መጽሐፈ መክብብ 2

AMHEVGአማርኛ26 ጥቅሶች4:40 አዳምጥ
አዳምጥ 4:40 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እኔ በልቤ፦ “ና በደስታም እፈትንሃለሁ፥ መልካምንም ቅመስ፡” አልሁ፤ ይህም ደግሞ እነሆ ከንቱ ነበረ።

2ሳቅን፦ “ዕብድ ነህ፤” ደስታንም፦ “ምን ታደርጋለህ?” አልሁት።

3የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች ሊሠሩት መልካም ነገር ምን እንደ ሆነ እስካይ ድረስ ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት ስንፍናንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ።

4ትልቅ ሥራን ሠራሁ፥ ቤቶችንም አደረግሁ፥ ወይንም ተከልሁ፤

5አትክልትንና ገነትን አደረግሁ፥ ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው፤

6በዱር የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያ አደረግሁ።

7ወንዶችንና ሴቶችን ባሪያዎች ገዛሁ፥ የቤት ውልድ ባሪያዎችም ነበሩኝ፤ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ ከብቶችና መንጋዎች ነበሩኝ።

8ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ፤ አዝማሪዎችንና አርሆዎችን የሰዎች ልጆችንም ተድላ እጅግ የበዙ ሴቶችንም አከማቸሁ።

9ታላቅም ሆንሁ፥ ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፤ ደግምም ጥበቤ ከእኔ ጋር ጸንታ ቀረች።

10ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፤ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ።

11እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም።

12እኔም ጥበብን ዕብደትንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ፤ በፊት ከተደረገው በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል?

13እኔም ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ጥበብ ከስንፍና እንዲበልጥ አየሁ።

14የጠቢብ ዓይኖች በራሱ ላይ ናቸው፥ ሰነፍ ግን በጨለማ ይሄዳል፤ ደግሞ ለሁለቱ መጨረሻቸው አንድ እንደ ሆነ አስተዋልሁ።

15እኔም በልቤ፦ “ለሰነፍ የሚደርሰው ለእኔም ይደርሳል፤ ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ?” አልሁ። የዚያን ጊዜም በልቤ፦ “ይህ ደግሞ ከንቱ ነው፡” አልሁ።

16በሚመጣው ዘመን ነገር ሁሉ የተረሳ ይሆናልና ለዘላለም የሚሆን የጠቢብና የሰነፍ መታሰቢያ አይገኝም። አዬ ጉድ! ጠቢብ ከሰነፍ ጋር እንዴት ይሞታል!

17ከፀሐይም በታች የተሠራው ሥራ ሁሉ ከብዶብኛልና ሕይወትን ጠላሁ፤ ሁሉም ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።

18ከእኔ በኋላ ለሚመጣው ሰው እተወዋለሁና ከፀሐይ በታች የደከምሁበትን ሁሉ ጠላሁት።

19ጠቢብ ወይም ሰነፍ እንዲሆን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? ከፀሐይ በታች በደከምሁበትና ጠቢብ በሆንሁበት በድካሜ ሁሉ ላይ ጌታ ይሆንበታል፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

20እኔም ተመልሼ ልቤን ከፀሐይ በታች በደከምሁበት ድካም ሁሉ ተስፋ አስቈረጥሁት።

21ሰው በጥበብና በእውቀት በብልሃትም ከደከመ በኋላ ለሌላ ላልደከመበት ሰው ያወርሰዋልና፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ትልቅም መከራ ነው።

22ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ አሳብ የሰው ጥቅም ምንድር ነው?

23ዘመኑ ሁሉ ኀዘን፥ ጥረትም ትካዜ ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።

24ለሰው ከሚበላና ከሚጠጣ በድካሙም ደስ ከሚለው በቀር የሚሻለው ነገር የለም፤ ይህም ደግሞ ከእግዚአብሔር እጅ እንደ ተሰጠ አየሁ።

25ያለ እርሱ ፈቃድ የበላ ደስ ብሎትም ተድላን የቀመሰ ማን ነው?

26እርሱም ደስ ለሚያሰኘው ሰው ጥበብንና እውቀትን ደስታንም ይሰጠዋል፤ ለኃጢአተኛ ግን እግዚአብሔርን ደስ ለሚያሰኘው ሰው ይሰጥ ዘንድ እንዲሰበስብና እንዲያከማች ጥረትን ይሰጠዋል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።

ማብራሪያ

2:1-11 ሰሎሞን ብዙም ሳይቆይ ሐሴትና ደስታ ከንቱ መሆናቸውን አገኘ። ጩኸትና ግርግር የበዛበት ደስታ ሰውን ደስተኛ ለማድረግ ምንስ ይጠቅማል? የሰዎች ልቦች ከዓለም እርካታን ለማግኘት የሚያደርጓቸው ልዩ ልዩ ዘዴዎች፣ ከአንዱ ነገር ወደ ሌላው የመለዋወጣቸውም ሁኔታ፣ ትኩሳት እንደያዘው ሰው ዕረፍት አልባነት ነው። ራሱን ለወይን መስጠት ሞኝነት እንደሆነ ከተረዳ በኋላ፣ ቀጥሎ የመሳፍንትን ውድ መዝናኛዎች ሞከረ። ድሆች፣ እንዲህ ያለውን መግለጫ በሚያነቡበት ጊዜ፣ አለመርካትን ለመሰማት ይዘጋጃሉ። ነገር ግን የእነዚህ ሁሉ ስሜቶች መድኃኒት፣ ያ ሁሉ ንብረት በባለቤቱ ራሱ የተገመተበት ሁኔታ ነው። ሁሉም ከንቱና ነፋስን እንደመከታተል ነበር፤ ለእኛም ለሰሎሞን እንደሆነው ሁሉ፣ ተመሳሳይ ነገሮች ተመሳሳይ ውጤት ይሰጡን ነበር። ምግብና ልብስ ካለን፣ በእነርሱ እንበቃ። ጥበቡ ከእርሱ ጋር ኖረ፤ ታላቅ ሰብዓዊ እውቀት የያዘ ብርቱ ማስተዋል። ነገር ግን ከፍ ካሉ በረከቶች ጋር ካልተያያዘ የሚገኝ እያንዳንዱ ምድራዊ ደስታ፣ አእምሮን እንደበፊቱ የሚጓጓና ያልረካ ያስቀረዋል። ደስታ የምንገኝበት ሁኔታ ውጤት አይደለም። የመጨረሻው በረከት የሚገኘው በኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6