ትንቢተ ኢሳይያስ 3

AMHEVGአማርኛ26 ጥቅሶች4:01 አዳምጥ
አዳምጥ 4:01 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እነሆ፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፍንና ብርታትን፥ የእንጀራን ድጋፍ ሁሉ የውኃውንም ድጋፍ ሁሉ፥

2ኃያሉንም፥ ተዋጊውንም፥ ፈራጁንም፥ ነቢዩንም፥ ምዋርተኛውንም፥

3ሽማግሌውንም፥ የአምሳ አለቃውንም፥ ከበርቴውንም፥ አማካሪውንም፥ ብልሁንም ሠራተኛ፥ አስማት አዋቂውንም ይነቅላል።

4አለቆቻቸው እንዲሆኑ ብላቴኖችን አስነሣባቸዋለሁ፥ ሕፃናቶችም ይገዙአቸዋል።

5ሕዝቡም፥ ሰው በሰው ላይ ሰውም በባልንጀራው ላይ፥ ይገፋፋል፤ ብላቴናውም በሽማግሌው ላይ የተጠቃውም በከበርቴው ላይ ይኰራል።

6ሰውም በአባቱ ቤት ውስጥ ወንድሙን ይዞ፦ አንተ ልብስ አለህ፥ አለቃም ሁንልን፥ ይህችም ባድማ ከእጅህ በታች ትሁን፡ ሲለው፥

7በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ፦ እኔ በቤቴ ውስጥ እንጀራ ወይም ልብስ የለኝምና ባለ መድኃኒት አልሆንም፤ በሕዝቡም ላይ አለቃ አታደርጉኝም፡ ይላል።

8የክብሩን ዓይን ያስቈጡ ዘንድ ምላሳቸውና ሥራቸው በእግዚአብሔር ላይ ነውና ኢየሩሳሌም ተፈታች ይሁዳም ወደቀ።

9የፊታቸውም እፍረት ይመሰክርባቸዋል፤ እንደ ሰዶምም ኃጢአታቸውን ያወራሉ፥ አይሠውሩአትም። በራሳቸው ላይ ክፉ ነገርን ሠርተዋልና ለነፍሳቸው ወዮ!

10የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና ጻድቁን፦ መልካም ይሆንልሃል፡ በሉት።

11እንደ እጁ ሥራ ፍዳው ይደረግበታልና ለበደለኛ ወዮ! ክፉም ደርሶበታል።

12ሕዝቤንስ አስገባሪዎቻቸው ይገፉአቸዋል፥ አስጨናቂዎችም ይሠለጥኑባቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፥ የመሩአችሁ ያስቱአችኋል የምትሄዱበትንም መንገድ ያጠፋሉ።

13እግዚአብሔር ለፍርድ ተነሥቶአል በሕዝቡም ላይ ሊፈርድ ቆሞአል።

14እግዚአብሔር ከሕዝቡ ሽማግሌዎችና ከአለቆቻቸው ጋር ይፋረዳል፤ የወይኑን ቦታ የጨረሳችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድሆች የበዘበዛችሁት በቤታችሁ አለ፤

15ሕዝቤንም ለምን ታደቅቁአቸዋላችሁ? የድሆችንስ ፊት ለምን ትፈጫላችሁ? ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

16ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ የጽዮን ቈነጃጅት ኰርተዋልና፥ አንገታቸውንም እያሰገጉ በዓይናቸውም እያጣቀሱ፥ ፈንጠርም እያሉ፥ በእግራቸውም እያቃጨሉ ይሄዳሉና፡

17ስለዚህ ጌታ የጽዮንን ቈነጃጅት አናት በቡሀነት ይመታል፥ እግዚአብሔርም ኀፍረተ ሥጋቸውን ይገልጣል።

18በዚያም ቀን ጌታ የእግር አልቦውን ክብር፥ መርበብንም፥ ጨረቃ የሚመስለውንም ጌጥ፥ የጆሮ እንጥልጥሉንም፥

19አንባሩንም፥ መሸፈኛውንም፥ ቀጸላውንም፥

20ሰንሰለቱንም፥ መቀነቱንም፥ የሽቱውንም ዕቃ፥

21አሸንክታቡንም፥ የእጅና የአፍንጫ ቀለበቱንም፥

22የዓመት በዓልንም ልብስ፥ መጐናጸፊያውንም፥ ልግምበገላውንም፥ ከረጢቱንም፥

23መስተዋቱንም፥ ከጥሩ በፍታ የተሰራውንም ልብስ፥ ራስ ማሰሪያውንም፥ ዓይነ ርግቡንም ያስወግዳል።

24እንዲህም ይሆናል፤ በሽቱ ፋንታ ግማት፥ በመታጠቂያውም ፋንታ ገመድ፥ ጠጕርንም በመንቀስ ፋንታ ቡሀነት፥ በመጐናጸፊያ ፋንታ ማቅ፥ በውበትም ፋንታ ጠባሳ ይሆናል።

25ጕልማሶችሽ በሰይፍ፥ ኃያላንሽም በውጊያ ይወድቃሉ።

26በሮችዋ ያዝናሉ ያለቅሱማል፤ እርስዋም ብቻዋን በምድር ላይ ትቀመጣለች።

ማብራሪያ

፫:፩-፱ እግዚአብሔር ይሁዳን ከእያንዳንዱ መደገፊያዋና ድጋፍዋ ሊያሳጣት ነበር። ከተማይቱና ምድሪቱም ባድማ ሊሆኑባት ነበር፤ ምክንያቱም ቃሎቻቸውና ሥራዎቻቸው በጌታ ላይ ያመፁ ስለነበሩ ነውና፤ በቅዱስ መቅደሱም ጭምር። ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ የማይደገፉ ከሆነ፣ እርሱም ሌሎች ድጋፎችን ሁሉ በፍጥነት ያስወግዳል፣ ከዚያም ይዘፈቃሉ። ክርስቶስ የሕይወት እንጀራና የሕይወት ውኃ ነው፤ እርሱ መደገፊያችን ከሆነ፣ የማይወሰድ መልካም ክፍል እንደሆነ እናገኛለን (ዮሐ ፮:፳፯)።

እዚህ ጋር ልብ ልንል የሚገባን፣ ፩. የኃጢአተኞች ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ነው። ፪. በኃጢአት የሚጎዳው ነፍስ መሆኑን ነው። ፫. በኃጢአተኞች ላይ የሚደርሰው ክፉ ነገር ሁሉ ምንም ቢሆን፣ እነርሱ ራሳቸው እንዳመጡት እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል።

3:10-15 ሕጉ የተረጋገጠ ነበር፤ ምንም እንኳ ብሔራዊ ብልጽግና ወይም ችግር ቢመጣም ለጻድቃን መልካም ይሆንላቸዋል፥ ለክፉዎች ግን ክፉ ይደርስባቸዋል። እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፥ ጻድቃን በእርሱ እንዲታመኑና ኃጢአተኞችም ንስሐ እንዲገቡና ወደ እርሱ እንዲመለሱ ብዙ ማበረታቻ አለ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6