ትንቢተ ዳንኤል 3

AMHNIVአማርኛ30 ጥቅሶች7:44 አዳምጥ
አዳምጥ 7:44 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ንጉሡ ናቡከደነፆር ከፍታው ሥልሳ ክንድ፣ ወርዱ ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው።

2ከዚያም መኳንንትን፣ ሹማምትን፣ አገረገዦችን፣ አማካሪዎችን፣ የግምጃ ቤት ኀላፊዎችን፣ ዳኞችን፣ ሌሎች የሕግ ዐዋቂዎችንና በየአውራጃው ያሉትን ሹማምንት ሁሉ ላቆመው ምስል ምረቃ በዓል እንዲመጡ ጠራ።

3መኳንንቱ፣ ሹማምቱ፣ አገረገዦችን፣ አማካሪዎችን፣ የግምጃ ቤት ኀላፊዎቹ፣ ዳኞቹ፣ ሌሎች የሕግ ዐዋቂዎችና በየአውራጃው ያሉ ሹማምት ሁሉ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው ምስል ምረቃ በዓል ተሰበሰቡ፤ በምስሉም ፊት ቆሙ።

4ከዚያም ከፍ ባለ ድምፅ እንዲህ የሚል ዐዋጅ ታወጀ፤ “ሕዝቦች ሆይ፤ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የምትናገሩ ሰዎች ሁሉ፤ እንድታደርጉ የታዘዛችሁት ይህ ነው፦

5የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት እንዲሁም የዘፈን ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ መስገድ አለባችሁ፤

6ተደፍቶ የማይሰግድ ማንም ሰው ቢኖር፣ ወዲያውኑ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።”

7ስለዚህ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ሁሉ ድምፅ በሰሙ ጊዜ ወዲያውኑ ሕዝቡ ሁሉ፣ መንግሥታትና ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች፣ ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ተደፍተው ሰገዱ።

8በዚህ ጊዜ አንዳንድ ኮከብ ቈጣሪዎች ወደ ፊት ቀርበው አይሁድን ከሰሱ፤

9ንጉሥ ናቡከደነፆርንም እንዲህ አሉት፤ “ንጉሥ ሆይ፤ ለዘላለም ንገሥ!

10ንጉሥ ሆይ፤ አንተ እንዲህ ብለህ ዐዋጅ አውጥተህ ነበር፤ የመለከትና የእንቢልታ፣ የመሰንቆና የክራር፣ የበገናና የዋሽንት፣ የዘፈንም ድምፅ የሰማ ሁሉ ለወርቁ ምስል ተደፍቶ መስገድ አለበት፤

11ማንም ተደፍቶ ለወርቁ ምስል ባይሰግድ በሚንበለበለው የእሳት እቶን ውስጥ ይጣላል።

12ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ በባቢሎን አውራጃ አስተዳዳሪዎች አድርገህ የሾምሃቸው ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ የሚባሉት አንዳንድ አይሁድ ትእዛዝህን አይቀበሉም፤ አማልክትህን አያገለግሉም፤ አንተም ላቆምኸው የወርቅ ምስል አይሰግዱም።”

13ንጉሥ ናቡከደነፆር በታላቅ ቍጣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስጠራቸው፤ እነዚህንም ሰዎች በንጉሡ ፊት አቀረቧቸው፤

14ናቡከደነፆርም እንዲህ አላቸው፤ “ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ሆይ፤ እኔ ላቆምሁት ምስል አለመስገዳችሁ፣ አማልክቴንም አለማገልገላችሁ እውነት ነው?

15አሁንም ቢሆን የመለከቱንና የእምቢልታውን፣ የመሰንቆውንና የክራሩን፣ የበገናውንና የዋሽንቱን፣ የዘፈኑንም ሁሉ ድምፅ ስትሰሙ፣ እኔ ላቆምሁት የወርቅ ምስል ተደፍታችሁ ለመስገድ ዝግጁ ከሆናችሁ መልካም! ባትሰግዱለት ግን ወዲያውኑ ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ትጣላላችሁ፤ ታዲያ ከእጄ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ ማን ነው?”

16ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ለንጉሡ እንዲህ ብለው መለሱ፤ “ናቡከደነፆር ሆይ፤ በዚህ ጒዳይ ላይ ስለ ራሳችን መልስ መስጠት አያስፈልገንም።

17ንጉሥ ሆይ፤ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ብንጣል፣ የምናመልከው አምላክ ሊያድነን ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል።

18ነገር ግን ንጉሥ ሆይ፤ ባያድነንም እንኳ፤ አማልክትህን እንደማናገለግል፣ ላቆምኸውም የወርቅ ምስል እንደማንሰግድ ዕወቅ።”

19ከዚያም ናቡከደነፆር በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ እጅግ ተቈጣ፣ ፊቱም ተለወጠባቸው፤ የእቶኑ እሳትም ቀደም ሲል ከነበረው ሰባት ዕጥፍ ተደርጎ እንዲነድ አዘዘ፤

20ከሰራዊቱም ብርቱ የሆኑትን ጥቂት ወታደሮች፣ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን አስረው ወደሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ።

21እነርሱም መጐናጸፊያቸውን፣ ሱሪያቸውን፣ የራስ ጥምጥማቸውንና ሌሎች ልብሶቻቸውን እንደ ለበሱ ታስረው በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ተጣሉ።

22የንጉሡ ትእዛዝ አስቸኳይ ስለ ነበረና የእቶኑም እሳት እጅግ ስለ ነደደ፤ የእሳቱ ወላፈን ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን ወስደው የጣሏቸውን ወታደሮች ገደላቸው።

23ሦስቱ ሰዎች ግን ተጠፍረው እንደ ታሰሩ በሚንበለበለው የእቶን እሳት ውስጥ ወደቁ።

24ከዚህ በኋላ ንጉሥ ናቡከደነፆር በአድናቆት ከተቀመጠበት ዘሎ በመነሣት አማካሪዎቹን “አስረን በእሳት ውስጥ የጣልናቸው ሰዎች ሦስት አልነበሩምን?” ሲል ጠየቀ። እነርሱም፣ “ንጉሥ ሆይ፤ እውነት ነው” አሉ።

25እርሱም፣ “እነሆ፤ ያልታሰሩና ያልተጎዱ አራት ሰዎች በእሳቱ ውስጥ ሲመላለሱ አያለሁ፤ አራተኛውም የአማልክትን ልጅ ይመስላል” አላቸው።

26ናቡከደነፆርም ወደሚነደው የእቶን እሳት በር ቀረብ ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ፣ “እናንተ የልዑል አምላክ አገልጋዮች ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ፤ ኑ ውጡ ወደዚህ ኑ” አላቸው። ስለዚህ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብድናጎ ከእሳቱ ወጡ፤

27መኳንንቱ፣ ሹማምንቱ፣ አገረ ገዦቹና የቤተ መንግሥት አማካሪዎችም በዙሪያቸው ተሰበሰቡ፤ እነርሱም እሳቱ ሰውነታቸውን እንዳልጎዳ፣ ከራሳቸውም ጠጒር አንዲቷ እንኳ እንዳልተቃጠለች አዩ፤ የመጐናጸፊያቸው መልክ አልተለወጠም፤ የእሳትም ሽታ በላያቸው አልነበረም።

28ከዚያም ናቡከደነፆር እንዲህ አለ፤ “መልአኩን ልኮ አገልጋዮቹን ያዳነ፣ የሲድራቅ፣ የሚሳቅና የአብደናጎ አምላክ ይባረክ፤ በእርሱ በመታመን የንጉሡን ትእዛዝ ጥሰው፣ ከአምላካቸው በቀር ሌላ አምላክ ለማገልገልም ሆነ ለእርሱ ለመስገድ ፈቃደኛ ባለመሆን ሕይወታቸውን አሳልፈው ሰጥተዋልና።

29ስለዚህ እንደዚህ የሚያድን ሌላ አምላክ የለምና በሲድራቅ፣ በሚሳቅና በአብደናጎ አምላክ ላይ ማናቸውንም ቃል የሚናገሩ ሕዝቦችም ሆኑ ልዩ ልዩ ቋንቋ የሚናገሩ ሁሉ ይቈራረጣሉ፤ ቤቶቻቸውም የፍርስራሽ ክምር ይሆናሉ ብዬ አዝዣለሁ።”

30ከዚያም ንጉሡ ሲድራቅን፣ ሚሳቅንና አብደናጎን በባቢሎን አውራጃ ላይ ሾማቸው።

ማብራሪያ

3:1-7 የምስሉ ከፍታ ወደ ሠላሳ ክንድ ያህል ሲሆን፣ ምናልባትም መቀመጫው ተጨምሮበት ይሆናል። እንዲሁም ይበልጥ የሚታሰበው ከጥቅል ውድ ብረት የተሰራ ሳይሆን በወርቅ ሳህኖች ብቻ የተሸፈነ ነበር። ትዕቢትና ጠባብ አመለካከት ሰዎችን ተገዢዎቻቸውን ትክክልም ይሁን ስህተት ሃይማኖታቸውን እንዲከተሉ ያስገድዳሉ። ዓለማዊ ጥቅም ሲያጓጓና ቅጣትም ሲያስፈራ፣ እምቢ የሚሉ ጥቂቶች ናቸው። ይህ ለቸልተኞች፣ ለስጋውያንና ለማያምኑት ቀላል ነው፤ እነርሱም አብዛኞቹ ናቸው። አብዛኞቹም በራሳቸው መንገድ ይሄዳሉ። ግድ የለሹ ዓለም በሙዚቃ ዜማ የማይሳበው ወይም በእቶን እሳት አስፈሪነት የማይገፋበት ምንም የከፋ ነገር የለም። በእንደዚህ ባሉ ዘዴዎች ሐሰተኛ አምልኮ ተመስርቶ ሲዘልቅ ቆይቷል።

3:8-18 እውነተኛ አምልኮ መንፈስን የሚያረጋጋ፣ የሚያቀዘቅዝና የሚያለሰልስ ነው። ነገር ግን አጉል እምነትና ለሐሰተኛ አማልክት መሰጠት የሰዎችን ፍላጎት ያነድዳል። ጉዳዩ በአጭር ቃል ተጠቃልሏል፦ "ተመለሱ፣ አለዚያ ትቃጠላላችሁ።" ትዕቢተኞች ሰዎች አሁንም ቢሆን እንደ ናቡከደነፆር፡ "ኃይሉን ፈርቼ የማከብርለት እግዚአብሔር ማነው?" ለማለት ዝግጁ ናቸው። ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ ሊታዘዙ ወይም እንዳልሆኑ አላመነቱም። ሕይወትም ሆነ ሞት ከግምት ውስጥ መግባት የለባቸውም ነበር። ኃጢአትን ለማስወገድ የሚፈልጉ ሰዎች፣ በሚፈተኑበት ወይም በሚፈሩበት ነገር ላይ ግልጽ የሆነ ክፋት ሲታይ፣ ከፈተና ጋር መደራደር የለባቸውም። በዚያ ላይ አትቆሙ፣ ነገር ግን ክርስቶስ እንዳደረገው፡ "ከኋላዬ ሂድ አንተ ሰይጣን!" በሉ። ቀጥተኛ መልስ በሚጠበቅበት ጊዜ አሻሚ መልስ አላዘጋጁም። ግዴታቸውን ዋና ጉዳያቸው የሚያደርጉ ሰዎች ስለ ፍጻሜው መጨነቅ ወይም መፍራት አያስፈልጋቸውም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6

AMHEVG ንጉሡ ናቡከደነፆር ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነውን የወርቁን ምስል አሠራ፤ በባቢሎንም አውራጃ በዱራ ሜዳ አቆመው። አማርኛ ENGNIV King Nebuchadnezzar made an image of gold, ninety feet high and nine feet wide, and set it up on the plain of Dura in t… English BCV ንጉስ ናቡከደነፆር ስሳ እመት ዝቑመቱ፥ ሽዱሽተ እመት ዝጐድኑ ናይ ወርቂ ምስሊ ኣስርሐ። ኣብ ጐልጐል ዱራ ኣብ ኣውራጃ ባቢሎንውን ኣቖሞ። ትግርኛ GAZBIB Nebukadnezaar mootichi bifa fakkeenyaa hojjaa isaa dhundhuma jaatamaan, bal'ina isaa immoo dhundhuma ja'aan warqee irra… Afaan Oromoo BCV GIZ አመ ዐሠርቱ ወሰማንቱ ዓመተ መንግሥቱ ለናቡከደነጾር ገብረ ምስለ ዘወርቅ ኑኁ ስሳ በእመት ወግድሙ ስድስ በእመት፤ ወአቀሞ ውስተ ሐቅለ ዱራ ብሔረ ባቢሎን። giz GAZGAZ Nebukadnezaar mootichi bifa fakkeenyaa hojjaa isaa dhundhuma jaatamaan, bal'ina isaa immoo dhundhuma ja'aan warqee irra… Afaan Oromoo BCV aksum ንጉስ ናቡከደነፆር ስሳ እመት ዝቑመቱ፥ ሽዱሽተ እመት ዝጐድኑ ናይ ወርቂ ምስሊ ኣስርሐ። ኣብ ጐልጐል ዱራ ኣብ ኣውራጃ ባቢሎንውን ኣቖሞ። ትግርኛ SWAHSUV Nebukadreza, mfalme, alifanya sanamu ya dhahabu, ambayo urefu wake ulikuwa ni dhiraa sitini, na upana wake dhiraa sita;… Kiswahili