1በመጠበቂያ ላይ እቆማለሁ፤ በምሽጒ ቅጥር ላይ ወጥቼ እቈያለሁ፤ ምን እንደሚለኝ፣ ለክርክሩም የምሰጠውን መልስ ለማወቅ እጠባበቃለሁ።
2እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “በቀላሉ እንዲነበብ፣ ራእዩን ጻፈው፤ በሰሌዳም ላይ ቅረጸው።
3ራእዩ የተወሰነለትን ጊዜ ይጠብቃልና፤ ስለ መጨረሻውም ይናገራል፤ እርሱም አይዋሽም፤ የሚዘገይ ቢመስልም ጠብቀው፤ በርግጥ ይመጣል፤ ከቶም አይዘገይም።
4“እነሆ፤ እርሱ ታብዮአል፤ ምኞቱ ቀና አይደለም፤ ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል።
5በእርግጥ የወይን ጠጅ አታሎታል፤ ትዕቢተኛ ነው፤ ከቶ አያርፍም፤ እንደ ሲኦል ስስታም ነው፣ እንደ ሞት ከቶ አይጠግብም፤ ሕዝቦችን ለራሱ ይሰበስባል፤ ሰዎችንም ሁሉ ማርኮ ይወስዳል።
6“ታዲያ በእንደዚህ ዐይነቱ ሰው ላይ በማፌዝና በመዘበት እንዲህ እያሉ ሁሉም አይሣለቁበትምን? “የተሰረቀውን ሸቀጥ ለራሱ ለሚያከማች፣ ራሱን በዐመፅ ባለጠጋ ለሚያደርግ ወዮለት! ይህ የሚቀጥለውስ እስከ መቼ ነው?”
7ባለዕዳ ያደረግሃቸው ድንገት አይነሡብህምን? ነቅተውስ አያስደነግጡህምን? በእጃቸውም ትወድቃለህ።
8አንተ ብዙ ሕዝብ ስለ ዘረፍህ፣ የተረፉት ሕዝቦች ይዘርፉሃል፤ የሰው ደም አፍሰሃልና፤ አገሮችንና ከተሞችን፣ በውስጣቸው የሚኖሩትን ሁሉ አጥፍተሃል።
9“በተጭበረበረ ትርፍ መኖሪያውን ለሚገነባ፣ ከጠላት እጅ ለማምለጥ፣ ቤቱን በከፍታ ላይ ለሚሠራ ወዮለት!
10የብዙ ሰዎች ነፍስ እንዲጠፋ አሢረሃል፤ በገዛ ቤትህ ላይ ውርደትን፣ በራስህም ላይ ጥፋትን አምጥተሃል።
11ድንጋይ ከቅጥሩ ውስጥ ይጮኻል፤ ከዕንጨት የተሠሩ ተሸካሚዎችም ይመልሱለታል።
12“ከተማን ደም በማፍሰስ ለሚሠራ፣ በወንጀልም ለሚመሠርታት ወዮለት።
13ሰዎች ለእሳት ማገዶ እንዲሆን እንዲለፉ፣ ሕዝቦችም በከንቱ እንዲደክሙ፣ እግዚአብሔር ጸባኦት ወስኖ የለምን?
14ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን ሁሉ፣ ምድርም የእግዚአብሔርን ክብር በማወቅ ትሞላለችና።
15“ኀፍረተ ሥጋቸውን ለማየት፤ ባልንጀሮቹን ለሚያጠጣ፣ እስኪሰክሩም ድረስ ወይን ለሚቀዳላቸው ወዮለት!
16በክብር ፈንታ ዕፍረት ትሞላለህ፤ አሁን ደግሞ ተራው የአንተ ነውና፤ ጠጣ፤ ኀፍረተ ሥጋህም ይገለጥ፤ በእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ያለው ጽዋ ይመለስብሃል፤ ክብርህንም ውርደት ይሸፍነዋል።
17በሊባኖስ ላይ የሠራኸው ግፍ ያጥለቀልቅሃል፤ እንስሳቱን ማጥፋትህም ያስደነግጥሃል፤ የሰው ደም አፍሰሃልና፤ አገሮችንና ከተሞችን በውስጣቸው የሚኖሩትንም ሁሉ አጥፍተሃልና።
18“የሰው እጅ የቀረጸው ጣዖት፣ ሐሰትንም የሚናገር ምስል ምን ፋይዳ አለው? ሠሪው በገዛ እጁ ሥራ ይታመናልና፣ መናገር የማይችሉ ጣዖታትን ይሠራልና።
19ዕንጨቱን፣ ‘ንቃ!’ ሕይወት የሌለውንም ድንጋይ፣ ‘ተነሣ!’ ለሚል ወዮለት፤ በውኑ ማስተማር ይችላልን? እነሆ፤ በወርቅና በብር ተለብጦአል፤ እስትንፋስም የለውም።
20እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፣ ምድር ሁሉ በፊቱ ጸጥ ትበል።