መጽሐፈ ምሳሌ 25

AMHEVGአማርኛ28 ጥቅሶች2:39 አዳምጥ
አዳምጥ 2:39 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1እነዚህም ደግሞ የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ሰዎች የቀዱአቸው የሰሎሞን ምሳሌዎች ናቸው።

2የእግዚአብሔር ክብር ነገርን መሰወር ነው፤ የነገሥታት ክብር ግን ነገርን መመርመር ነው።

3እንደ ሰማይ ከፍታ እንደ ምድርም ጥልቀት፡ የነገሥታት ልብ አይመረመርም።

4ከብር ዝገትን አስወግድ፥ ፈጽሞም ይጠራል።

5ከንጉሥ ፊት ኀጥኣንን አርቅ፥ ዙፋኑም በጽድቅ ትጸናለች።

6በንጉሥ ፊት አትመካ፥ በታላልቆችም ስፍራ አትቁም፤

7ዓይኖችህ ባዩት በመኰንን ፊት ከምትዋረድ፦ ወደዚህ ከፍ በል፡ ብትባል ይሻልሃልና።

8ባልንጀራህ ባሳፈረህ ጊዜ ኋላ እንዳትጸጸት፡ ለክርክር ፈጥነህ አትውጣ፤

9ክርክርህን ከባልንጀራህ ጋር ተከራከር፤ የሌላ ሰው ምሥጢር ግን አትግለጥ፥

10የሚሰማ እንዳይነቅፍህ፥ አንተንም ከማነወር ዝም እንዳይል።

11የወርቅ እንኮይ በብር ፃሕል ላይ፤ የጊዜው ቃል እንዲሁ ነው።

12የምትሰማን ጆሮ የሚዘልፍ ጠቢብ ሰው፡ እንደ ወርቅ ጉትቻ እንደሚያንጸባርቅም ዕንቍ እንዲሁ ነው።

13በመከር ወራት የውርጭ ጠል ደስ እንደሚያሰኝ፥ እንዲሁ የታመነ መልእክተኛ ለላኩት ነው፤ የጌቶቹን ነፍስ ያሳርፋልና።

14ስለ ስጦታው በሐሰት የሚመካ ሰው፡ ዝናብ እንደማይከተለው ደመና ነፋስም ነው።

15በትዕግሥት አለቃ ይለዝባል፥ የገራም ምላስ አጥንትን ይሰብራል።

16አጥብቀህ እንዳትጠግብ እንዳትተፋውም፡ ማር ባገኘህ ጊዜ የሚበቃህን ብላ።

17እንዳይሰለችህ እንዳይጠላህም፡ እግርህን ወደ ባልንጀራህ ቤት አታዘውትር።

18በባልንጀራው በሐሰት የሚመሰክር፡ እንደ መዶሻና እንደ ሰይፍ እንደ ተሳለም ፍላጻ ነው።

19ወስላታውን ሰው በመከራ ጊዜ መተማመን፡ እንደ ተሰበረ ጥርስና እንደ ሰለለ እግር ነው።

20ለሚያዝን ልብ ዝማሬ የሚዘምር፥ ለብርድ ቀን መጐናጸፊያውን እንደሚያስወግድ፡ በቍስልም ላይ እንደ መጻጻ እንዲሁ ነው።

21ጠላትህ ቢራብ እንጀራ አብላው፥ ቢጠማም ውኃ አጠጣው፤

22ፍም በራሱ ላይ ትሰበስባለህና፥ እግዚአብሔርም ዋጋህን ይመልስልሃልና።

23የሰሜን ነፋስ ወጀብ ያመጣል፤ ሐሜተኛ ምላስም የሰውን ፊት ያስቈጣል።

24ከጠበኛ ሴት ጋር በአንድ ቤት ከመቀመጥ፡ በሰገነት ማዕዘን መቀመጥ ይሻላል።

25የቀዘቀዘ ውኃ ለተጠማች ነፍስ ደስ እንደሚያሰኝ፥ ከሩቅ አገር የመጣ መልካም ምስራች እንዲሁ ነው።

26በኀጥእ ፊት የሚወድቅ ጻድቅ፡ እንደደፈረሰ ፈሳሽና እንደ ረከሰ ምንጭ ነው።

27ብዙ ማር መብላት መልካም አይደለም፤ እንዲሁም የራስን ክብር መፈላለግ አያስከብርም።

28ቅጥር እንደሌላት እንደ ፈረሰች ከተማ፥ መንፈሱን የማይከለክል ሰው እንዲሁ ነው።

ማብራሪያ

መጽሐፈ ምሳሌ ፳፭ (ምዕራፍ ሃያ አምስት)፳፭:፩-፫

እግዚአብሔር ምንም ነገር መመርመር አያስፈልገውም፤ ከእርሱ የተሰወረ ምንም ነገር የለምና። ነገር ግን ገዥዎች ነገሮችን መመርመር፣ የተሰወሩትን የጨለማ ሥራዎችም ወደ ብርሃን ማምጣት ክብራቸው ነው።

፬-፭

ልዑል ክፋትን መገደብና ሕዝቡንም ማነጽ መንግሥቱን ለመደገፍ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ነው።

፮-፯

ሃይማኖት ትህትናንና ራስን መካድን ታስተምረናለች። በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ የጌታን ክብር ያየ ሁሉ የራሱን ብቁ አለመሆን ይሰማዋል።

፰-፲

ጠብ ለመጀመር መቸኮል ወደ ችግር ያመራል። ጦርነት በመጨረሻ ማብቃት አለበት፤ እንዳይሆን መከላከልም የተሻለ ነው። በግል ጠብም እንዲሁ ነው፤ ጉዳዩን ለመፍታት የምትችለውን ሁሉ አድርግ።

፲፩-፲፪

በትክክል የተነገረ የምክር ወይም የገሠጻ ቃል፣ ጥሩ ፍሬ በብር ቅርጫቶች ውስጥ ይበልጥ እንደሚያምር ሁሉ፣ በተለይ ውብ ነው።

፲፫

ማንኛውንም ሥራ የተሰጠው / የታመነበት ሰው ዓላማ ምን መሆን እንዳለበት ተመልከት፤ ታማኝ መሆን ነው። ታማኝ አገልጋይ፣ የክርስቶስ መልእክተኛ፣ ለእኛም እንዲሁ ተቀባይነት ያለው መሆን አለበት።

፲፬

ያልነበረውን ነገር እንደተቀበለ ወይም እንደሰጠ የሚያስመስል እንደ ማለዳ ደመና ነው፤ ዝናብ የሚጠብቁትንም ተስፋ ያስቆርጣል።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6