1በሰባተኛው ወር፣ በሃያ አንደኛ ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤
2“ለይሁዳ ገዥ ለሰላትያል ልጅ ለዘሩባቤል፣ ለሊቀ ካህናቱ ለኢዮሴዴቅ ልጅ ለኢያሱ፣ ከምርኮ ለተረፈውም ሕዝብ እንዲህ ብለህ ተናገር፤ እንዲህም ብለህ ጠይቃቸው፤
3‘ይህን ቤት በቀድሞ ክብሩ ሳለ ያየ ከመካከላችሁ ማን አለ? አሁንስ ምን መስሎ ይታያችኋል? ይህ በፊታችሁ ምንም እንዳይደለ የሚቈጠር አይደለምን?
4እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል ‘አሁን ግን ዘሩባቤል ሆይ፤ በርታ፤ የሊቀ ካህናቱ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ሆይ፤ በርታ፤ እናንተም የምድሪቱ ሕዝብ ሁሉ በርቱ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና ሥሩ’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር፤
5‘ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ የገባ ሁላችሁ ቃል ይህ ነው፤ መንፈሴም በመካከላችሁ ይሆናልና አትፍሩ።’
6“ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘በቅርብ ጊዜ እንደ ገና ሰማያትንና ምድርን፣ ባሕሩንና የብሱን አንድ ጊዜ አናውጣለሁ።
7ሕዝቦችን ሁሉ አናውጣለሁ፤ የሕዝቦችም ሀብት ሁሉ ወደዚህ ይመጣል፤ ይህንም ቤት በክብር እሞላዋለሁ’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር።
8‘ብሩ የእኔ ነው፤ ወርቁም የእኔ ነው’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ጸባኦት፤
9‘የዚህ የአሁኑ ቤት ክብር ከቀድሞው ቤት ክብር ይበልጣል’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ጸባኦት፤ ‘በዚህም ቦታ ሰላምን እሰጣለሁ’ ይላል ሁሉን የሚገዛ እግዚአብሔር ጸባኦት።”
10ዳርዮስ በነገሠ በሁለተኛው ዓመት፣ በዘጠነኛው ወር፣ በሃያ አራተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤
11“እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘ሕጉምን እንደሚል ካህናቱን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፤
12አንድ ሰው የተቀደሰውን ሥጋ በልብሱ ዕጥፋት ቢይዝ፣ ያም ዕጥፋት እንጀራ ወይም ወጥ፣ የወይን ጠጅ ወይም ዘይት ወይም ሌላ ምግብ ቢነካ የተቀደሰ ይሆናልን?” ካህናቱም፣ “የተቀደሰ አይሆንም” ብለው መለሱ።
13ሐጌም፣ “ሬሳ በመንካቱ የረከሰ ሰው፣ ከእነዚህ አንዱን ቢነካ፣ የተነካው ነገር ይረክሳልን?” ሲል ጠየቀ። ካህናቱም፣ “አዎን፣ ይረክሳል” ሲሉ መለሱ።
14ከዚያም ሐጌ እንዲህ አለ፤ “ ‘ይህ ሕዝብና ይህ ወገንም በፊቴ እንደዚሁ ነው’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘የእጃቸው ሥራና የሚያቀርቡት ሁሉ የረከሰ ነው’።
15“ ‘እንግዲህ ከዛሬ ጀምራችሁ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ከመነባበሩ በፊት የነበረውን ሁኔታ አስተውሉ።
16አንድ ሰው ሃያ መስፈሪያ ወደ ሚሆን የእህል ክምር በመጣ ጊዜ ዐሥር ብቻ አገኘ፤ አምሳ ማድጋ የወይን ጠጅ ለመቅዳት ወደ መጭመቂያው በሄደ ጊዜ ሃያ ብቻ አገኘ፤
17የእጃችሁን ሥራ ሁሉ በዋግ፣ በአረማሞና በበረዶ መታሁት፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም’ ይላል እግዚአብሔር፤
18‘ከዚህ ቀን ጀምሮ፣ ይኸውም ከዘጠነኛው ወር ሃያ አራተኛ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት እስከ ተጣለበት ቀን ድረስ ያለውን ዘመን አስተውሉ፤ ልብ ብላችሁም አስቡ፤
19በጐተራ የቀረ ዘር አሁንም ይገኛልን? የወይኑና የበለሱ ዛፍ፣ የሮማኑና የወይራው ዛፍ እስካሁን አላፈሩም። “ ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ እባርካችኋለሁ።’ ”
20በወሩ ሃያ አራተኛ ቀን የእግዚአብሔር ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ ሐጌ መጣ፤
21“ለይሁዳ ገዥ ለዘሩባቤል ሰማያትንና ምድርን እንደማናውጥ ንገረው፤
22የመንግሥታትን ዙፋን እገለብጣለሁ፤ የባዕዳንን መንግሥታት ኀይል አጠፋለሁ፤ ሠረገሎችንና ሠረገለኞችን እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችና ጋላቢዎቻቸውም በገዛ ወንድሞቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ።
23“ ‘እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘በዚያን ቀን ባሪያዬ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል ሆይ፤ እኔ እወስድሃለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እንደ ማተሚያ ቀለበቴ አደርግሃለሁ፤ እኔ መርጬአለሁና’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።”