ትንቢተ ሆሴዕ 13

AMHNIVአማርኛ16 ጥቅሶች3:05 አዳምጥ
አዳምጥ 3:05 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ኤፍሬም ሲናገር ሰዎች ተንቀጠቀጡ፤ በእስራኤልም የተከበረ ነበር፤ ነገር ግን በኣልን ስላመለከ በደለ፤ ሞተም።

2አሁንም ኀጢአትን መሥራት አበዙ፤ ብራቸውን አቅልጠው ለራሳቸው ጣዖት ሠሩ፣ በጥበብ የተሠሩ ምስሎችን አበጁ፤ ሁሉም የባለ እጅ ሥራ ናቸው። ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ተብሎአል፤ “ሰውን መሥዋዕት አድርገው ያቀርባሉ፤ የጥጃ ጣዖቶችንም ይስማሉ”

3ስለዚህ እንደ ማለዳ ጉም፣ ፈጥኖ እንደሚጠፋ የጧት ጤዛ፣ ከዐውድማ እንደሚጠረግ ዕብቅ፣ በመስኮትም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ።

4“እኔ ግን ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ፣ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፤ ከእኔም በቀር ሌላ አዳኝ የለም።

5በምድረ በዳ፣ በሐሩር ምድርም ተንከባከብሁህ።

6ካበላኋቸው በኋላ ጠገቡ፤ በጠገቡ ጊዜ ታበዩ፤ ከዚያም ረሱኝ።

7ስለዚህ እንደ አንበሳ እመጣባቸዋለሁ፤ እንደ ነብርም በመንገድ አደባባቸዋለሁ።

8ግልገሎቿን እንደ ተነጠቀች ድብ፣ እመታቸዋለሁ፤ እዘነታትላቸዋለሁ። እንደ አንበሳም ሰልቅጬ እውጣቸዋለሁ፤ የዱር አራዊትም ይገነጣጥላቸዋል።

9“እስራኤል ሆይ፤ በእኔ ላይ ስለ ተነሣህ፣ ረዳትህንም ስለ ተቃወምህ ትጠፋለህ።

10“ንጉሥንና አለቆችን ስጠኝ፤” ብለህ እንደ ጠየቅኸው፣ ያድንህ ዘንድ ንጉሥህ የት አለ? በከተሞችህ ሁሉ የነበሩ ገዦችህስ የት አሉ?

11በቊጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፤ በመዓቴም ሻርሁት።

12የኤፍሬም በደል ተከማችቶአል፤ ኀጢአቱም በመዝገብ ተይዞአል።

13በምጥ ላይ እንዳለች ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፤ እርሱ ግን ጥበብ የሌለው ልጅ ነው፤ የሚወለድበት ጊዜ ሲደርስ፣ ከእናቱ ማሕፀን መውጣት የማይፈልግ ሕፃን ነው።

14“ከመቃብር ኀይል እታደጋቸዋለሁ፤ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፤ መቅሠፍትህ የት አለ? መቃብር ሆይ፤ ማጥፋትህ የት አለ? “ከእንግዲህ ወዲህ አልራራለትም፤

15በወንድሞቹ መካከል ቢበለጽግም እንኳ፣ የምሥራቅ ነፋስ ከምድረ በዳ እየነፈሰ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይመጣል፤ ምንጩ ይነጥፋል፤ የውሃ ጒድጓዱም ይደርቃል። የከበረው ሀብቱ ሁሉ፣ ከግምጃ ቤቱ ይበዘበዛል።

16የሰማርያ ሰዎች በደላቸውን ይሸከማሉ፤ በአምላካቸው ላይ ዐምፀዋልና፤ በሰይፍ ይወድቃሉ፤ ሕፃኖቻቸውም በምድር ላይ ይፈጠፈጣሉ፤ የእርጉዝ ሴቶቻቸውም ሆድ ይቀደዳል።

ማብራሪያ

ምዕራፍ 13፥1-8። ኤፍሬም በእግዚአብሔር ላይ ቅዱስ ፍርሃትን ሲጠብቅና በዚያ ፍርሃት ሲያመልከው በነበረበት ጊዜ እጅግ ታላቅ ነበር። ኤፍሬም እግዚአብሔርን በተወና ጣዖት አምልኮን በተከተለ ጊዜ ግን ወደቀ። የሚሠዉ ሰዎች ጥጆችን እንደሚያመልኩ፣ እንደሚወዱና እንደሚታዘዙ ምልክት አድርገው ይስሙአቸው፤ ነገር ግን ጌታ ክብሩን ለሌላ አይሰጥምና ምስሎችን የሚያመልኩ ሁሉ ያፍራሉ። ጽኑና ዘላቂ የሆነ መጽናኛ በእግዚአብሔር ብቻ እንጂ በሌላ ቦታ አይገኝም። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ብቻ ሳይሆን መልካም ምድር በሆነችው በከነዓንም አስገባቸው፤ ነገር ግን ዓለማዊ ብልጽግና የሰዎችን ትዕቢት ሲያባብስ እግዚአብሔርን እንዲረሱ ያደርጋቸዋል። ስለዚህም ጌታ በጽድቅ ቁጣ እንደ ደኖቻቸው አስፈሪ አውሬዎች ይገናኛቸዋል። የተናቀው ቸርነት ደግሞ ታላቅ ቁጣን ያስከትላል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6