋሉ።

16እኔን በመተው ክፋት ስለ ሠሩ፣ ለሌሎች አማልክት ዕጣን ስላጠኑ፣ እጆቻቸው የሠሯቸውን ስላመለኩ፣ በሕዝቤ ላይ ፍርድን ዐውጄአለሁ።

17“አንተ ግን ወገብህን ታጠቅ፤ ተነሥተህም ያዘዝሁን ሁሉ ንገራቸው፤ አትፍራቸውም፤ አለዚያ በፊታቸው አስፈራሃለሁ።

18እነሆ፤ ዛሬ በመላዪቱ ምድር ላይ አስነሣሃለሁ፤ ይኸውም የይሁዳን ነገሥታት፣ አለቆቿን፣ ካህናቷንና የምድሪቱን ሕዝብ ሁሉ መቋቋም እንድትችል የተመሸገ ከተማ፣ የብረት ምሰሶና የናስ ቅጥር አድርጌሃለሁ።

19ይዋጉሃል፤ ዳሩ ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም” ይላል እግዚአብሔር።

ማብራሪያ

1:1-10 የኤርምያስ የትንቢት አገልግሎት እና የነቢይነት ሥልጣን ቀደምት ጥሪ ተገልጿል። እርሱ ነቢይ እንዲሆን የታሰበው ለአይሁድ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች አሕዛብም ነበር። ዛሬም እርሱ ለዓለም ሁሉ ነቢይ ነው፣ እነርሱም እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች ቢያዳምጡ መልካም ይሆናል። የፈጠረን ጌታ ለእኛ ያሰበልንን ልዩ አገልግሎትና ዓላማ ያውቃል። ነገር ግን በአዲስ በሚፈጥረው መንፈሱ ቅድሳት ካላደረገልን፣ በምድር ላይ ለቅዱስ አገልግሎቱ፣ በሰማይም ለቅዱስ ደስታው ብቁ አንሆንም። ስለራሳችን ዝቅ ያለ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል። ወጣቶች ወጣትነታቸውን ሊረዱ ይገባል፣ ከችሎታቸውም በላይ አሳልፈው መሄድ የለባቸውም። ነገር ግን የራሳችንን ድክመትና አለመብቃት ስሜት ስራችንን በትህትና እንድንሰራ ቢያደርገንም፣ እግዚአብሔር ሲጠራን ወደኋላ እንድናፈገፍግ ሊያደርገን አይገባም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6