1አለቃም አድርገው ቢሾሙህ ራስህን አታኵራ፤ከእነርሱ እንደ አንዱ ሁን፤ኀዘናቸውንም እዘን፤ ተቀምጠህም ፍረድላቸው።
2ሥራህን ጨርሰህ ዕረፍ፤መልእክትህን ጨርሰህ የክብር ዘውድን ታገኝ ዘንድ ከእነርሱ ጋራ ደስ ይበልህ።
3ሽማግሌ ሆይ፥ ተናገር፤ ይገባሃልም፥ለበጎ ነገርም ቸል አትበል፤የጥበብህንም ነገር ተናገር።
4ለመረመረህ ሰው ሁሉ ቃልህን አትናገር፤እንዳገኘህም አትራቀቅ።
5በወርቅ ጌጥ ክቡር ዕንቍ ደስ እንደሚያሰኝ፥ዘፈንም ወይን በሚጠጡ ሰዎች ዘንድ እንዲሁ ነው።
6በወርቅ ዝርግፍ ላይ ዕንቍ እንደሚያምር፤ዘፈንና መሰንቆ በመጠጥ ቤት እንዲሁ ያማረ ነው።
7ጎልማሳ! ከተፈቀደልህ ተናገር፤ዳግመኛም ቢጠይቁህ በጭንቅ ተናገር።
8አንድ ጊዜ ተናግረህ፥ ወዲያውኑ ነገርህን ጨርስ፤እያወቅህም በአንደበትህ ዝም በል።
9በታላላቆች መካከል አትቀመጥ፤ሌላ ሰውም ሲናገር ነገርህን አትናገር።
10መብረቅ ከነጐድጓድ በፊት እንደሚሮጥ፥ እንዲሁ የሚያፍር ሰው መከበሩ በፊቱ ነው።
11ወደ ቤትህ ገብተህ ሁሉን በጊዜው መጥነህ አድርግ፤በዚያም ደስ ይበልህ ተጫወትም።
12የሚገባውንና የሚወደደውንም ሁሉ አድርግ፤የትዕቢትን ነገር እንዳትናገር ዕወቅ፤በቃልህም አትበድል።
13ከዚህ ሁሉ ጋራ ፈጣሪህን አመስግነው፤እርሱም ከበረከቱ ሁሉ ያጠግብሃል።
14እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ለሕጉ ይገዛል፤ወደ እርሱም ፈጥነው የሚሄዱ ሰዎች መፍቅዳቸውን ያገኛሉ።
15ሕጉንም የሚፈልገው ከእርሱ ይጠግባል፤በእርሱ የሚጠራጠር ግን ይወድቃል፤ ይበድላልም።
16እግዚአብሔርን የሚፈሩት ሰዎች ፍርድን ያገኛሉ፤በእኩለ ቀንም ተበቅሎ ጠላቶቻቸውን ያጠፋላቸዋል።
17ኀጢአተኛ ሰው ግን የሚመክሩትን አይሰማም፤ሁሉም እንደ እርሱ ይመስለዋል።
18ብልህ ሰው ያለ ምክር የሚሠራው ሥራ የለም፤የሚሠራውም ሥራ የበጀ ይሆንለታል፤ፍርሀትን የማያስብ ትዕቢተኛ ጠላት ግን ያለ ምክር ይሠራል።
19ልጄ ሆይ፥ አንተ ግን ያለ ምክር የምትሠራው ሥራ አይኑር፤የሠራኸውንም ሥራ አታጥፋ።
20በጥፋት ድንጋይ እንዳትሰነካከል፥መንገድ በሌለበት በምድረ በዳ አትሂድ።
21ጠላትህን በምድረ በዳ አትመነው።
22በፈቃድህ የማይሄድ ልጅህን ስንኳ አትመነው።
23በሠራኸው ሥራ ሁሉ ሰውነትህን ደስ አሰኛት፥በሁሉም ትእዛዙን ጠብቅ።
24ሕጉን የሚጠብቅ ሰው የመጽሓፉን ትእዛዝ ይሰማል፤በእግዚአብሔርም የሚያምን ሰው የሚያጣው ነገር የለም።