መጽሐፈ ዮዲት 5

ACEDአማርኛ24 ጥቅሶች

1የእስራኤል ልጆች ለጦርነት መዘጋጀታቸው፥ ወደ ተራራማው ከተማ የሚያስተላልፈውን መንገድ መዝጋታቸው፥ የከፍተኛ ኮረብታዎቻቸውን ራሶች ማጠራቸው፥ በሜዳዎቻቸው ወጥመድ ማበጀታቸው ለአሦር ዋና የጦር አዛዥ ለሆሎፎርኒስ ተነገረው፤

2እርሱም እጅግ በጣም ተቆጥቶ የሞዓብን ገዢዎች፥ የአሞንን የጦር አዛዦችና የባሕር ጠረፍ ገዢዎችን ጠራ፤

3እንዲህም አላቸው፦ “የከነዓን ልጆች እስቲ ንገሩኝ፥ በተራራማው አገር የሚቀመጠው ሕዝብ ምን ዓይነት ነው? በየትኞቹ ከተሞችስ ይኖራሉ? የሠራዊታቸው ብዛት ምን ያህል ነው? ኃይላቸውና ጽናታቸውስ ምን ላይ ነው? ሠራዊታቸውን የሚመራና እንደ ንጉሣቸው የተሾመስ ማን ነው?

4በምዕራብ ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ እነርሱ ሊቀበሉኝ ያልመጡት ስለምንድን ነው?”

5የአሞን ልጆች ሁሉ መሪ የሆነው አክዮር እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እንግዲህ ጌታዬ ከባርያህ አንደበት ቃል ስማ፤ በዚህ በተራራማው አገር፥ በአጠገብህ ስለሚኖሩ ሕዝብ እውነቱን እነግርሃለሁ፤ ከባርያህ አንደበት ሐሰት አይወጣም።

6ይህ ሕዝብ የከለዳውያን ዘር ነው።

7በፊት በእንግድነት በመስጴጦምያ ይኖሩ ነበር፥ ምክንያቱም በከላውዴዎን የነበሩት የአባቶቻቸውን አማልክት አንከተልም ብለው ነበርና።

8የአባቶቻቸውን መንገድ ትተዋልና፥ አሁን ያወቁትን የሰማዩን አምላክ አምልከዋልና፥ ከአማልክቶቻቸው ፊት አባረሩአቸው፤ ወደ መስጴጦምያ ሸሸተው መጡ፥ በዚያም ብዙ ዘመን ኖሩ።

9አምላካቸው ከሚኖሩበት አገር ወጥተው ወደ ከነዓን ምድር እንዲሄዱ አዘዛቸው፤ እዚያም ሄደው ሲቀመጡ በዚያ በብዙ ወርቅ፥ በብዙ ብርና በብዙ መንጋዎች በለጸጉ።

10የከነዓንን ምድር ረሃብ ባጠቃት ጊዜ ወደ ግብጽ ወረዱ፥ እራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ በዚያ ተቀመጡ፤ በዚያም በጣም ተባዙ፥ ዘራቸውም ከቍጥር በላይ ሆነ።

11ነገር ግን የግብጽ ንጉሥ በእነርሱ ላይ ተነሣባቸው፥ በጡብ ሥራ ላይ በማሰማራት አላግባብ ተጠቀመባቸው፤ ጨቆናቸው፥ ባርያዎችም አደረጋቸው።

12ወደ አምላካቸው ጮኹ፥ እርሱም በማይድን መቅሠፍት የግብጽን ምድር በሙሉ መታ፤ ግብጻውያንም ከፊታቸው አስወጡአቸው።

13እግዚአብሔርም በፊታቸው ቀይ ባሕርን አደረቀላቸው፤

14በሲናና በቃዴስ በርኔ መንገድ መራቸው፤ በምድረ በዳ የሚኖሩትንም ሁሉ አባረሩአቻው።

15በአሞራውያን ምድርም ተቀመጡ፤ ሐሴቦናውያንንም ሁሉ በኃይላቸው አጠፉአቸው፤ ዮርዳኖስን ተሻግረው ተራራማውን አገር ሁሉ ወረሱ።

16ከነዓናውያንን፥ ፌርዛውያንን፥ ኢያቡሳውያንን፥ ሴኬማውያንንና ጌርጌሳውያንን ሁሉ ከፊታቸው አስወጥተው በዚያ ብዙ ዘመን ኖሩ።

17በአምላካቸው ፊት ኃጢአትን እስካልሰሩ ድረስ በለጸጉ፥ ኃጢአትን የሚጠላ አምላካቸው ከእነርሱ ጋር ነውና።

18ነገር ግን እርሱ ከወሰነላቸው መንገድ ፈቀቅ ባሉ ጊዜ በብዙ ጦርነቶች ተደመሰሱ፥ ተማርከው ወደ ባእድ አገር ተወሰዱ፤ የአምላካቸው ቤተ መቅደስ ፈረሰ፤ ከተሞቻቸውም በጠላቶቻቸው ተያዙ።

19አሁን ግን ወደ አምላካቸው ተመልሰዋል፥ ከተበታተኑበትም ቦታ ተመልሰዋል፥ ቤተ መቅደሳቸው ያለበትን ኢየሩሳሌምንም ይዘዋል፤ ባዶውን ስለ ነበር ተራራማውን አገር ያዙ።

20ስለዚህ አሁን አልቃዬና ጌታዬ በዚህ ሕዝብ ጥፋት ካለበት፥ በአምላካቸው ላይ ኃጢአት ከሠሩና እኛም ጥፋታቸውን ካረጋገጥን ወጥተን እንገጥማቸዋለን።

21ያልበደሉ ሕዝቦች ከሆኑ ግን ጌታዬ አልፎአቸው ይሂድ፤ ጌታቸውና አምላካቸው ይቆምላቸዋልና፤ እኛም በምድር ሁሉ ፊት እንዋረዳለንና።

22አኪዮር ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ በድንኳኑ ዙሪያ ከቦ የነበረ ሕዝብ ሁሉ አጉረመረመ፤ የሆሎፎርኒስ ሹማምንትና በባሕሩ ዳርና በሞዓብ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ፥ መቆራረጥ አለበት አሉ።

23የእስራኤልን ልጆች አንፈራቸውም፤ ብርቱ ሰልፍ ለመቋቋም ኃይልና ብርታት የላቸውምና።

24ስለዚህ አሁን ጌታ ሆሎፎርኒስ እንውጣ፤ ለሠራዊትህ ሁሉ መብል ይሆናሉ።”

ትርጉሞች1 · 1