መኃልየ መኃልይ 1

AMHNIVአማርኛ17 ጥቅሶች2:46 አዳምጥ
አዳምጥ 2:46 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር።

2በከንፈሩ መሳም ይሳመኝ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ደስ ያሰኛልና።

3የሽቱህ መዐዛ ደስ ያሰኛል፤ ስምህ እንደሚፈስ ሽቱ ነው፤ ታዲያ ቈነጃጅት ቢወዱህ ምን ያስደንቃል

4ይዘኸኝ ሂድ፤ እንፍጠን፤ ንጉሡ ወደ ዕልፍኞቹ አምጥቶኛል። በአንተ ደስ ይለናል፤ ሐሤትም እናደርጋለን፤ ከወይን ጠጅ ይልቅ ፍቅርህን እንወድሳለን። አንተን እንደዚህ ማፍቀራቸው ትክክል ነው።

5እናንት የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፤ እኔ ጥቊር ነኝ፤ ይሁን እንጂ ውብ ነኝ፤ ጥቊረቴ እንደ ቄዳር ድንኳኖች፣ እንደ ሰሎሞን ቤተ መንግሥት መጋረጃዎችም ነው።

6ጥቊር ስለ ሆንሁ ትኵር ብላችሁ አትዩኝ፤ መልኬን ያጠቈረው ፀሓይ ነውና፤ የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ተቈጡኝ፤ የወይን ተክል ቦታዎችም ጠባቂ አደረጉኝ፤ የራሴን የወይን ተክል ቦታ ተውሁት።

7ውዴ ሆይ፤ መንጋህን የት እንደምታሰማራ፣ በቀትርም የት እንደምትመስጋቸው እባክህ ንገረኝ፤ በወዳጆችህ መንጎች ኋላ፣ ፊቷን ሸፍና እንደምትቅበዘበዝ ሴት ለምን ልሁን?

8አንቺ ከሴቶች ሁሉ ይበልጥ የተዋብሽ ሆይ፤ የማታውቂ ከሆነ፣ የበጎቹን ዱካ ተከተዪ፤ የፍየል ግልገሎችሽንም፣ በእረኞቹ ድንኳን አጠገብ አሰማሪ።

9ውዴ ሆይ፤ የፈርዖንን ሠረገሎች ከሚስቡ ፈረሶች መካከል፣ በአንዲቱ ባዝራ መሰልሁሽ።

10ጒንጮችሽ በጒትቻ፣ ዐንገትሽም በዕንቊ ሐብል አጊጠዋል።

11እኛም ባለ ብር ፈርጥ፣ የወርቅ ጒትቻ እናሠራልሻለን።

12ንጉሡ ማእዱ ላይ ሳለ፣ ሽቱዬ መዐዛውን ናኘው።

13ውዴ ለእኔ በጡቶቼ መካከል እንዳረፈ፣ በመቋጠሪያ እንዳለ ከርቤ ነው።

14ውዴ ለእኔ ከዓይንጋዲ የወይን ተክል ቦታ፣ እንደ መጣ የሄና አበባ ዕቅፍ ነው።

15ውዴ ሆይ፤ እንዴት ውብ ነሽ እንዴትስ ያለሽ ቈንጆ ነሽ ዐይኖችሽም እንደ ርግብ ዐይኖች ናቸው።

16አንተ ውዴ ሆይ፤ እንዴት ውብ ነህ እንዴትስ ታምራለህ ዐልጋችንም እንደ ለምለም ሣር ነው።

17የቤታችን ተሻካሚዎች ዝግባዎች፣ የጣራችን ማዋቀሪያዎችም ጥዶች ናቸው።

ትርጉሞች8 · 6