መኃልየ መኃልይ 2

AMHNIVአማርኛ17 ጥቅሶች2:57 አዳምጥ
አዳምጥ 2:57 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እኔ የሳሮን ጽጌረዳ፣ የሸለቆም አበባ ነኝ።

2በእሾኽ መካከል እንዳለ ውብ አበባ፣ ውዴም በቈነጃጅት መካከል እንዲሁ ናት።

3በዱር ዛፎች መካከል እንዳለ እንኰይ፣ ውዴም በጐልማሶች መካከል እንዲሁ ነው፤ በጥላው ሥር መቀመጥ ደስ ያሰኛል፤ የፍሬውም ጣፋጭነት ያረካኛል።

4ወደ ግብዣው አዳራሽ ወሰደኝ፤ በእኔ ላይ ያለው ዐላማው ፍቅር ነው።

5በዘቢብ አበረታቱኝ፤ በእንኰይም አስደስቱኝ፤ በፍቅሩ ተይዤ ታምሜአለሁና።

6ግራ እጁን ተንተርሻለሁ፤ ቀኝ እጁም ዐቅፎኛል።

7እናንት የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት፣ ራሱ እስኪፈልግ ድረስ፣ ፍቅርን እንዳታስነሡት ወይም እንዳትቀሰቅሱት፣ በሚዳቋና በሜዳ ዋልያ አማጥናችኋለሁ።

8እነሆ፤ የውዴ ድምፅ በተራሮች ላይ እየዘለለ፣ በኰረብቶችም ላይ እየተወረወረ፣ ሲመጣ ይሰማኛል።

9ውዴ ሚዳቋ ወይም የዋልያ ግልገል ይመስላል፤ እነሆ፤ ከቤታችን ግድግዳ ኋላ ቆሞአል፤ በመስኮት ትክ ብሎ ወደ ውስጥ ያያል፤ በፍርግርጉም እያሾለከ ይመለከታል።

10ውዴም እንዲህ አለኝ፤ “ፍቅሬ ሆይ፤ ተነሺ፤ አንቺ የእኔ ቈንጆ፤ ከእኔ ጋር ነዪ።

11እነሆ! ክረምቱ ዐለፈ፤ ዝናሙም አባርቶ አበቃ፤

12አበቦች በምድር ላይ ታዩ፤ የዝማሬ ወቅት መጥቶአል፤ የርግቦችም ድምፅ፣ በምድራችን ተሰማ።

13በለስ ፍሬዋን አፈራች፤ ያበቡ ወይኖችም መዐዛቸውን ሰጡ፤ ፍቅሬ ሆይ፤ ተነሺና ነዪ፤ አንቺ የእኔ ቈንጆ፤ ከእኔ ጋር ነዪ።”

14አንቺ በገደል ዐለት ንቃቃት፣ በተራሮችም ባሉ መደበቂያ ስፍራዎች ውስጥ ያለሽ ርግቤ ሆይ! ፊትሽን አሳይኝ፤ ድምፅሽንም አሰሚኝ፤ ድምፅሽ ጣፋጭ፣ መልክሽም ውብ ነውና።

15የወይን ተክሉን ቦታ፣ በማበብ ላይ ያለውን የወይን ተክል ቦታችንን፣ የሚያጠፉትን ቀበሮዎች፣ እነዚያን ትንንሽ ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን።

16ውዴ የእኔ ነው፤ እኔም የእርሱ ነኝ፣ እርሱ መንጋውን በውብ አበቦች መካከል ያሰማራል።

17ጎሕ ከመቅደዱ በፊት፣ ጥላውም ሳይሸሽ፣ ውዴ ሆይ፤ ተመለስ፣ ሚዳቋን ምሰል፤ ወይም በወጣ ገባ ኰረብቶች እንዳለው የዋልያ ግልገል ሁን።

ትርጉሞች8 · 6