1ከንጉሥ ናቡከደነፆር፣ በምድር ሁሉ ለሚኖሩ ሕዝቦች፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋዎችን ለሚናገሩ ሰዎች ሁሉ፤ ሰላም ይብዛላችሁ!
2ልዑል አምላክ ያደረገልኝን ታምራዊ ምልክቶችንና ድንቅ ሥራዎች ስነግራችሁ እጅግ ደስ እያለኝ ነው።
3ምልክቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁስ እንዴት ብርቱ ነው! መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፤ ግዛቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።
4እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደልቶኝ በቤተ መንግሥቴም ተመችቶኝ እኖር ነበር።
5አንድ ያስፈራኝ ሕልም አየሁ፤ በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ፣ ወደ አእምሮዬ የመጡት ምስሎችና ራእዮች አስደነገጡኝ።
6ስለዚህ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ መጥተው ሕልሜን እንዲተረጒሙልኝ አዘዝሁ።
7ጠንቋዮቹ፣ አስማተኞቹ፣ ኮከብ ቈጣሪዎቹና መተተኞቹ በመጡ ጊዜ ሕልሙን ነገርኋቸው፤ ነገር ግን ሊተረጒሙልኝ አልቻሉም።
8በመጨረሻም በአምላኬ ስም ብልጣሶር ተብሎ የተጠራውና የቅዱሳን አማልክት መንፈስ ያለበት ዳንኤል ገብቶ በፊቴ ቆመ፤ ሕልሜንም ነገርሁት።
9እኔም እንዲህ አልሁት፤ “የጠቢባን አለቃ ብልጣሶር ሆይ፤ የቅዱሳን አማልክት መንፈስ በአንተ ውስጥ እንዳለ ዐውቃለሁ፤ ምንም ዐይነት ምስጢር አያስቸግርህም፤ ያየሁት ሕልም እነሆ፤ ተርጒምልኝ።
10በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ያየሁት ራእይ ይህ ነው፦ እነሆ በፊቴ በምድር መካከል ቁመቱ እጅግ ረጅም የሆነ ዛፍ ቆሞ ተመለከትሁ።
11ዛፉም እጅግ አደገ፤ ጠነከረም፤ ጫፉም ሰማይ ደረሰ፤ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ይታይ ነበር።
12ቅጠሎቹ ያማሩ፣ ፍሬዎቹ የተንዠረገጉ ነበሩ፤ በላዩም ለሁሉ የሚሆን ምግብ ነበረበት። የምድር አራዊት ከጥላው በታች ያርፉ ነበር፤ በቅርንጫፎቹም ላይ የሰማይ ወፎች ይኖሩ ነበር፤ ፍጥረትም ሁሉ ከእርሱ ይመገብ ነበር።
13“በዐልጋዬ ላይ ተኝቼ ሳለሁ ባየሁት ራእይ አንድ ቅዱስ መልእክተኛ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ።
14እርሱም ድምፁን ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፤ ‘ዛፉን ቊረጡ፤ ቅርንጫፎቹን ጨፍጭፉ፤ ቅጠሎቹን አራግፉ፤ ፍሬውንም በትኑ፤ ከሥሩ ያሉት እንስሶች፣ በቅርንጫፎቹም ላይ ያሉት ወፎች ይሽሹ።
15ነገር ግን ጒቶውና ሥሩ በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ። “ ‘በሰማይ ጠል ይረስርስ፤ በጥሻም ውስጥ ከአራዊት ጋር ይኑር።
16አእምሮው ከሰው አእምሮ ይለወጥ፤ የእንስሳም አእምሮ ይሰጠው፤ ሰባት ዓመትም ይለፍበት።
17“ ‘ውሳኔው በመልእክተኞች ተገልጾአል፤ ፍርዱም በቅዱሳኑ ተነግሮአል፤ ይኸውም፣ ልዑል በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ፣ ከሰዎችም የተናቁትን በላያቸው እንደሚሾም፣ ሕያዋን ሁሉ ያውቁ ዘንድ ነው።’
18“እኔ ናቡከደነፆር ያየሁት ሕልም ይህ ነው፤ አሁንም ብልጣሶር ሆይ፤ በመንግሥቴ ካሉ ጠቢባን ሁሉ አንዳቸውም ሊተረጒሙልኝ ስላልቻሉ፣ ምን ማለት እንደሆነ ንገረኝ። አንተ የአማልክት መንፈስ በውስጥህ ስላለ ልትተረጒምልኝ ትችላለህ።
19ከዚያም ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል ለጥቂት ጊዜ በጣም ታወከ፤ ሐሳቡም አስደነገጠው። ንጉሡም፣ “ብልጣሶር ሆይ፤ ሕልሙም ሆነ ትርጒሙ አያስደንግጥህ” አለው። ብልጣሶርም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “ሕልሙ ለሚጠሉህ ይሁን፤ ትርጒሙም ለጠላቶችህ!
20እጅግ አድጎና ጠንክሮ ያየኸው ዛፍ፣ ጫፉም እስከ ሰማይ ደርሶ በምድር ሁሉ የሚታየው፣
21ቅጠሎቹ የሚያምሩ፣ ፍሬውም ተንዠርግጎ ለሁሉ ምግብ የሆነው፣ የዱር አራዊት መጠለያ የሆነውና በቅርንጫፎቹ ላይ ለሰማይ ወፎች ጎጆ መሥሪያ ያለው፣
22ንጉሥ ሆይ፤ ያ ዛፍ አንተ ነህ፤ ታላቅና ብርቱ ሆንህ፤ ታላቅነትህ አድጎ እስከ ሰማይ ደረሰ፤ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ተንሰራፋ።
23“ንጉሥ ሆይ፤ አንተ፣ ‘ዛፉን ቊረጡ፣ አጥፉትም፤ በብረትና በናስ የታሰረውን ጒቶና ሥሩን በሜዳው ሣር ላይ በብረትና በናስ ታስሮ በመሬት ውስጥ ይቈይ፤ በሰማይ ጠል ይረስርስ፤ እንድ ዱር አራዊትም ይኑር፤ ሰባት ዓመትም ይለፍበት’ እያለ ከሰማይ የወረደውን ቅዱሱን መልእክተኛ አየህ።
24“ንጉሥ ሆይ፤ ትርጒሙ ይህ ነው፤ ልዑሉ በንጉሡ በጌታዬ ላይ ያወጣው ዐዋጅ ይህ ነው፤
25ከሕዝብ ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ ዱር አራዊትም ጋር ትኖራለህ። እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ በሰማይ ጠልም ትረሰርሳለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመታት ያልፉብሃል።
26የዛፉ ጒቶ ከነሥሩ እንዲቀር መታዘዙ፣ ሥልጣን ከሰማይ መሆኑን ስታውቅ መንግሥትህ እንደሚመለስልህ ያመለክታል።
27ስለዚህ ንጉሥ ሆይ፤ ምክሬን ስማ፤ ኀጢአት መሥራትን ትተህ ትክክለኛ የሆነውን አድርግ፤ ክፋትን ትተህ ለተጨቈኑት ቸርነትን አድርግ፤ ምናልባት በሰላም የምትኖርበት ዘመን ይራዘምልህ ይሆናል።”
28ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤
29ከዐሥራ ሁለት ወራት በኋላ፣ ንጉሡ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ሲመላለስ ሳለ፣
30“በብርቱ ኀይሌ፣ ለገናናው ክብሬ ንጉሣዊ መኖሪያ ትሆን ዘንድ ያሠራኋት ታላቂቷ ባቢሎን ይህች አይደለችምን?” አለ።
31ንግግሩን ገና ከአፉ ሳይጨርስ፣ እንዲህ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ፤ “ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ፤ ስለ አንተ የታወጀው ይህ ነው፤ መንግሥትህ ከአንተ ተወስዶአል፤
32ከሕዝብ መካከል ትሰደዳለህ፤ ከዱር አራዊት ጋርም ትኖራለህ፤ እንደ ከብት ሣር ትበላለህ፤ ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ሁሉ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለውና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ እስክታውቅ ድረስ ሰባት ዓመት ያልፋል።”
33ወዲያውኑ በናቡከደነፆር ላይ የተነገረው ሁሉ ተፈጸመ፤ ከሕዝቡ መካከል ተሰደደ፤ እንደ ከብትም ሣር በላ። የራስ ጠጒሩ እንደ ንስር ላባና፣ ጥፍሮቹም እንደ ወፍ ጥፍሮች እስኪያድጉ ድረስ ሰውነቱ በሰማይ ጠል ረሰረሰ።
34ጊዜው ከተፈጸመ በኋላ፣ እኔ ናቡከደነፆር ዐይኖቼን ወደ ሰማይ አነሣሁ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁት፤ ለዘላለምም የሚኖረውን ወደስሁት፤ ክብርንም ሰጠሁት። ግዛቱ የዘላለም ግዛት ነው፤ መንግሥቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ ይኖራል።
35የምድር ሕዝቦች ሁሉ፣ እንደ ኢምንት ይቈጠራሉ፤ በሰማይ ኀይላት፣ በምድርም ሕዝቦች ላይ፣ የወደደውን ያደርጋል፤ እጁን መከልከል የሚችል የለም፤ ‘ምን ታደርጋለህ?’ ብሎ የሚጠይቀውም የለም።
36አእምሮዬ እንደ ተመለሰልኝ፣ ወዲያው ለመንግሥቴ ክብር፣ ግርማዊነቴና ሞገሴ ተመለሱልኝ፤ አማካሪዎቼና መኳንንቴ ፈለጉኝ፤ ወደ ዙፋኔም ተመለስሁ፤ ከቀድሞውም የበለጠ ታላቅ ሆንሁ።
37የሰማይ አምላክ የሚያደርገው ሁሉ ትክክል፣ መንገዶቹም ሁሉ ጽድቅ ስለሆኑ፣ አሁንም እኔ ናቡከደነፆር እርሱን አወድሰዋለሁ፤ ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ፤ አከብረዋለሁም፤ እርሱም በትዕቢት የሚመላለሱትን ማዋረድ ይችላል።