ትንቢተ ኤርምያስ 17

AMHNIVአማርኛ27 ጥቅሶች5:25 አዳምጥ
አዳምጥ 5:25 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1“የይሁዳ ኀጢአት በብረት ብርዕ፣ በሾለ የአልማዝ ጫፍ፣ ተጽፎአል፤ በልባቸው ጽላት፣ በመሠዊያቸውም ቀንዶች ላይ ተቀርጾአል።

2ልጆቻቸው እንኳ ሳይቀሩ፣ በለመለሙ ዛፎች ሥር፣ ከፍ ባሉ ኰረብቶችም ላይ ያሉትን፣ መሠዊያቸውንና አሼራ የተባለችውን ጣዖት ምስል ያስባሉ።

3በአገርህ ሁሉ ከተፈጸመው ኀጢአት የተነሣ፣ በምድሪቱ ያለህ ተራራዬ፣ ሀብትህንና ንብረትህን ሁሉ፣ መስገጃ ኰረብቶችህንም ጭምር፣ ለብዝበዛ አደርገዋለሁ።

4በገዛ ጥፋትህ፣ የሰጠሁህን ርስት ታጣለህ፤ በማታውቀውም ምድር፣ ለጠላቶችህ ባሪያ አደርግሃለሁ፤ ለዘላለም የሚነደውን፣ የቍጣዬን እሳት ጭረሃልና።”

5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሰው የሚታመን፣ በሥጋ ለባሽ የሚመካ፣ ልቡንም ከእግዚአብሔር የሚያርቅ የተረገመ ነው።

6በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፤ መልካም ነገር ሲመጣ አያይም፤ ሰው በሌለበት በጨው ምድር፣ በምድረ በዳ በደረቅ ስፍራ ይቀመጣል።

7“ነገር ግን በእግዚአብሔር የሚታመን፣ መታመኛውም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።

8በውሃ ዳር እንደ ተተከለ፣ ሥሩንም ወደ ወንዝ እንደ ሰደደ ዛፍ ነው፣ ሙቀት ሲመጣ አይፈራም፤ ቅጠሉም ዘወትር እንደለመለመ ነው፤ በድርቅ ዘመን አይሠጋም፤ ፍሬ ማፍራቱንም አያቋርጥም።”

9የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ ነው፤ ፈውስም የለውም፤ ማንስ ሊረዳው ይችላል?

10“እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፣ እንደ ሥራው ፍሬ ለመስጠት፣ ልብን እመረምራለሁ፤ የአእምሮንም ሐሳብ እፈትናለሁ።”

11ሀብትን በግፍ የሚያከማች ሰው፣ ያልፈለፈለችውን ጫጩት እንደምትታቀፍ ቆቅ ነው፤ በዕድሜው አጋማሽ ትቶት ይሄዳል፤ በመጨረሻም ሞኝነቱ ይረጋገጣል።

12የመቅደሳችን ስፍራ፣ ከጥንት ጀምሮ ከፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው።

13የእስራኤል ተስፋ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጥለውህ የሚሄዱ ሁሉ ያፍራሉ፤ ፊታቸውን ከአንተ የሚመልሱ በምድር ውስጥ ይጻፋሉ፤ የሕይወትን ውሃ ምንጭ፣ እግዚአብሔርን ትተዋልና።

14እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈውሰኝ፤ እፈወሳለሁ፤ አድነኝ እኔም እድናለሁ፤ አንተ ምስጋናዬ ነህና።

15እነርሱ ደጋግመው፣ “የእግዚአብሔር ቃል የት አለ? እስቲ አሁን ይፈጸም!” ይሉኛል።

16እረኛ ሆኜ አንተን ከማገልገል ወደ ኋላ አላልሁም፤ ክፉ ቀን እንዳልተመኘሁ ታውቃለህ፤ ከአንደበቴ የሚወጣውም በፊትህ ግልጽ ነው።

17አስደንጋጭ አትሁንብኝ፤ በመከራ ቀን መሸሸጊያዬ አንተ ነህ።

18አሳዳጆቼ ይፈሩ፤ እኔን ግን ከዕፍረት ጠብቀኝ፤ እነርሱ ይደንግጡ፤ እኔን ግን ከድንጋጤ ሰውረኝ፤ ክፉ ቀን አምጣባቸው፤ በዕጥፍ ድርብ ጥፋት አጥፋቸው።

19እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ሄደህ የይሁዳ ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ በር በሌሎቹም የኢየሩሳሌም በሮች ሁሉ ቁም፤

20እንዲህም በላቸው፤ ‘በእነዚህ በሮች የምትገቡ የይሁዳ ነገሥታት ሆይ፤ የይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳታስገቡ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።

22አባቶቻችሁን እንዳዘዝኋቸው ሰንበትን አክብሩ እንጂ በሰንበት ቀን ከየቤታችሁ ሸክም ይዛችሁ አትውጡ፤ ምንም ሥራ አትሥሩ።”

23እነርሱ ግን አልሰሙም፤ ልብም አላሉም፤ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም ዐንገታቸውን አደነደኑ።

24ነገር ግን በጥንቃቄ ብትታዘዙኝ ይላል እግዚአብሔር፤ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ይዛችሁ ባትገቡ፣ የሰንበትንም ቀን ምንም ሳትሠሩ ብትቀድሱት፣

25በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መኳንንታቸው በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ በፈረሶችና በሠረገሎች ተቀምጠው በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ታጅበው ይመጣሉ፤ ይህቺም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች።

26ሰዎች ከይሁዳ ከተሞች፣ ከኢየሩሳሌም ዙሪያ፣ ከብንያምም አገር፣ ከቈላውና ከደጋው አገር እንዲሁም ከኔጌቭ የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ ዕጣንና የምስጋና መሥዋዕት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ።

27ነገር ግን የሰንበትን ቀን ሳትቀድሱ፣ በሰንበት ቀን ሸክም ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች በመግባት ትእዛዜን ብትጥሱ፣ በኢየሩሳሌም በሮች ላይ ምሽጎቿን የሚበላ፣ የማይጠፋ እሳት እጭራለሁ።”

ማብራሪያ

፲፯፥፩-፬ ሰዎች የሚፈጽሟቸው ኃጢአቶች በአእምሯቸው ላይ ብዙም አሻራ አያሳርፉም፤ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ኃጢአት በእግዚአብሔር መጽሐፍ ተመዝግቧል፤ ሁሉም በልብ ሰሌዳ ላይ እንደዚያው ተቀርጸዋልና በሕሊናም ሁሉ ይታወሳሉ። በልብ የተቀረጸው ነገር በሕይወት ይገለጣል፤ የሰው ልጆች ተግባራት የልባቸውን ምኞትና ዓላማ ያሳያሉ። በእርሱ እይታ እጅግ በጣም ርኩስ የሆንን እኛ፣ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን ዝቅ ማድረግ ምን ያህል ያስፈልገናል! በእርሱ ምሕረትና ጸጋ እንዴት ልንደገፍ ይገባናል፤ እግዚአብሔርን እየለመንን እንዲመረምረንና እንዲፈትነን፤ በገዛ ልባችን እንድንታለል እንዳይፈቅድልን፣ ነገር ግን ንጹሕና ቅዱስ ባሕርይ በመንፈሱ በውስጣችን እንዲፈጥርልን!

17:5-11 በሰው የሚታመን፣ በምድረ በዳ እንደምትገኝ በረሀማ ቁጥቋጦ፣ ቅጠል እንደሌለው ዛፍ፣ አሳዛኝ ቁጥቋጦ፣ በባዶ መሬት የበቀለ፣ ጥቅም የለሽና ዋጋ ቢስ ይሆናል። በራሳቸው ጽድቅና ጉልበት የሚታመኑ፣ ክርስቶስን አያስፈልገንም ብለው የሚያስቡ፣ ሥጋን ክንዳቸው ያደርጋሉ፤ ነፍሶቻቸውም በጸጋዎችም ሆነ በመጽናናት ሊበለጽጉ አይችሉም። እግዚአብሔርን ተስፋቸው የሚያደርጉ ግን ቅጠሉ ፈጽሞ እንደማይደርቅ ዘወትር አረንጓዴ እንደሆነ ዛፍ ይበለጽጋሉ። በአእምሮ ሰላምና እርካታ ጸንተው ይኖራሉ፤ በድርቅ ዓመትም አይጨነቁም። እግዚአብሔርን ተስፋቸው የሚያደርጉ፣ የፍጡራን ሁሉ ማጽናኛ መጉደልን ለመሙላት በእርሱ ዘንድ በቂ አላቸው። በቅድሳትና በመልካም ሥራዎች ፍሬ መስጠታቸውን አያቆሙም።

የሰው ልብ፣ ሕሊናውም ጭምር፣ በኃጢአት በወደቀበትና በተበላሸው ሁኔታ ውስጥ ከሁሉ ነገር ይልቅ ተንኮለኛና አታላይ ነው። ክፉውን መልካም፣ መልካሙንም ክፉ ይላል፤ ሰላም የሌላቸውንም ሰላም ብሎ ይጮኻል። በዚህም ልብ እጅግ ክፉ ነው፤ ገዳይ ነው፣ ተስፋ የቆረጠ (የማይድን) ነው። የሌሎች የሰውነት ክፍሎች (ችሎታዎች) ስህተቶችን ማስተካከል የሚገባው ሕሊና በማሳሳቱ ውስጥ መሪ ከሆነ ሁኔታው በእርግጥም እጅግ የከፋ ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6