መጽሐፈ ምሳሌ 22

AMHNIVአማርኛ29 ጥቅሶች3:38 አዳምጥ
አዳምጥ 3:38 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1መልካም ስም ከብዙ ብልጽግና ይመረጣል፤ መከበርም ከብርና ከወርቅ ይበልጣል።

2ባለጠጋና ድኻ የሚጋሩት ነገር፣ እግዚአብሔር የሁላቸውም ፈጣሪ መሆኑ ነው።

3አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል።

4ትሕትናና እግዚአብሔርን መፍራት፣ ሀብትን፣ ክብርንና ሕይወትን ያስገኛል።

5በክፉዎች መንገድ ላይ እሾህና ወጥመድ አለ፤ ነፍሱን የሚጠብቅ ግን ከእነዚህ ይርቃል።

6ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።

7ባለጠጋ ድኻን ይገዛል፤ ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው።

8ክፋትን የሚዘራ መከራን ያጭዳል፤ የቊጣውም በትር ይጠፋል።

9ቸር ሰው ራሱ ይባረካል፤ ምግቡን ከድኾች ጋር ይካፈላልና።

10ፌዘኛን አስወጣው፤ ጠብ ይወገዳል፤ ጥልና ስድብም ያከትማል።

11የልብ ንጽሕናን ለሚወድና ንግግሩም ሞገስ ላለው ሰው፣ ንጉሥ ወዳጁ ይሆናል።

12የእግዚአብሔር ዐይኖች ዕውቀትን ይጠብቃሉ፤ የማይታመኑትን ሰዎች ቃል ግን እርሱ ከንቱ ያደርጋል።

13ሰነፍ፣ “አንበሳ ውጪ አለ፤ መንገድ ላይ እገደላለሁ” ይላል።

14የአመንዝራ ሴት አፍ ጥልቅ ጕድጓድ ነው፤ እግዚአብሔር የተቈጣውም ይገባበታል።

15ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል፤ የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያርቅለታል።

16ሀብቱን ለማካበት ድኻን የሚበድል፣ ለባለጠጋም ስጦታ የሚያቀርብ፣ ሁለቱም ይደኸያሉ።

17የጠቢባንን ቃል ልብ ብለህ ስማ፤ ልብህም ወደ ትምህርቴ ያዘንብል፤

18በልብህ ስትጠብቃቸው፣ ሁሉም በከንፈሮችህ ላይ የተዘጋጁ ሲሆኑ ደስ ይላልና።

19ስለዚህ እምነትህ በእግዚአብሔር ላይ እንዲሆን፣ ዛሬ አንተን ራስህን አስተምርሃለሁ።

20የምክርና የዕውቀት ቃል የሆኑ፣ መልካም ትምህርቶችን አልጻፍሁልህምን?

21ለላከህ ተገቢውን መልስ ትሰጥ ዘንድ፣ እውነተኛውና የታመኑ ቃሎችን እንዳስተምርህ አይደለምን?

22ድኾች በመሆናቸው ብቻ ድኾችን አትበዝብዛቸው፤ ችግረኛውንም በአደባባይ አታንገላታው፤

23እግዚአብሔር ይፋረድላቸዋልና፤ የሚቀሟቸውንም ይቀማቸዋል።

24ከግልፍተኛ ጋር ወዳጅ አትሁን፤ በቀላሉ ቱግ ከሚልም ሰው ጋር አትወዳጅ፤

25አለበለዚያ መንገዱን ትማራለህ፤ ራስህም ትጠመድበታለህ።

26በዋስትና ቃል እጅ አትምታ፤ ለብድር ተያዥ አትሁን፤

27የምትከፍለው ካጣህ፣ የምትተኛበት ዐልጋ ከሥርህ ይወሰድብሃል።

28የቀድሞ አባቶችህ ያስቀመጡትን፣ የጥንቱን የወሰን ምልክት አታፋልስ።

29በሙያው ሥልጡን የሆነውን ሰው አይተሃልን? በነገሥታት ዘንድ ባለሟል ይሆናል፤ አልባሌ ሰዎችን አያገለግልም።

ማብራሪያ

የሚከተለው የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ወደ አማርኛ ተተርጉሟል፦

22:1 ታላቅ ሀብትን ከመሰብሰብ ወይም ከመጨመር ይልቅ መልካም ስምን የምናገኝበትንና የምንጠብቅበትን ነገር ለማድረግ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። 2. መለኮታዊ አድራጎት (አቅርቦት) አንዳንዶች ሀብታም ሌሎች ደግሞ ድሆች እንዲሆኑ ደንግጓል፤ ሁሉም ግን በእግዚአብሔር ፊት በደለኛ ናቸው፤ በእግዚአብሔር ጸጋ ዙፋንም ዘንድ ድሆች እንደ ሀብታሞች ሁሉ ተቀባይነት አላቸው። 3. እምነት በኃጢአተኞች ላይ የሚመጣውን ክፉ ነገር አስቀድሞ ያያል፤ ከዐውሎ ነፋስ አስተማማኝ መጠጊያ ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስም ይመለከታል። 4. እግዚአብሔርን መፍራት ባለበት ቦታ ትሕትና ይኖራል። በእርሱም ብዙ የሚገኝ ነገር አለ፤ መንፈሳዊ ሀብትና በመጨረሻም የዘላለም ሕይወት። 5. የኃጢአት መንገድ የሚያስጨንቅና አደገኛ ነው። የተግባር መንገድ ግን አስተማማኝና ቀላል ነው። 6. ልጆችን ማሰልጠን ያለብን የራሳቸው በጠማማ ልባቸው መንገድ ሳይሆን ሊሄዱበት በሚገባው መንገድ ነው። እነርሱን የምትወዱ ከሆነ እንዲሄዱ የምትሹበት መንገድ ነው።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6