1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦
2የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዋይ! በሉ፥ ለቀኑ ወዮ!
3ቀኑ ቅርብ ነው፥ የእግዚአብሔር ቀን ቅርብ ነው፥ የደመና ቀን፥ የአሕዛብ ጊዜ ይሆናል።
4ሰይፍ በግብፅ ላይ ይመጣል፥ ሁከትም በኢትዮጵያ ይሆናል፤ የተገደሉትም በግብፅ ውስጥ ይወድቃሉ፥ ብዛትዋንም ይወስዳሉ፥ መሠረትዋም ይፈርሳል።
5ኢትዮጵያና ፉጥ ሉድም የተደባለቀም ሕዝብ ሁሉ ኩብም ቃል ኪዳንም የገባችው ምድር ልጆች ከእነርሱ ጋር በሰይፍ ይወድቃሉ።
6እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ግብፅን የሚደግፉ ይወድቃሉ፥ የኃይልዋም ትዕቢት ይወርዳል፤ ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሴዌኔ ድረስ በእርስዋ ውስጥ በሰይፍ ይወድቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
7ባድማም በሆኑ አገሮች መካከል ባድማ ይሆናሉ፥ ከተሞችዋም በፈረሱ ከተሞች መካከል ይሆናሉ።
8እሳትንም በግብፅ ባነደድሁ ጊዜ ረዳቶችዋም ሁሉ በተሰበሩ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
9በዚያ ቀን መልእክተኞች ተዘልለው የሚኖሩትን ኢትዮጵያውያንን ለማስፈራት ከፊቴ በመርከብ ይወጣሉ፤ እንደ ግብፅም ቀን ሁከት ይሆንባቸዋል፤ እነሆ፥ ይመጣልና።
10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የግብፅን ብዛት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ እሽራለሁ።
11እርሱና የአሕዛብ ጨካኞች ሕዝቡ ምድሪቱን ለማጥፋት ይመጣሉ፤ ሰይፋቸውንም በግብፅ ላይ ይመዝዛሉ ምድሪቱንም በተገደሉት ይሞላሉ።
12ወንዞችንም ምድረ በዳ አደርጋለሁ ምድሪቱንም በክፉ ሰዎች እጅ እሸጣለሁ፥ ምድሪቱንና ሙላዋንም በእንግዶች እጅ ባድማ አደርጋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬያለሁ።
13ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣዖቶቹን አጠፋለሁ፥ ምስሎችንም ከሜምፎስ እሽራለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ በግብፅ ምድር አለቃ አይሆንም፥ በግብፅም ምድር ላይ ፍርሃትን አደርጋለሁ።
14ጳትሮስንም አፈርሳለሁ፥ በጣኔዎስም እሳትን አነድዳለሁ፥ በኖእ ላይም ፍርድን አደርጋለሁ።
15በግብፅም ምሽግ በሲን ላይ መዓቴን አፈስሳለሁ፥ የኖእንም ብዛት አጠፋለሁ።
16በግብፅም እሳትን አነድዳለሁ፥ ሲንም ትጨነቃለች ኖእም ትሰበራለች፥ በሜምፎስም በየቀኑ ጠላቶች ይሆኑባታል።
17የሄልዮቱ ከተማና የቡባስቱም ጕልማሶች በሰይፍ ይወድቃሉ ሴቶችም ይማረካሉ።
18የግብፅን ቀንበር በዚያ በሰበርሁ ጊዜ በጣፍናስ ቀኑ ይጨልማል የኃይልዋም ትዕቢት ይጠፋባታል፤ ደመናም ይጋርዳታል፥ ሴቶች ልጆችዋም ይማረካሉ።
19እንዲሁ በግብፅ ላይ ፍርድን አደርጋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
20እንዲህም ሆነ፤ በአሥራ አንደኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በሰባተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦
21የሰው ልጅ ሆይ፥ የግብፅን ንጉሥ የፈርዖንን ክንድ ሰብሬያለሁ፤ እነሆም፥ በጨርቅ በመጠቅለል ይፈወስ ዘንድ ሰይፉንም ለመያዝ እንዲበረታ አልታሰረም።
22ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ እኔ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ላይ ነኝ፥ የጸናችውንና የተሰበረችውንም ክንዱን እሰብራለሁ፥ ሰይፉንም ከእጁ አስረግፈዋለሁ።
23ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ።
24የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አበረታለሁ ሰይፌንም በእጁ እሰጣለሁ፤ የፈርዖንን ክንድ ግን እሰብራለሁ፥ ተወግቶም በሚሞተው እንጕርጕሮ በፊቱ ያንጐራጕራል።
25የባቢሎንንም ንጉሥ ክንድ አጸናለሁ የፈርዖንም ክንድ ይወድቃል፤ ሰይፌንም በባቢሎን ንጉሥ እጅ በሰጠሁ ጊዜ እርሱም በግብፅ ምድር ላይ በዘረጋው ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
26ግብጻውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናለሁ ወደ አገሮችም እዘራቸዋለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።