ትንቢተ ኤርምያስ 17

AMHEVGአማርኛ27 ጥቅሶች4:41 አዳምጥ
አዳምጥ 4:41 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የይሁዳ ኃጢአት በብረት ብርዕና በተሾለ ዕብነ አልማዝ ተጽፎአል፤ በልባቸው ጽላትና በመሠዊያቸው ቀንዶች ተቀርጾአል።

2ልጆቻቸውም ከለመለሙ ዛፎች በታችና በረዘሙት ኮረብቶች ላይ ያሉትን መሠዊያቸውንና የማምለኪያ ዐፀዳቸውን ያስባሉ።

3በሜዳ ያለው ተራራዬ ሆይ፥ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችህም ስለ ኃጢአት በድንበሮችህ ሁሉ ለመበዝበዝ እሰጣለሁ።

4አንተም የሰጠሁህን ርስት ትለቅቃለህ ለዘላለምም በማታውቃትም ምድር ለጠላቶቻችሁ ባሪያ አደርግሃለሁ፤ ለዘላለም የሚነድደውን እሳት በቍጣዬ አንድዳችኋልና።

5እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በሰው የሚታመን ሥጋ ለባሹንም ክንዱ የሚያደርግ፥ ልቡም ከእግዚአብሔር የሚመለስ ሰው፥ ርጉም ነው።

6በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ይሆናል፥ መልካምም በመጣ ጊዜ አያይም፤ ሰውም በሌለበት፥ ጨው ባለበት ምድር በምድረ በዳ በደርቅ ስፍራ ይቀመጣል።

7በእግዚአብሔር የታመነ እምነቱም እግዚአብሔር የሆነ ሰው ቡሩክ ነው።

8በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለ፥ በወንዝም ዳር ሥሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም፥ በድርቅ ዓመትም እንደማይሠጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።

9የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው፤ ማንስ ያውቀዋል?

10እኔ እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ እንደ መንገዱ፥ እንደ ሥራው ፍሬ እሰጥ ዘንድ ልብን እመረምራለሁ ኵላሊትንም እፈትናለሁ።

11ያልወለደችውን እንደምታቅፍ ቆቅ፥ እንዲሁ በቅን ሳይሆን ባለጠግነትን የሚሰበስብ ሰው ነው፤ በእኩሌታ ዘመኑ ይተወዋል፥ በፍጻሜውም ሰነፍ ይሆናል።

12የመቅደሳችን ስፍራ ከጥንት ጀምሮ ከፍ ያለ የክብር ዙፋን ነው።

13አቤቱ፥ የእስራኤል ተስፋ ሆይ፥ የሚተዉህ ሁሉ ያፍራሉ፤ ከአንተም የሚለዩ የሕይወትን ውኃ ምንጭ እግዚአብሔርን ትተዋልና በምድር ላይ ይጻፋሉ።

14አቤቱ፥ ፈውሰኝ እኔም እፈወሳለሁ፤ አድነኝ እኔም እድናለሁ፤ አንተ ምስጋናዬ ነህና።

15እነሆ፦ የእግዚአብሔር ቃል ወዴት አለች? አሁን ትምጣ፡ ይሉኛል።

16እኔም አንተን ተከትዬ እረኛ ከመሆን አልቸኰልሁም፥ የመከራንም ቀን አልወደድሁም፤ አንተ ታውቃለህ፤ ከከንፈሬ የወጣው በፊትህ ነበረ።

17ለማስፈራራት አትሁንብኝ፤ በመከራ ቀን አንተ መጠጊያዬ ነህ።

18አሳዳጆቼ ይፈሩ፥ እኔ ግን አልፈር፤ እነርሱ ይደንግጡ፥ እኔ ግን አልደንግጥ፤ ክፉንም ቀን አምጣባቸው፥ በሁለት እጥፍ ጥፋት አጥፋቸው።

19እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል፦ ሂድ፥ የይሁዳም ነገሥታት በሚገቡበትና በሚወጡበት በሕዝቡ ልጆች በር በኢየሩሳሌምም በሮች ሁሉ ቁም፤

20እንዲህም በላቸው፦ በእነዚህ በሮች የምትገቡ፥ እናንተ የይሁዳ ነገሥታት፥ ይሁዳም ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፥ በሰንበትም ቀን ሸክም አትሸከሙ፥ በኢየሩሳሌምም በሮች አታግቡ፥

22ከቤቶቻችሁም በሰንበት ቀን ሸክምን አታውጡ፥ ሥራንም ሁሉ አትሥሩበት፤ አባቶቻችሁንም እንዳዘዝሁ የሰንበትን ቀን ቀድሱ።

23እነርሱ ግን አልሰሙም ጆሮአቸውን አላዘነበሉም፥ እንዳይሰሙና እንዳይገሠጹም አንገታቸውን አደነደኑ።

24እኔን ፈጽሞ ብትሰሙ፤ ይላል እግዚአብሔር፥ በሰንበትም ቀን በዚህች ከተማ በሮች ሸክም ባታገቡ፥ የሰንበትንም ቀን ብትቀድሱ ሥራንም ሁሉ ባትሠሩበት፥

25በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡ ነገሥታትና መሳፍንት በሰረገሎችና በፈረሶች ላይ እየተቀመጡ በዚህች ከተማ በሮች ይገባሉ፤ እነርሱና መሳፍንቶቻቸው የይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም የሚቀመጡ ይገባሉ፥ ይህችም ከተማ ለዘላለም የሰው መኖሪያ ትሆናለች።

26የሚቃጠለው መሥዋዕትና ሌላ መሥዋዕትን የእህሉንም ቍርባን ዕጣኑንም የምስጋናውንም መሥዋዕት ይዘው ከይሁዳ ከተሞች ከኢየሩሳሌምም ዙሪያ ከብንያምም አገር ከቈላውም ከደጋውም ከደቡብም ወደ እግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ።

27ነገር ግን የሰንበትን ቀን እንድትቀድሱ፥ በሰንበትም ቀን ሸክምን ተሸክማችሁ በኢየሩሳሌም በሮች እንዳትገቡ የነገርኋችሁን ባትሰሙኝ፥ በበሮችዋ ላይ እሳትን አነድዳለሁ፥ የኢየሩሳሌምንም አዳራሾች ትበላለች፥ አትጠፋም።

ማብራሪያ

፲፯፥፩-፬ ሰዎች የሚፈጽሟቸው ኃጢአቶች በአእምሯቸው ላይ ብዙም አሻራ አያሳርፉም፤ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ኃጢአት በእግዚአብሔር መጽሐፍ ተመዝግቧል፤ ሁሉም በልብ ሰሌዳ ላይ እንደዚያው ተቀርጸዋልና በሕሊናም ሁሉ ይታወሳሉ። በልብ የተቀረጸው ነገር በሕይወት ይገለጣል፤ የሰው ልጆች ተግባራት የልባቸውን ምኞትና ዓላማ ያሳያሉ። በእርሱ እይታ እጅግ በጣም ርኩስ የሆንን እኛ፣ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን ዝቅ ማድረግ ምን ያህል ያስፈልገናል! በእርሱ ምሕረትና ጸጋ እንዴት ልንደገፍ ይገባናል፤ እግዚአብሔርን እየለመንን እንዲመረምረንና እንዲፈትነን፤ በገዛ ልባችን እንድንታለል እንዳይፈቅድልን፣ ነገር ግን ንጹሕና ቅዱስ ባሕርይ በመንፈሱ በውስጣችን እንዲፈጥርልን!

17:5-11 በሰው የሚታመን፣ በምድረ በዳ እንደምትገኝ በረሀማ ቁጥቋጦ፣ ቅጠል እንደሌለው ዛፍ፣ አሳዛኝ ቁጥቋጦ፣ በባዶ መሬት የበቀለ፣ ጥቅም የለሽና ዋጋ ቢስ ይሆናል። በራሳቸው ጽድቅና ጉልበት የሚታመኑ፣ ክርስቶስን አያስፈልገንም ብለው የሚያስቡ፣ ሥጋን ክንዳቸው ያደርጋሉ፤ ነፍሶቻቸውም በጸጋዎችም ሆነ በመጽናናት ሊበለጽጉ አይችሉም። እግዚአብሔርን ተስፋቸው የሚያደርጉ ግን ቅጠሉ ፈጽሞ እንደማይደርቅ ዘወትር አረንጓዴ እንደሆነ ዛፍ ይበለጽጋሉ። በአእምሮ ሰላምና እርካታ ጸንተው ይኖራሉ፤ በድርቅ ዓመትም አይጨነቁም። እግዚአብሔርን ተስፋቸው የሚያደርጉ፣ የፍጡራን ሁሉ ማጽናኛ መጉደልን ለመሙላት በእርሱ ዘንድ በቂ አላቸው። በቅድሳትና በመልካም ሥራዎች ፍሬ መስጠታቸውን አያቆሙም።

የሰው ልብ፣ ሕሊናውም ጭምር፣ በኃጢአት በወደቀበትና በተበላሸው ሁኔታ ውስጥ ከሁሉ ነገር ይልቅ ተንኮለኛና አታላይ ነው። ክፉውን መልካም፣ መልካሙንም ክፉ ይላል፤ ሰላም የሌላቸውንም ሰላም ብሎ ይጮኻል። በዚህም ልብ እጅግ ክፉ ነው፤ ገዳይ ነው፣ ተስፋ የቆረጠ (የማይድን) ነው። የሌሎች የሰውነት ክፍሎች (ችሎታዎች) ስህተቶችን ማስተካከል የሚገባው ሕሊና በማሳሳቱ ውስጥ መሪ ከሆነ ሁኔታው በእርግጥም እጅግ የከፋ ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6