1ስለ ጢሮስ የተነገረ ንግር፤ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፤ ዋይ በሉ፤ ጢሮስ ተደምስሳለችና፤ ያለ ቤትና ያለ ወደብ ቀርታለች። ከቆጵሮስ ምድር፣ ዜናው ወጥቶላቸዋል።
2እናንት የባሕር ተጓዦች ያበለጠጓችሁ፣ በደሴቲቱ የምትኖሩ፣ የሲዶና ነጋዴዎችም ጸጥ በሉ።
3በታላላቅ ውሆች ላይ፣ ለጢሮስ የሺሖር እህል ይመጣላት ነበር፤ የዐባይ መከር ገቢዋ ነበር፤ እርሷም የመንግሥታቱ የንግድ መናኸሪያ ሆነች።
4አንቺ ሲዶና ሆይ፣ አንቺ የባሕር ምሽግ ሆይ፣ ዕፈሪ፤ ባሕሩ፣ “አላማጥሁም፤ አልወለድሁም፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን አላሳደግሁም” ብሎአልና።
5ከጢሮስ የሚመጣው ዜና፣ በግብፅ በሚሰማበት ጊዜ ጭንቅ ይይዛቸዋል።
6እናንት በደሴቲቱ የምትኖሩ፣ በዋይታ አልቅሱ፤ ወደ ተርሴስም ተሻገሩ፤
7እግሮቿ ሩቅ አገር የወሰዷት፣ በዚያም እንድትሰፍር ያደረጓት፣ ጥንታዊቷ የድሮ ከተማ፣ የተድላ የደስ ከተማችሁ ይህች ናትን?
8አክሊል በምታቀዳጀዋ፣ ነጋዴዎቿ መሳፍንት በሆኑ፣ በምድር የከበሩ ሻጮችና ለዋጮች በነበሯት፣ በጢሮስ ላይ ይህን ያሰበ ማን ነበር?
9የክብርን ሁሉ ትዕቢት ሊያዋርድ፣ በምድር ከፍ ከፍ ያለውንም ሁሉ ዝቅ ሊያደርግ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወስኖአል።
10የተርሴስ ልጅ ሆይ፤ ከእንግዲህ የሚከለክልሽ የለምና እንደ ዐባይ ወንዝ ምድርሽን አጥለቅልቂ።
11እግዚአብሔር እጁን በባሕር ላይ ዘረጋ፤ መንግሥታቷንም አስደነገጠ፤ የከነዓንም ምሽጎች እንዲፈርሱ፣ ትእዛዝ ሰጠ፤
12እንዲህም አለ፤ “አንቺ የተቀጠቀጥሽ የሲዶን ድንግል ሆይ! ከእንግዲህ ደስ አይበልሽ፤ “ተነሺ ወደ ቆጵሮስ ተሻገሪ፤ በዚያም እንኳ ሰላም አታገኚም።”
13እነሆ፤ የባቢሎናውያንን ምድር ተመልከቱ፤ ሕዝቡ ከንቱ ሆኖአል። አሦራውያን የምድረ በዳ አራዊት መፈንጪያ አደረጓት፤ የግንብ ማማቸውን ሠሩባት፤ ምሽጎቿን አወደሙ፤ የፍርስራሽ ክምር አደረጓት።
14እናንት የተርሴስ መርከቦች፣ ዋይ በሉ፤ ምሽጋችሁ ፈርሶአል።
15በዚያ ጊዜ ጢሮስ፣ የአንድ ንጉሥ የሕይወት ዘመን ያህል፣ ለሰባ ዓመታት ትረሳለች። ከሰባ ዓመት በኋላ ግን፣ ስለ ጋለሞታዪቱ የተዘፈነው በጢሮስ ላይ ይሆናል፤
16“አንች የተረሳሽ ጋለሞታ፤ በገና አንሺ፤ በከተማዪቱ ውስጥ ዙሪ፤ እንድትታወሽም፣ በገናሽን አሳምረሽ ምቺ፤ ብዙ ዘፈን ዝፈኚ።”
17ሰባው ዓመት ካለፈ በኋላ እግዚአብሔር ጢሮስን ይጐበኛታል፤ ወደ ቀድሞው የግልሙትና ሥራዋ ተመልሳ፣ በምድር ላይ ካሉት የዓለም መንግሥታት ሁሉ ጋር በንግዷ ትገለሙታለች።
18ያም ሆኖ ትርፏና ያገኘችው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል፤ አይከማችም፤ አይጠራቀምም። ትርፏም በእግዚአብሔር ፊት ለሚኖሩት የተትረፈረፈ ምግብና ጥሩ ልብስ ይሆናል።