የማቴዎስ ወንጌል 1

AMHNIVአማርኛ25 ጥቅሶች3:57 አዳምጥ
አዳምጥ 3:57 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1የዳዊት ልጅ፣ የአብርሃም ልጅ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ሐረግ የሚከተለው ነው፤

2አብርሃም ይስሐቅን ወለደ፤ ይስሐቅ ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብ ይሁዳንና ወንድሞቹን ወለደ፤

3ይሁዳ ከትዕማር ፋሬስንና ዛራን ወለደ፤ ፋሬስ ኤስሮምን ወለደ፤ ኤስሮምም አራምን ወለደ፤

4አራም አሚናዳብን ወለደ፤ አሚናዳብ ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶን ሰልሞንን ወለደ፤

5ሰልሞን ቦዔዝን ከረዓብ ወለደ፤ ቦዔዝ ከሩት ኢዮቤድን ወለደ፤ ኢዮቤድ እሴይን ወለደ፤

6እሴይ ንጉሥ ዳዊትን ወለደ። ዳዊት የኦርዮ ሚስት ከነበረችው ሰሎሞንን ወለደ፤

7ሰሎሞን ሮብዓምን ወለደ፤ ሮብዓም አቢያን ወለደ፤ አቢያም አሣፍን ወለደ፤

8አሣፍ ኢዮሣፍጥን ወለደ፤ ኢዮሣፍጥ ኢዮሆራምን ወለደ፤ ኢዮሆራም ዖዝያንን ወለደ፤

9ዖዝያን ኢዮአታምን ወለደ፤ ኢዮአታም አካዝን ወለደ፤ አካዝ ሕዝቅያስን ወለደ፤

10ሕዝቅያስ ምናሴን ወለደ፤ ምናሴ አሞንን ወለደ፤ አሞንም ኢዮስያስን ወለደ፤

11ኢዮስያስ በባቢሎን ምርኮ ጊዜ፣ ኢኮንያንንና ወንድሞቹን ወለደ፤

12ከባቢሎን ምርኮ በኋላ፣ ኢኮንያን ሰላትያልን ወለደ፤ ሰላትያልም ዘሩባቤልን ወለደ፤

13ዘሩባቤል አብዩድን ወለደ፤ አብዩድ ኤልያቄምን ወለደ፤ ኤልያቄም አዛርን ወለደ፤

14አዛር ሳዶቅን ወለደ፤ ሳዶቅ አኪምን ወለደ፤ አኪምም ኤልዩድን ወለደ፤

15ኤልዩድ አልዓዛርን ወለደ፤ አልዓዛር ማታንን ወለደ፤ ማታን ያዕቆብን ወለደ፤

16ያዕቆብ ዮሴፍን ወለደ፤ ዮሴፍም የኢየሱስ ክርስቶስ እናት የማርያም እጮኛ ነበር።

17እንግዲህ ከአብርሃም እስከ ዳዊት ዐሥራ አራት ትውልድ፣ ከዳዊት እስከ ባቢሎን ምርኮ ዐሥራ አራት ትውልድ፣ ከባቢሎን ምርኮ እስከ ክርስቶስ ልደት ዐሥራ አራት ትውልድ ይሆናል።

18የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ታሪክ እንዲህ ነው፤ እናቱ ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ሳይገናኙ፣ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ ተገኘች።

19እጮኛዋ ዮሴፍ ጻድቅ ሰው ስለ ነበርና ማርያምን በሰው ፊት ሊያጋልጣት ስላልፈለገ በስውር ሊተዋት ወሰነ።

20በዚህ ሐሳብ ሳለ፣ የጌታ መልአክ በሕልም ተገለጠለት፤ እንዲህም አለው፤ “የዳዊት ልጅ ዮሴፍ ሆይ፤ እጮኛህን ማርያምን ወደ ቤትህ ለመውሰድ አትፍራ፤ የፀነሰችው በመንፈስ ቅዱስ ነውና።

21ወንድ ልጅ ትወልዳለች፤ ስሙንም ኢየሱስ ብለህ ትጠራዋለህ፤ ሕዝቡን ከኀጢአታቸው ያድናቸዋልና።”

22ጌታ በነቢዩ እንዲህ ሲል የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆነ፤

23“እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል፤” ትርጕሙም፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ማለት ነው።

24ዮሴፍም ከእንቅልፉ ነቃ፤ ከዚያም የጌታ መልአክ እንዳዘዘው ማርያምን ወደ ቤቱ ወሰዳት።

25ይሁን እንጂ የበኵር ልጇን እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም፤ የተወለደውንም ሕፃን፣ “ኢየሱስ” ብሎ ጠራው።

ማብራሪያ

፩፡፩-፲፯ የጌታችንን የዚህን የዘር ሐረግ በተመለከተ፣ ዋና ዓላማውን እንመልከት። እሱም አላስፈላጊ የዘር ሐረግ አይደለም። እንደ ብዙዎቹ የታላላቅ ሰዎች የዘር ሐረግ፣ የከንቱ ክብር መኩሪያም አይደለም። ጌታችን ኢየሱስ መሲሑ ከሚነሣበት ነገድና ቤተሰብ እንደሆነ ያረጋግጣል። የበረከት ተስፋ ለአብርሃምና ለዘሩ ተሰጥቶ ነበር፤ የአገዛዝም (የንግሥና) ተስፋ ደግሞ ለዳዊትና ለዘሩ። ክርስቶስ ከእርሱ እንደሚወለድ ለአብርሃም ቃል ተገብቶለት ነበር (ዘፍ ፲፪፡፫፤ ፳፪፡፲፰)፤ ከዳዊትም እንደሚወለድ ቃል ተገብቶለት ነበር (፪ኛ ሳሙ ፯፡፲፪፤ መዝ ፹፱፡፫፣ ወዘተ. ፻፴፪፡፲፩)። ስለዚህም ኢየሱስ የዳዊት ልጅና የአብርሃም ልጅ ካልሆነ፣ እርሱ መሲሕ አይደለም። አሁን ይህ ከታወቁ መዝገቦች ተረጋግጧል። የእግዚአብሔር ልጅ ተፈጥሮአችንን ሊወስድ በፈቀደ ጊዜ፣ በወደቅነውና በችጋራችን ሁኔታ ውስጥ ወደ እኛ ቀረበ፤ ነገር ግን እርሱ ከኃጢአት ፍጹም ነጻ ነበር። የዘር ሐረጉን ስሞች ስናነብም፣ የክብር ጌታ የሰውን ዘር ለማዳን ምን ያህል ዝቅ እንዳለ ልንረሳ አይገባም።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6