1እናንት አሕዛብ ሆይ፤ ኑ አድምጡም፤ እናንተ ሰዎች ሆይ፤ አስተውሉ። ምድርና በውስጧ ያለ ሁሉ፣ ዓለምና ከእርሷ የሚበቅል ሁሉ ይስማ።
2እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ ተቈጥቶአል፤ ቍጣውም በሰራዊታቸው ሁሉ ላይ ነው፤ ፈጽሞ ያጠፋቸዋል፤ ለዕርድም አሳልፎ ይሰጣቸዋል።
3ከእነርሱም የተገደሉት ወደ ውጭ ይጣላሉ፤ ሬሳቸው ይከረፋል፤ ተራሮችም ደም በደም ይሆናሉ።
4የሰማይ ከዋክብት ሁሉ ይሟሽሻሉ፤ ሰማይ እንደ ብራና ይጠቀለላል፤ የከዋክብት ሰራዊት ሁሉ፣ ጠውልጎ እንደ ረገፈ የወይን ቅጠል፣ ደርቆም እንደ ወደቀ የበለስ ቅጠል ይሆናሉ።
5ሰይፌ በሰማያት እስኪበቃት ጠጥታለች፤ እነሆ፤ ወደ ኤዶም፣ ፈጽሞ ወዳጠፋሁት ሕዝብ ለፍርድ ወርዳለች።
6የእግዚአብሔር ሰይፍ በደም ተነክራለች፤ ሥብ ጠግባለች፤ በበግ ጠቦትና በፍየል ደም፣ በአውራም በግ ኵላሊት ሥብ ተሸፍናለች። እግዚአብሔር በባሶራ ከተማ መሥዋዕት፣ በኤዶምም ታላቅ ዕርድ አዘጋጅቶአልና።
7ጐሽ አብሮአቸው፣ ኮርማም ከወይፈን ጋር ይወድቃል፤ ምድራቸው በደም ትርሳለች፤ ዐፈራቸውም ሥብ በሥብ ይሆናል።
8እግዚአብሔር የበቀል ቀን፣ ስለ ጽዮንም የሚሟገትበት ዓመት አለውና።
9የኤዶም ምንጮች ሬንጅ፣ ዐፈሯ የሚቃጠል ድኝ፣ ምድሯም የሚንበለበል ዝፍት ይሆናል።
10እሳቷ ሌሊትና ቀን አይጠፋም፤ ጢሷም ለዘላለም ይትጐለጐላል፤ ከትውልድ እስከ ትውልድ ባድማ ትሆናለች፤ ማንም በዚያ ዳግም አያልፍም።
11ጭልፊትና ጃርት ይወርሷታል፤ ጒጒትና ቍራም ጐጆ ይሠሩባታል። እግዚአብሔር በኤዶም ላይ፣ የመፈራረሷን ገመድ፣ የመጥፊያዋንም ቱንቢ ይዘረጋል።
12መሳፍንቷም መንግሥት ተብለው ለመጠራት የሚያስችላቸው ነገር አይኖራቸውም፤ አለቆቿም በሙሉ ጥርግ ብለው ይጠፋሉ።
13በቅጥር የተመሸጉ ከተሞቿን እሾኽ፣ ምሽጎቹንም ሳማና አሜከላ ይወርሷቸዋል፤ የቀበሮዎች ጒድጓድ፣ የጒጒቶችም መኖሪያ ትሆናለች።
14የምድረ በዳ አራዊት ከጅቦች ጋር አብረው ይሆናሉ፤ በበረሓ ፍየል የሚመሰሉ አጋንንትም እርስ በእርስ ይጠራራሉ፤ የሌሊት ፍጥረታት ማረፊያቸውን በዚያ ያደርጋሉ፤ ለራሳቸውም የማረፊያ ቦታ ያገኛሉ።
15ጒጒት በዚያ ጐጆ ሠርታ ዕንቍላል ትጥላለች፤ ትቀፈቅፋለች፤ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ትታቀፋቸዋለች፤ ጭላቶችም ጥንድ ጥንድ ሆነው፣ ለርቢ በዚያ ይሰበሰባሉ።
16በእግዚአብሔር መጽሐፍ እንዲህ የሚለውን ተመልከቱ፤ አንብቡም፤ ከእነዚህ አንዱ አይጐድልም፤ እያንዳንዷም አጣማጇን አታጣም፤ ይህ ትእዛዝ ከአፉ ወጥቶአል፤ መንፈሱ በአንድ ላይ ይሰበስባቸዋልና።
17ድርሻ ድርሻቸውን ይመድብላቸዋል፤ እጁም ለክታ ታካፍላቸዋለች። ለዘላለም የእነርሱ ትሆናለች፤ ከትውልድ እስከ ትውልድም ይኖሩባታል።