ትንቢተ ሆሴዕ 13

AMHEVGአማርኛ16 ጥቅሶች2:36 አዳምጥ
አዳምጥ 2:36 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ኤፍሬም በተናገረ ጊዜ ፍርሃት ነበረ፥ በእስራኤልም ዘንድ ታበየ፤ ነገር ግን በኣልን በማምለክ በበደለ ጊዜ ሞተ።

2አሁንም ኃጢአትን ይሠሩ ዘንድ ጨመሩ፤ በብራቸውም ለራሳቸው ቀልጦ የተሠራ ምስልን፥ እንደ ጥበባቸውም ጣዖታትን ሠርተዋል፤ ሁሉም የሠራተኛ ሥራ ናቸው። ስለ እነርሱም፦ “የሚሠዉ ሰዎች እምቦሳውን ይሳሙ፡” ይላሉ።

3ስለዚህም እንደ ማለዳ ደመና፥ በጥዋትም እንደሚያልፍ ጠል፥ በዐውሎ ነፍስም ከአውድማ እንደሚበተን እብቅ፥ ከመስኮትም እንደሚወጣ ጢስ ይሆናሉ።

4እኔ ግን ከግብፅ ምድር ጀምሬ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ አምላክ አታውቅም፥ ከእኔም በቀር ሌላ መድኃኒት የለም።

5በምድረ በዳ፥ እጅግ በደረቀ ምድር አውቄህ ነበር።

6ከተሰማሩ በኋላ ጠገቡ፥ በጠገቡም ጊዜ ልባቸው ታበየ፤ ስለዚህ ረሱኝ።

7ስለዚህም እኔ እንደ አንበሳ ሆንሁባቸው፥ እንደ ነብርም በመንገድ አጠገብ አደባባቸዋለሁ፤

8ልጅዋ እንደ ተነጠቀባት ድብ እገጥማቸዋለሁ፥ የልባቸውንም ስብ እቀድዳለሁ፤ በዚያም እንደ አንበሳ እበላቸዋለሁ፥ የምድረ በዳም አውሬ ይነጣጠቃቸዋል።

9እስራኤል ሆይ፥ በእኔ በረዳትህ ላይ በመነሣትህ ጥፋትህ ነው።

10በየከተማህ ሁሉ ያድንህ ዘንድ ንጉሥህ ወዴት አለ? ስለ እነርሱም፦ “ንጉሥንና አለቆችን ስጠኝ፡” ብለህ የተናገርኸው መሳፍንቶችህ ወዴት አሉ?

11በቍጣዬ ንጉሥን ሰጠሁህ፥ በመዓቴም ሻርሁት።

12የኤፍሬም በደል ታስሮአል፥ ኃጢአቱም ተከማችቶአል።

13ምጥ እንደ ያዛት ሴት ጭንቅ ይመጣበታል፤ በሚወለድበት ጊዜ በማኅፀን አፍ ቀጥ ብሎ አይወጣምና አእምሮ የሌለው ልጅ ነው።

14ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፥ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤ ሞት ሆይ፥ ቸነፈርህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ፥ ማጥፋትህ ወዴት አለ? ርኅራኄ ከዓይኔ ተሰወረች።

15በወንድሞቹ መካከል ፍሬያማ ቢሆን የምሥራቅ ነፋስ ይመጣል፥ የእግዚአብሔር ነፋስ ከምድረ በዳ ይመጣል፤ ምንጩንም ያደርቃል፥ ፈሳሹንም ያጠፋል፥ የተከበሩ ዕቃዎች ሁሉ ያሉበትን መዝገብ ይበዘብዛል።

16ሰማርያ በአምላክዋ ላይ ዐምፃለችና በደልዋን ትሸከማለች፤ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ሕፃኖቻቸውም ይፈጠፈጣሉ፥ እርጕዞቻቸውም ይቀደዳሉ።

ማብራሪያ

ምዕራፍ 13፥1-8። ኤፍሬም በእግዚአብሔር ላይ ቅዱስ ፍርሃትን ሲጠብቅና በዚያ ፍርሃት ሲያመልከው በነበረበት ጊዜ እጅግ ታላቅ ነበር። ኤፍሬም እግዚአብሔርን በተወና ጣዖት አምልኮን በተከተለ ጊዜ ግን ወደቀ። የሚሠዉ ሰዎች ጥጆችን እንደሚያመልኩ፣ እንደሚወዱና እንደሚታዘዙ ምልክት አድርገው ይስሙአቸው፤ ነገር ግን ጌታ ክብሩን ለሌላ አይሰጥምና ምስሎችን የሚያመልኩ ሁሉ ያፍራሉ። ጽኑና ዘላቂ የሆነ መጽናኛ በእግዚአብሔር ብቻ እንጂ በሌላ ቦታ አይገኝም። እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ብቻ ሳይሆን መልካም ምድር በሆነችው በከነዓንም አስገባቸው፤ ነገር ግን ዓለማዊ ብልጽግና የሰዎችን ትዕቢት ሲያባብስ እግዚአብሔርን እንዲረሱ ያደርጋቸዋል። ስለዚህም ጌታ በጽድቅ ቁጣ እንደ ደኖቻቸው አስፈሪ አውሬዎች ይገናኛቸዋል። የተናቀው ቸርነት ደግሞ ታላቅ ቁጣን ያስከትላል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6