መጽሐፈ ሲራክ 47

AMHSDVአማርኛ25 ጥቅሶች

1ከእርሱም በኋላ ናታን ተነሣ፤በዳዊትም ዘመን ትንቢት ተናገረ።

2ስቡን ከድኅነቱ መሥዋዕት እንደሚለዩእንደዚሁ ዳዊት ከእስራኤል ልጆች ተለየ።

3በእርሱም ዘንድ አንበሳ እንደ ፍየል ጠቦት፥ግስላም እንደ በግ ጠቦት ነበር።

4በወጣትነቱ አርበኛን የገደለ አይደለምን?እጁንስ አንሥቶ ድንጋይ በወነጨፈ ጊዜ ጎልያድን ግንባሩን የመታው፥ ናላውንም የበጠበጠው አይደለምን?የሕዝቡንስ ተግዳሮት ያስወገደ አይደለምን?

5ልዑል እግዚአብሔርን ለምኖታልናበሰልፍ ኀይለኛውን ሰው ይገድል ዘንድየወገኖቹንም ቀንድ ያጸና ዘንድ በቀኝ እጁ ኀይልን ሰጠው።

6ዘፋኞቹም ዳዊትን ዐሥር ሺህ ገዳይ አሉት፤በእግዚአብሔርም በረከት አመሰገኑት፤የክብር ዘውድንም ተቀዳጀ።

7በዙሪያው ያሉ ጠላቶቹንም ቀጠቀጣቸው፤ጠላቶቹ ፍልስጥኤማውያንንም አዋረዳቸው፤እስከ ዛሬም ድረስ ቀንዳቸውን ሰበረ።

8በሚሠራው ሥራ ሁሉ ቅዱስና ልዑል እግዚአብሔርን በምስጋና ቃል አመሰገነ፤በፍጹም ልቡም ፈጣሪውን አመሰገነው፤ ወደደውም።

9በመሠዊያውም ፊት መዘምራንን መደበ፤የቃላቸውም ዜማ ያማረና የጣፈጠ ነበር።

10መልካም በዓልንም አደረገ፤ዓመቱን ሁሉ ደስ አሰኘ፥ቅዱስ ስሙንም አመሰገነው፤ቅድስናውም ከነግህ ጀምሮ ይነገራል።

11እግዚአብሔርም ኀጢአቱን አስተሰረየለት፤ቀንዱንም ለዘለዓለሙ ከፍ ከፍ አደረገለት፤የተባረከች መንግሥትን፥ የእስራኤልንም የክብር ዙፋን ሰጠው።

12ከእርሱም በኋላ ጠቢብ የሆነ ልጁ ተተካለትስለ እርሱም በስፋት ኖረ።

13ሰሎሞንም በሰላም ዘመን ነገሠ፥እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ሁሉ አሳረፈው፤በስሙ ቤትን ሠራ፤ የዘለዓለም መቅደሱንም አዘጋጀ።

14ሰሎሞን ሆይ፥ ከሕፃንነትህ ጀምሮ ጥበብህ እንዴት በዛ፤ማስተዋልህም እንደ ፈሳሽ ውኃ ሞላ።

15ጥበብህ ምድርን ሸፈነቻት፥ምሳሌህን፥ የነገርህንም ትርጓሜ አበዛህ።

16ስምህም እስከ ሩቅ ደሴት ድረስ ተሰማ፤ስለ ሰላምህም ተወደድህ።

17ሀገሮችም ስለ መዝሙርህ፥ ስለ ምሳሌህ፥ስለ እንቆቅልሾችህና ስለ ትርጓሜዎችህ አደነቁህ።

18የእስራኤል አምላክ በተባለ በእግዚአብሔር ስም፥ወርቁንም እንደ እርሳስ አደለብኸው፤ ብርንም እንደ ማዕድን ቅልቅል መላኸው።

19ሴቶች ልቡናህን ለወጡት፤በሥጋህም ሠለጠኑብህ።

20ክብርህን አስነቀፍህ፤ ዘርህንም አሳደፍኽ፤በልጆችህም ላይ መቅሠፍትንና ጥፋትን አመጣህ፤ስንፍናህም አስደነገጠኝ።

21መንግሥትህም ተከፈለ፤ዐመፀኛ መንግሥትም ከኤፍሬም ወጣች።

22እግዚአብሔር ግን ቸርነቱን አልተወም፤ሥራውንም አላጠፋም፤ የጻድቃኑንም ልጆች አልደመሰሰም፤የሚወዱትንም ሰዎች ዘር አላጠፋም፤ለያዕቆብም ቅሬትን ሰጠው፥ ከእርሱም ለዳዊት ሥርን ሰጠው።

23ሰሎሞንም እንደ አባቶቹ አረፈከእርሱም በኋላ አእምሮ የሌለው ልጁን ለእስራኤል ተወ።ይኸውም ሕዝቡን በምክሩ ያሳመፃቸው ሮብዓም ነው።እስራኤልን ያሳታቸው፥ ለኤፍሬምም የኀጢአት መንገድን ያሳየ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ነበረ።

24ኀጢአታቸውም ፈጽሞ በዛ፥ከሀገራቸውም አስወጥቶ ሰደዳቸው።

25ፍዳቸውም እስክትደርስባቸው ድረስ ኀጢአትን ሁሉ ፈለጓት።

ትርጉሞች1 · 1