1ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ፣ ለራሱም ቤተ መንግሥት እንዲሠራ አዘዘ።
2እርሱም፣ የሚሸከሙ ሰባ ሺህ፣ ከኰረብታ ላይ ድንጋይ የሚፈልጡ ሰማንያ ሺህ ሰዎችና ሦስት ሺህ ስድስት መቶ የሥራ ተቈጣጣሪዎች አሰማራ።
3ከዚህ በኋላ፣ ሰሎሞን ለጢሮስ ንጉሥ ለኪራም የሚከተለውን ይህን መልእክት ላከ፤ “አባቴ ዳዊት የሚኖርበትን ቤተ መንግሥት ሲሠራ እንደ ላክህለት ሁሉ፣ ለእኔም የዝግባ እንጨት ላክልኝ።
4ሽታው ደስ የሚያሰኝ ዕጣን በፊቱ የሚታጠንበትን፣ የተቀደሰ እንጀራ በየጊዜው የሚቀርብበትን፣ በየጧቱና በየማታው፣ በየሰንበቱና በየመባቻው እንዲሁም በተወሰኑት በአምላካችን በእግዚአብሔር በዓላት የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን ቤተ መቅደስ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ሠርቼ እቀድስ ዘንድ አስቤአለሁ። ይህም ለእስራኤል የዘላለም ሥርዐት ነው።
5“አምላካችን ከሌሎች አማልክት ሁሉ ይበልጥ ታላቅ ስለ ሆነ፣ የምሠራውም ቤተ መቅደስ ታላቅ ይሆናል።
6ነገር ግን ሰማይና ከሰማያት በላይ ያለው ሰማይ እንኳን እርሱን ይይዘው ዘንድ አይችልምና፣ ቤተ መቅደስ ሊሠራለት የሚችል ማነው? በፊቱ ዕጣን የሚታጠንበትን እንጂ ቤተ መቅደስ እሠራለት ዘንድ እኔ ማን ነኝ?
7“ስለዚህ አንተ በወርቅና በብር፣ በናስና በብረት፣ በሐምራዊና በደማቅ ቀይ፣ በሰማያዊም ግምጃ ሥራ ዕውቀት ያለውን እንዲሁም አባቴ ዳዊት ካዘጋጃቸው ከእኔ የእጅ ባለ ሙያዎች ጋር በይሁዳና በኢየሩሳሌም የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ሥራ የሚሠራ ሰው ላክልኝ።
8ሰዎችህ ከሊባኖስ እንጨት በመቍረጥ ሥራ ዐዋቂዎች መሆናቸውን ስለማውቅ፣ ከሊባኖስ የዝግባ፣ የጥድና የሰንደል ዕንጨትም ላክልኝ፤ ሰዎቼም ከሰዎችህ ጋር አብረው ይሠራሉ።
9የምሠራው ቤተ መቅደስ ትልቅና እጅግ ውብ መሆን ስላለበት፣ ብዙ ጠርብ ያዘጋጁልኛልና።
10ዕንጨቱን ለሚቈርጡ አገልጋዮችህ ሃያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ ዱቄት፣ ሃያ ሺህ የባዶስ መስፈሪያ ወይን ጠጅና ሃያ ሺህ የባዶስ መስፈሪያ ዘይት እሰጣለሁ።”
11የጢሮስ ንጉሥ ኪራምም ለሰሎሞን እንዲህ ሲል በደብዳቤ መለሰለት፤ “እግዚአብሔር ሕዝቡን ስለሚወድድ አንተን በእነርሱ ላይ አነገሠህ፤”
12ኪራምም በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ! ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን፣ ለራሱም ቤተ መንግሥትን የሚሠራ፣ ብልኅነትንና ማስተዋልን የተሞላ ጥበበኛ ልጅ ለንጉሥ ዳዊት ሰጥቶአልና።
13“እጅግ ብልሃተኛ የሆነውን ኪራም አቢን ልኬልሃለሁ፤
14እርሱም እናቱ ከዳን ወገን፣ አባቱም የጢሮስ አገር ሰው ነው፤ በወርቅና በብር፣ በናስና በብረት፣ በድንጋይና በዕንጨት፤ እንዲሁም በሐምራዊና በሰማያዊ፣ በቀይ ግምጃና በቀጭን በፍታ ሥራ የሠለጠነ ሲሆን፣ በልዩ ልዩ ቅርጻ ቅርጽ ሥራ ልምድ ያካበተና የተሰጠውን ማናቸውንም ንድፍ በሥራ መተርጐም የሚችል ባለ ሙያ ነው። እርሱም ከአንተ የእጅ ሥራ ባለሙያዎችና ከጌታዬ ከአባትህ የእጅ ሥራ ባለ ሙያዎች ጋር አብሮ ይሠራል።
15“አሁንም ጌታዬ በሰጠው ተስፋ መሠረት ስንዴውንና ገብሱን፣ የወይራ ዘይቱንና የወይን ጠጁን ለአገልጋዮቹ ይላክ፤
16እኛም የሚያስፈልግህን ግንድ ሁሉ ከሊባኖስ ቈርጠንና አስረን እስከ ኢዮጴ ድረስ ቍልቍል በማንሳፈፍ እንሰድልሃለን፤ አንተም ወደ ኢየሩሳሌም ታስወስደዋለህ።”
17ሰሎሞን አባቱ ዳዊት ካደረገው ቈጠራ በኋላ፣ በእስራኤል ምድር የነበሩትን መጻተኞች ሁሉ ቈጠረ፤ ቊጥራቸውም አንድ መቶ አምሳ ሦስት ሺህ ስድስት መቶ ሆነ።
18ከእነዚህም ሰባ ሺውን ተሸካሚዎች፣ ሰማንያ ሺውን በኰረብታው ላይ ድንጋይ ፈላጮች፣ ሦስት ሺህ ስድስት መቶውን ደግሞ የሥራው ተቈጣጣሪዎች ሆነው ሰዎቹን እንዲያሠሩ መደበ።