መጽሐፈ ሲራክ 25

AMHSDVአማርኛ26 ጥቅሶች

1በእነዚህ በሦስቱ ነገሮች ያማርሁ ሆንሁ፤በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ያማርሁ ሆኜ ቆምሁ፥እነዚህም በአንድ ልብ የሚተባበሩ ወንድማማቾች፥የባልንጀሮች ፍቅር፥ የባልና ሚስትም ስምምነት ናቸው።

2ሦስት ዐይነት ሰዎችን ሰውነቴ ፈጽማ ጠላቻቸው፤ኑሯቸውም እጅግ አበሳጨኝ፤እነዚህም ትዕቢተኛ ድሃ፥ንፉግ ባለጸጋና አእምሮ የሌለው ሴሰኛ ሽማግሌ ናቸው።

3ከሕፃንነትህ ጀምረህ ያልተመከርህ፥በእርጅናህ ጊዜ እንዴት ብልህ ትሆናለህ?

4ሺበት ፍርድ ሊሰጥ ይገባዋል፤ሽማግሎችም መምከር ይገባቸዋል።

5ለሽማግሎችም ጥበብ ይገባቸዋል፤ለታላላቅ ሰዎችም ጥበብን መማር ይገባቸዋል።

6የትምህርት ብዛት የሽማግሎች ዘውዳቸው ነው፤መመኪያቸውም እግዚአብሔርን መፍራት ነው።

7በልቤ ያደነቅኋቸው ዘጠኝ ናቸው፤ዐሥረኛውን ግን በቃሌ እናገራለሁ፤እነርሱም በልጆቹ ደስ የሚለው ሰው፥በሕይወቱም ሳለ የጠላቱን ውድቀት የሚያይ ሰው ናቸው።

8ልባም ሴትን ያገባ ብፁዕ ነው፤በአንደበቱም ያልሳተ ሰው ብፁዕ ነው፤ከእርሱ ላነሰ ሰው ያላደረ ብፁዕ ነው፤

9ዕውቀትና ጥበብን ያገኛት ሰው፥የሚታዘዝለትንም ያገኘ ሰው ብፁዕ ነው።

10ጥበብን ያገኘ ሰው እንዴት ታላቅ ነው!ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚፈራ ይህን ይበልጠዋል።

11እግዚአብሔርን መፍራት ከሁሉ ትበልጣለች።

12እርሷንም የጠበቀ ሰውን የሚመስለው የለም።

13ከቍስል ሁሉ ይልቅ የልብ ቍስል ይከፋል፤ከክፋትም ሁሉ የሴት ክፋት ትከፋለች።

14በሁሉም ብትወድቅ በጠላትህ እጅ አትውደቅ፤ሁሉ ቢበቀልህ ጠላትህ አይበቀልህ።

15ከእባብ ራስ የሚከፋ ራስ የለም፤ከጠላትም ቂም የሚከፋ ቂም የለም።

16ከክፉ ሴት ጋራ ከምትኖር፥ከአንበሶችና ከምድር አውሬዎች ጋር መኖር ይሻላል።

17ክፋትዋ መልኳን ይለውጠዋል፤ፊትዋንም እንደ ድብ መልክ ያጠቍረዋል።

18ባሏንም በባልንጀሮቹ መካከል ይንቁታል፤መራራ ኀዘንንም ያሳዝኑታል፤አስጨንቀውም ይይዙታል።

19ክፋት ሁሉ ከሴት ክፋት ታንሳለች፤እርስዋም ወደ ኀጢአት ዕድል ታደርሳለች።

20የአሸዋ ዐቀበት የሽማግሌዎችን እግራቸውን እንደሚያደክም፥እንዲሁ ቀባጣሪ ሴት የዋህ ባልን ታደክመዋለች።

21የሴት መልኳ አያስትህ፤ ሀብቷም አያስጐምጅህ።መቅሠፍትና ጥፋት ጽኑ ውርደትም ናትና፤

22ሴት ባሏን ብትመግበው፥ቍጣን፥ አለማክበርንና ብዙ ዘለፋን የተሞላች ትሆናለች።

23ለልብ ቍስል ናት፥ ለፊትም ጥቁረት ናት፥ ለነፍስም ኀዘን ናት፤እንዲሁ ባሏን የማታከብር ሴትእንደ ሽባ እጅና ልምሾ እንደ ሆነ እግር ናት።

24በመጀመሪያም ኀጢአት ከሴት ተገኘች፤በእርስዋም ምክንያት ሁላችን እንሞታለን።

25ለውኃ መፍሰሻ አታብጅለትለሴትም የልብህን ምሥጢር አታውጣላት።

26እንደ ጠባይህ ካልሆነች ፍታት፤ከሰውነትህም ለያት።

ትርጉሞች1 · 1