ትንቢተ ሕዝቅኤል 6

AMHNIVአማርኛ14 ጥቅሶች3:34 አዳምጥ
አዳምጥ 3:34 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2“የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ እስራኤል ተራሮች አዙር፤ ትንቢትም ተናገርባቸው፤

3እንዲህም በል፤ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የጌታ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኰረብቶች፤ ለገደላገደሎችና ለሸለቆች እንዲህ ይላል፤ “ሰይፍን አመጣባችኋለሁ፤ የማምለኪያ ኰረብቶቻችሁን አጠፋለሁ።

4መሠዊያዎቻችሁ ይፈርሳሉ፤ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁም ይሰባበራሉ፤ የታረዱ ሰዎቻችሁን በጣዖቶቻችሁ ፊት እጥላለሁ።

5የእስራኤላውያንን ሬሳ በጣዖቶቻችሁ ፊት አጋድማለሁ፤ ዐጥንቶቻችሁንም በመሠዊያዎቻችሁ ዙሪያ እበትናለሁ።

6መሠዊያዎቻችሁ እንዲፈራርሱና እንዲወድሙ፣ ጣዖቶቻችሁ እንዲሰባበሩና እንዲደቁ፣ የዕጣን መሠዊያዎቻችሁ እንዲንኰታኰቱ፣ የእጆቻችሁም ሥራ እንዲደመሰስ፣ የምትኖሩባቸው ከተሞች ሁሉ ባድማ ይሆናሉ፤ ማምለኪያ ኰረብቶችም እንዳልነበሩ ይሆናሉ።

7የታረዱ ሰዎቻችሁ በመካከላችሁ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

8“በአሕዛብ መካከል ስትበተኑ፣ አንዳንዶቻችሁ ከሰይፍ ታመልጣላችሁና፣ ጥቂት ሰዎችን አስቀራለሁ።

9እነዚህ ከሰይፍ የተረፉት፣ ከእኔ ዘወር ባለ አመንዝራ ልባቸውና ጣዖትን በተከተለ አመንዝራ ዐይናቸው የቱን ያህል እንዳሳዘኑኝ፤ በአሕዛብ ምድር ሆነው ያስታውሱኛል፤ ካደረጉት ክፋትና ከፈጸሙት ርኩስ ተግባር ሁሉ የተነሣም ራሳቸውን ይጸየፋሉ።

10እነርሱም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ፤ ይህንም ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁ ብዬ የተናገርሁት በከንቱ አይደለም።

11“ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የእስራኤል ቤት ካደረጉት ክፋትና ከፈጸሙት ጸያፍ ተግባራቸው ሁሉ የተነሣ በሰይፍ በራብና በቸነፈር ይወድቃሉና፤ በእጅህ እያጨበጨብህ በእግርህም መሬት እየረገጥህ፣ ‘ወየው!’ ብለህ ጩኽ።

12በሩቅ ያለው በቸነፈር ይሞታል፤ በቅርብ ያለው በሰይፍ ይወድቃል፤ በሕይወት የተረፈውና የዳነው በራብ ያልቃል። መዓቴንም በዚህ ዐይነት ሁኔታ በእነርሱ ላይ እፈጽማለሁ።

13የታረዱት ሰዎቻቸው በመሠዊያው ዙሪያ በጣዖቶቻቸው መካከል፣ ከፍ ባሉ ኰረብቶች ሁሉና በተራሮች ዐናት ሁሉ ላይ፣ በለመለመ ዛፍ ሁሉና ቅጠሉ በበዛ ወርካ ሁሉ ሥር፣ በአጠቃላይ ለጣዖቶቻቸው ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን ባቀረቡበት ስፍራ ሁሉ ተጥለው ሲታዩ፣ ያን ጊዜ እኔ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

14እጄን በእነርሱ ላይ አነሣለሁ፤ የሚኖሩበትንም ስፍራ ከምድረ በዳው እስከ ዴብላታ ድረስ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፤ ያን ጊዜም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።”

ማብራሪያ

6:1-7. ጦርነት ሰዎችን፣ ቦታዎችንና እጅግ ቅዱስ እንደሆኑ የሚታሰቡትን ነገሮች ባድማ ያደርጋል። እግዚአብሔር ጣዖት አምልኮዎችን በጣዖት አምላኪዎች እጅ እንኳ ያጠፋል። እኛ ጣዖት የምናደርገውን ነገር ባድማ እንዲሆን ማድረጉ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍትሐዊ ነው። ብዙዎች ለደኅንነት የሚታመኑባቸው አጉል እምነቶች ብዙ ጊዜ ጥፋታቸውንም ያመጣሉ። ቀኑም ቀርቧል፤ ያን ጊዜም ጣዖታትና ጣዖት አምልኮ በአይሁድ ዘንድ ሙሉ በሙሉ እንደጠፉት ሁሉ፣ በስም ክርስቲያን ነን ከሚለው ቤተ ክርስቲያን ጭምር ሙሉ በሙሉ ይወድማሉ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6