1በቀረውስ ወንድሞች ሆይ፤ በእናንተ ዘንድ እንደሆነው የጌታ ቃል በፍጥነት እንዲሠራጭና እንዲከበር ለእኛ ጸልዩልን፤
2ደግሞም ሰው ሁሉ እምነት ያለው ስለማይሆን ከዐመፀኞችና ከክፉ ሰዎች እንድንድን ጸልዩልን።
3ጌታ ግን ታማኝ ነው፤ እርሱም ያበረታችኋል፤ ከክፉውም ይጠብቃችኋል።
4እኛ ያዘዝናችሁን አሁን አደረጋችሁ፤ ወደ ፊትም እንደምታደርጉ በጌታ እንታመናለን።
5ጌታ ልባችሁን ወደ እግዚአብሔር ፍቅርና ወደ ክርስቶስ ጽናት ይምራው።
6ወንድሞች ሆይ፤ ሥራ ፈት ከሆነና ከእኛ በተቀበላችሁት ትምህርት መሠረት ከማይኖር ወንድም እንድትርቁ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛችኋለን፤
7የእኛን ምሳሌ እንዴት መከተል እንደሚገባችሁ እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና። ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ ሥራ ፈቶች አልነበርንም፤
8ደግሞም የማንንም እንጀራ በነጻ አልበላንም፤ ነገር ግን ከእናንተ በአንዳችሁም ላይ ሸክም እንዳንሆን ሌሊትና ቀን እንደክምና እንሠራ ነበር፤
9ይህን ያደረግነው ምሳሌነታችንን እንድትከተሉ ብለን እንጂ የሚያስፈልገንን ነገር ከእናንተ ለማግኘት ሥልጣን ሳይኖረን ቀርቶ አይደለም።
10ከእናንተ ጋር በነበርንበት ጊዜ፣ “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” ብለን ይህን ትእዛዝ ሰጥተናችሁ ነበርና።
11ከእናንተ አንዳንዶች ሥራ ፈቶች እንደሆኑ ሰምተናል፤ እነርሱም ያለ ሥራ እየዞሩ በሰው ጒዳይ ጣልቃ የሚገቡ ናቸው።
12እንደዚህ ያሉ ሰዎች ተግተው ሥራቸውን እንዲሠሩና እንጀራቸውን እንዲበሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዛቸዋለን፤ እንመክራቸዋለንም።
13እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ፤ መልካም ሥራን ከመሥራት ከቶ አትታክቱ።
14በዚህ መልእክት ላይ ላለው ቃላችን የማይታዘዝ ማንም ቢኖር፣ እንደዚህ ያለውን ሰው በጥንቃቄ ተከታተሉት፤ በሥራውም እንዲያፍር ከእርሱ ጋር አትተባበሩ።
15ሆኖም እንደ ወንድም ገሥጹት እንጂ እንደ ጠላት አትቍጠሩት።
16የሰላም ጌታ ራሱ በሁሉም ነገር ዘወትር ሰላም ይስጣችሁ። ጌታ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።
17ይህንን ሰላምታ በገዛ እጄ የጻፍሁት እኔ ጳውሎስ ነኝ፤ የመልእክቶቼም ሁሉ መለያ ይህ ነው፤ አጻጻፌም እንደዚህ ነው።
18የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን።