ትንቢተ ሕዝቅኤል 2

AMHNIVአማርኛ10 ጥቅሶች1:50 አዳምጥ
አዳምጥ 1:50 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ተነሥተህ በእግርህ ቁም፤ እኔም እናገርሃለሁ” አለኝ።

2እርሱም ሲናገር፣ መንፈስ ወደ ውስጤ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤ ሲናገረኝም ሰማሁት።

3እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእኔ ላይ ወደ ዐመፀው ወደ ዐመፀኛው የእስራኤል ሕዝብ እልክሃለሁ፤ እነርሱና አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ ዐምፀውብኛል።

4ሕዝቡም እልኸኛና ዐንገተ ደንዳና ነው፤ እኔ ወደ እነርሱ እልክሃለሁ፤ አንተም ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ በላቸው።

5እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ስለሆኑ፤ ቢሰሙም ባይሰሙም በመካከላቸው ነቢይ እንደነበር ያውቃሉ።

6አንተ የሰው ልጅ ሆይ፤ እነርሱን ወይም ቃላቸውን አትፍራ፤ ኵርንችትና እሾኽ በዙሪያህ ቢኖሩም፣ በጊንጦች መካከል ብትቀመጥም አትፍራ። እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም፣ አንተ በሚሉህ ነገር አትፍራ፤ እነርሱም አያስደንግጡህ።

7እነርሱ ዐመፀኛ ቤት ስለሆኑ፣ ቢሰሙም ባይሰሙም አንተ ቃሌን ንገራቸው።

8አንተ ግን የሰው ልጅ ሆይ፤ እኔ የምልህን ስማ፤ እንደዚያ ዐመፀኛ ቤት ዐታምፅ፤ አፍህን ክፈት፤ የምሰጥህንም ብላ።”

9ከዚህም በኋላ፣ እነሆ አንድ እጅ ወደ እኔ ተዘርግቶ አየሁ፤ ጥቅልል መጽሐፍም ነበረበት፤

10እርሱም በፊቴ ዘረጋው፤ መጽሐፉም ከፊትና ከኋላው የሰቈቃ፣ የልቅሶና የዋይታ ቃላት ተጽፎበት ነበር።

ማብራሪያ

2:1-5 ዕዝቅኤል በብዙዎቹ ራዕዮች እንዳይታበይ፣ አሁንም የሰው ልጅ፣ ደካማና ሟች ፍጡር መሆኑ ይታሰብለት ነበር። ክርስቶስ ራሱን የሰው ልጅ ብሎ ይጠራ እንደነበር ሁሉ፣ ይህ ደግሞ የተከበረ መለያ ነበር። የዕዝቅኤል አኳኋን አክብሮትን ያሳየ ነበር፤ ነገር ግን መቆሙ ለሥራው የላቀ ዝግጁነትንና ብቃትን ያመለክት ነበር። እግዚአብሔር የሚያዘንበትን ለማድረግ ዝግጁ ሆነን ስንቆም ይናገረናል። ዕዝቅኤል የራሱ ብርታት ስላልነበረው፣ መንፈሱ ወደ እርሱ ገባ። እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን ሁሉ በእኛ ውስጥ ለመሥራት በጸጋው ደስ ይለዋል። መንፈስ ቅዱስ ፈቃዳችንን ወደ ግዴታችን በማዘንበል በእግራችን እንድንቆም ያደርገናል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6