መጽሐፈ ሲራክ 19

AMHSDVአማርኛ27 ጥቅሶች

1ሰካራም ሠራተኛ አይበለጥግም፥ጥቂቱን የሚያቃልል ብዙውን ያጠፋል።

2መጠጥና ሴት ጠቢባንን ያስትዋቸዋል፥ጋለሞታን የሚከተላት በደለኛ ነው።

3የዚህም ፍጻሜው ትልና ጥፋት ነው።ደፋር ሰውነት ከመከራ አትጠበቅም።

4ፈጥኖ የሚያምን ልቡናው ቀሊል ነው፥ኀጢአትን የሚሠራም ራሱን ይበድላል።

5ልቡናውን ደስ የሚያሰኝ ሰው ይደነቃል።

6ብዙ መናገርንም የሚጠላ ኀጢአቱን ያሳንሣል።

7የሰማኸውን ቃል አታውጣ፥ አትድገመውም፥ለዘለዓለሙም የባሰ አያገኝህም።

8በወዳጅና በጠላት ዘንድ የምትናገረው ነገር አይኑር፥ስተህ የሠራኸው ኀጢአትህንም አትናገር።

9ቢሰማ አይሰውርልህምና፥እስክትሞትም ድረስ ይጠብቅሃል።

10የሰማኸውን ቃል አታውጣ፥ከዚህም በኋላ የሚያገኝህ ክፉ ነገር እንደሌለ እመን።

11አላዋቂ ሰው የሰማውን ነገር እስከሚያወጣ ድረስ ይቅበዘበዛል፥ልጅ የምትወልድ ሴትም በምጥ እንደምትጨነቅ ይጨነቃል።

12የተወጋ ሰውም ጦሩን ከላዩ ይነቅል ዘንድ እንደሚቸኩል፥አላዋቂ ሰው የሰማውን ቃል ያወጣ ዘንድ ይቸኩላል።

13ወዳጅህን አላደረገ እንደ ሆነወይም አድርጎ እንደ ሆነ እንዳይደግም ገሥጸው።

14ወዳጅህን፥ አልተናገረ እንደ ሆነወይም ተናግሮ እንደ ሆነ እንዳይደግም ገሥጸው።

15ወዳጅህን በጥላቻ ነገር ተሠርቶበት ይሆናልና ገሥጸው፤ከልቡ ሳይፈቅድ የሚሳሳት ሰው አለና የነገሩህን ነገር ሁሉ አትመን።

16በአንደበቱ የማይሳሳት ማን ነው?

17ቍጣ ሳይበዛ ወዳጅህን ገሥጸው፥ስለ እግዚአብሔር ሕግም ቍጣን አሳልፋት።

18ጥበብ ሁላ እግዚአብሔርን መፍራት ናትና፥ጥበብም ሁላ ሕጉን ታስጠብቃለችና።

19ክፉን የሚያስተምር ጥበብ የለም፥ለኃጥኣንም ምክር ጥበብ የላትም።

20ከሁሉ የምትረክስ ክፋት አለች፥አእምሮ የጐደለው አላዋቂም አለ።

21ነገር ግን ከሚራቀቅ፥ የእግዚአብሔርንም ሕግ ከሚክድ ይልቅ፥እግዚአብሔርን የሚፈራ አላዋቂ ይሻላል።

22እየበደለ የሚራቀቅና የሚጠነቀቅ አለ፥ለባልንጀራው የሚያደላ፥ ለወዳጁም ፍርድን የሚያቀና መስሎ ፍርድን የሚለውጥ ሰው አለ።

23እያመሰገነ ለክፉ ነገር የሚያደላ ሰው አለ፥ልቡናው ግን ሽንገላን ተሞልትዋል።

24በልቡናው ሌላ ነገር እያለ ፊት አይቶ የሚያዳላ አለ፥ባላሰብኸውም ነገር ይመጣብሃል።

25ኀይሉ ቢደክም፥ በአንተም ላይ ክፉ ማድረግ ቢሳነው፥ያስትህ ዘንድ መከራን በግድ ያመጣብሃል።

26ሰው በመልኩ ይታወቃልና፥ ጠቢብም በገጹ ይታወቃል።

27ካለባበሱና ካካሄዱ፥ ከአሳሣቁም የተነሣ፥የሰው ጠባዩ ይታወቃል።

ትርጉሞች1 · 1