1እግዚአብሔር፣ “ሄደህ ከተልባ እግር የተሠራ መቀነት ግዛ፤ ወገብህንም ታጠቅበት፤ ነገር ግን ውሃ አታስነካው” አለኝ።
2ስለዚህ እግዚአብሔር እንዳዘዘኝ መቀነቱን ገዛሁ፤ ወገቤንም ታጠቅሁበት።
3ለሁለተኛም ጊዜ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤
4“ገዝተህ የታጠቅህበትን መቀነት ይዘህ፣ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፤ በዚያም በዐለት ንቃቃት ውስጥ ሸሽገው።”
5ስለዚህ እግዚአብሔር በነገረኝ መሠረት ወደ ኤፍራጥስ ሄጄ ሸሸግሁት።
6ከብዙ ቀን በኋላም እግዚአብሔር፣ “ተነሥተህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፤ በዚያ እንድትሸሽገው የነገርሁህን መቀነት አምጣ” አለኝ።
7እኔም ወደ ኤፍራጥስ ሄጄ፤ መታጠቂያውን ከሸሸግሁበት ቦታ ቈፍሬ አወጣሁ፤ መታጠቂያውም ተበላሽቶ፣ ከጥቅም ውጭም ሆኖ ነበር።
8የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤
9“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የይሁዳን ትዕቢትና የኢየሩሳሌምን እብሪት እንደዚሁ አጠፋለሁ።
10ቃሌን መስማት እምቢ ብለው በልባቸው እልኸኝነት በመሄድ ሊያመልኳቸውና ሊሰግዱላቸው ሌሎችን ጣዖቶች የሚከተሉ እነዚህ ክፉ ሕዝቦች ከጥቅም ውጭ እንደሆነው እንደዚህ መቀነት ይበላሻሉ።
11መቀነት በሰው ወገብ ላይ እንደሚታሰር፣ መላው የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ከእኔ ጋር ተጣብቆ ለስሜ ምስጋናና ክብር፣ የኔ ሕዝብ እንዲሆንልኝ አድርጌው ነበር፤ ሕዝቤ ግን አልሰማም’ ይላል እግዚአብሔር።
12“እንዲህ በላቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ማድጋ ሁሉ በወይን ጠጅ ይሞላል” ይላል። እነርሱም፣ “ማድጋ ሁሉ በወይን ጠጅ እንደሚሞላ እኛ አናውቅምን?” ቢሉህ፣
13እንዲህ በላቸው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጡትን ነገሥታት፣ ካህናትን፣ ነቢያትን እንዲሁም በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሁሉ ጨምሮ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ።’ ”
14አንዱን ሰው ከሌላው ጋር፣ አባትንና ወንድ ልጅን እርስ በእርስ አጋጫለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ያለ ሐዘኔታ፣ ያለ ምሕረትና ያለ ርኅራኄ አጠፋቸዋለሁ።’ ”
15እግዚአብሔር ተናግሮአልና፣ ስሙ፤ ልብ በሉ፤ ትዕቢተኛም አትሁኑ።
16ጨለማን ሳያመጣ፣ በሚጨልሙትም ተራሮች ላይ፣ እግሮቻችሁ ሳይሰናከሉ፣ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ። ብርሃንን ተስፋ ታደርጋላችሁ፤ እርሱ ወደ ጨለማ ይለውጠዋል፤ ድቅድቅ ጨለማም ያደርገዋል።
17ባትሰሙ ግን፣ ነፍሴ ስለ ትዕቢታችሁ፣ በስውር ታለቅሳለች፤ የእግዚአብሔር መንጋ ተማርኮአልና፣ ዐይኔ አምርሮ ያለቅሳል፤ እንባዬም እንደ ጐርፍ ይወርዳል።
18ለንጉሡና ለእናቱ ለእቴጌዪቱ፣ የክብር ዘውዳችሁ፣ ከራሳችሁ ይወድቃልና፣ ከዙፋናችሁ ውረዱ” በላቸው።
19በኔጌቭ ያሉ ከተሞች ይዘጋሉ፤ የሚከፍታቸውም አይኖርም፤ ይሁዳ ሁሉ ተማርኮ ይሄዳል፤ ሙሉ በሙሉም ይዘጋል።
20ዐይኖቻችሁን ከፍታችሁ፣ ከሰሜን የሚመጡትን እዩ። ለአንቺ የተሰጠው መንጋ፣ የተመካሽባቸው በጎች የት አሉ?
21ልዩ ወዳጆች እንዲሆኑሽ ያስተማርሻቸው፣ ባለ ሥልጣን ሲሆኑብሽ ምን ትያለሽ? እንደምትወልድ ሴት፣ ምጥ አይዝሽምን?
22“ይህ ለምን ደረሰብኝ?” ብለሽ ራስሽን ብትጠይቂ፣ ልብስሽን ተገልበሽ የተገፈተርሽው፣ በሰውም እጅ የተንገላታሽው፣ ከኀጢአትሽ ብዛት የተነሣ ነው።
23ኢትዮጵያዊ መልኩን፣ ነብርስ ዝንጒርጒርነቱን መለወጥ ይችላልን? እናንት ክፉ ማድረግ የለመዳችሁትም፣ መልካም ማድረግ አትችሉም።
24“የበረሓ ነፋስ ብትንትኑን እንደሚያወጣው ገለባ፣ እንዲሁ እበታትናችኋለሁ።
25እኔን ረስተሽ፣ በከንቱ አማልክት ስለታመንሽ፣ ያወጅሁልሽ ድርሻሽ፣ ዕጣ ፈንታሽ ይህ ነው፤” ይላል እግዚአብሔር፤
26“ኀፍረትሽ እንዲገለጥ፣ ልብስሽን ፊትሽ ድረስ እገልባለሁ፤
27በኰረብቶችና በሜዳዎች ላይ፣ አስጸያፊ፣ ተግባርሽን፣ ምንዝርናሽንና ማሽካካትሽን፣ ኀፍረተቢስ ግልሙትናሽን አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ወዮልሽ፤ ከርኵሰትሽ የማትጸጂው እስከ መቼ ነው?”