ትንቢተ ኢሳይያስ 24

AMHNIVአማርኛ23 ጥቅሶች3:59 አዳምጥ
አዳምጥ 3:59 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እነሆ፤ እግዚአብሔር ምድርን ባድማ ያደርጋታል፤ ፈጽሞ ያጠፋታል፤ የፍርስራሽ ክምር ያደርጋታል፤ ነዋሪዎቿንም ይበትናል።

2ነገሩ ሁሉም አንድ ዐይነት ይሆናል፤ በሕዝቡ ላይ የሚሆነው በካህኑ፣ በአገልጋዩ ላይ የሚሆነው በጌታው፣ በአገልጋይዋ ላይ የሚሆነው በእመቤቷ፣ በገዢው ላይ የሚሆነው በሻጩ፣ በተበዳሪው ላይ የሚሆነው በአበዳሪው፣ በብድር ከፋይ ላይ የሚሆነው በብድር ሰጪው ይሆናል።

3ምድር ፈጽሞ ባድማ ትሆናለች፤ ጨርሶም ትበዘበዛለች፤ እግዚአብሔር ይህን ቃል ተናግሮአልና።

4ምድር ትደርቃለች፤ ትረግፋለች፤ ዓለም ትዝላለች፤ ትረግፋለች፤ የምድርም መሳፍንት ይዝላሉ።

5ምድር በሕዝቧ ትረክሳለች፤ ሕግን ጥሰዋል፤ ሥርዐትን ተላልፈዋል፤ ዘላለማዊውንም ኪዳን አፍርሰዋል።

6ስለዚህ ርግማን ምድርን ትበላለች፤ ሕዝቦቿም ስለ በደላቸው ይቀጣሉ፤ ስለዚህ የምድር ነዋሪዎች ተቃጥለዋል፤ በጣም ጥቂት የሆኑት ቀርተዋል።

7አዲሱ የወይን ጠጅ አለቀ፤ የወይኑም ተክል ደረቀ፤ ደስተኞችም ሁሉ አቃሰቱ።

8የከበሮ ደስታ ጸጥ አለ፤ የጨፋሪዎች ጩኸት አበቃ፤ ደስ የሚያሰኘውም በገና እረጭ አለ።

9ከእንግዲህ እየዘፈኑ የወይን ጠጅ አይጠጡም፤ መጠጡም ለሚጠጡት ይመራል።

10የፈራረሰችው ከተማ ባድማ ሆነች፤ የየቤቱም መግቢያ ተዘጋ።

11በየአደባባዩ የወይን ጠጅ ያለህ እያሉ ይጮኻሉ፤ ደስታው ሁሉ ወደ ሐዘን ይለወጣል፤ ሐሤቱም ሁሉ ከምድር ገጽ ጠፍቶአል።

12ከተማዪቱ ፈጽማ ፈርሳለች፤ በሮቿም ደቀው ወድቀዋል።

13የወይራ ዛፍ ሲመታ፣ የወይንም ዘለላ ሲቈረጥ ቃርሚያ እንደሚቀር ሁሉ፣ በምድሪቱ ላይ፣ በሕዝቦችም ላይ እንዲሁ ይሆናል።

14ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ፤ በደስታም ይጮኻሉ፤ ከምዕራብም የእግዚአብሔርን ክብር ያስተጋባሉ።

15ስለዚህ በምሥራቅ ለእግዚአብሔር ክብር ስጡ፤ ከባሕር ደሴቶችም፣ የእስራኤልን አምላክ፣ የእግዚአብሔርን ስም ከፍ ከፍ አድርጉ።

16“ለጻድቁ ክብር ይሁን” የሚል ዝማሬ፣ ከምድር ዳርቻ ሰማን፤ እኔ ግን፣ “ከሳሁ፤ መነመንሁ፤ ወዮልኝ! ከዳተኞች አሳልፈው ሰጡ፤ ከዳተኞች በክሕደታቸው አሳልፈው ሰጡ” አልሁ።

17በምድር የምትኖር ሕዝብ ሆይ፤ ሽብር፣ ጒድጓድና ወጥመድ ይጠብቁሃል።

18ከሽብር ድምፅ የሚሸሽ፣ ወደ ጒድጓድ ይገባል፤ ከጒድጓድ የወጣም፣ በወጥመድ ይያዛል። የሰማይ መስኮቶች ተከፍተዋልና፤ የምድርም መሠረት ተናወጠ።

19ምድር ተከፈለች፤ ምድር ተሰነጠቀች፤ ምድር ፈጽማ ተናወጠች።

20ምድር እንደ ሰካራም ዞረባት፤ ነፋስ እንደሚወዘውዘውም ጐጆ ሆነች፣ የዐመጿ ሸክም ከባድ ስለ ሆነ ትወድቃለች፤ እንደ ገናም አትነሣም።

21በዚያ ቀን እግዚአብሔር፣ በላይ በሰማያት ያሉትን ኀይሎች፣ በታችም በምድር ያሉትን ነገሥታት ይቀጣቸዋል።

22በጒድጓድ ውስጥ እንዳሉ እስረኞች፣ በአንድ ላይ ይታጐራሉ፤ በእስር ቤት ይዘጋባቸዋል፣ ከብዙ ቀንም በኋላ ለፍርድ ይቀርባሉ።

23የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በጽዮን ተራራና በኢየሩሳሌም፣ በሽማግሌዎቹም ፊት በክብሩ ይነግሣል፤ ጨረቃ ትሸማቀቃለች፤ ፀሓይም ታፍራለች።

ማብራሪያ

24:1-12 ሀብታቸውና ደስታቸው በምድር ላይ ብቻ የተከማቸባቸው ሁሉ ብዙም ሳይቆይ ወደ እጦትና መከራ ይወርዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ከንቱነትና በምድር ላይ ያሉትን ነገሮች ሁሉ የሚያጅበውን የመንፈስ ማቅበዝበዝ በተመለከተ የሚናገረውን ቃል ለራሳችን ማዋል መልካም ነው። ኃጢአት ምድርን ወዲህና ወዲያ አናውጧታል፤ ምድርም እግዚአብሔር በመጀመሪያ የመኖሪያ ስፍራው እንድትሆን አድርጎ ከፈጠራት ጊዜ ጀምሮ ለሰው ፈጽሞ የተለየች ሆናለች። ምድር በጣም ብትታይም እንኳ፣ በእጆቻቸው ይዘው ደስ በሚላቸውና በብብታቸው በሚያስቀምጧት ሰዎች እጅ ውስጥ እንደምትጠወልግ አበባ ናት። እየኖርንበት ያለነው ዓለም የተስፋ መቁረጥ ዓለም፣ የእንባ ሸለቆ ነው፤ በውስጡ ያሉት የሰው ልጆችም ጥቂት ቀኖች ብቻ ያላቸውና በችግር የተሞሉ ናቸው። የእግዚአብሔርን እርግማን ኃይል ተመልከቱ፤ ሁሉን እንዴት ባዶ እንደሚያደርግና ሁሉንም የኑሮ ደረጃዎችና ሁኔታዎች እንደሚያፈርስ። ኃጢአት እነዚህን መከራዎች በምድር ላይ ያመጣል፤ በሰዎች ኃጢአት ተበክላለችና፣ ስለዚህም በእግዚአብሔር ፍርዶች ትፈርስበታለች። ሥጋዊ ደስታ ብዙም ሳይቆይ ያበቃል፣ መጨረሻውም ከባድ ሐዘን ነው። እግዚአብሔር ወይንና ጠንካራ መጠጥን ለሚወዱት መራራ ለማድረግ ብዙ መንገዶች አሉት፤ የሰውነት በሽታ፣ የአእምሮ ጭንቀትና የሀብት መጥፋት ጠንካራ መጠጥን መራራ ያደርጉታል፣ የስሜትን ደስታም ጣዕም የለሽ ያደርጉታል። ሰዎች ስለ ኃጢአታቸው ማዘንን፣ በእግዚአብሔርም መደሰትን ይማሩ፤ ያኔ ምንም ሰውም ሆነ ምንም ዓይነት ክስተት ደስታቸውን ከእነርሱ ሊነጥቃቸው አይችልም።

24:13-15

ከአጠቃላይ ጥፋት የሚተርፍ ቅሬታ ይኖራል፤ ይህ ቅሬታም ታማኝና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ይሆናል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6