ትንቢተ ሚልክያ 2

AMHNIVአማርኛ17 ጥቅሶች3:58 አዳምጥ
አዳምጥ 3:58 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1“አሁንም ካህናት ሆይ፤ ይህ ማስጠንቀቂያ ለእናንተ የተሰጠ ነው፤

2ባትሰሙ፣ ልባችሁንም ስሜን ለማክበር ባታዘጋጁ፣ ርግማን እሰድባችኋለሁ፤ በረከታችሁንም ወደ መርገም እለውጠዋለሁ፤ ልታከብሩኝ ልባችሁን አላዘጋጃችሁምና ረግሜዋለሁ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

3“ዘራችሁን እገሥጻለሁ፤ የመሥዋታችሁን ፋንድያ በፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ እናንተም ከእርሱ ጋር ትወገዳላችሁ፤

4ከሌዊ ጋር የገባሁት ኪዳን ይጸና ዘንድ፣ ይህን ማስጠንቀቂያ የላክሁት እኔ መሆኔንም ታውቃላችሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

5“ከእርሱ ጋር የገባሁት ኪዳን የሕይወትና የሰላም ኪዳን ነበር፤ እነርሱንም ሰጠሁት፤ ይህም ክብርን አመጣ፤ እርሱም አከበረኝ፤ ስሜንም በመፍራትም ጸና።

6እውነተኛ ትምህርት በአፉ ነበር፤ ምንም ዐይነት የሐሰት ነገር በአንደበቱ አልተገኘም፤ ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ተራመደ፤ ብዙዎችንም ከኀጢአት መለሰ።

7“ካህኑ የሁሉ ገዥ፣ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ስለ ሆነ ከንፈሮቹ ዕውቀትን ሊጠብቁ፣ ሰዎችም ከአንደበቱ ትምህርትን ሊፈልጉ ይገባል፤

8እናንተ ግን ከመንገዱ ወጥታችኋል፤ በትምህርታችሁም ብዙዎች እንዲሰናከሉ አድርጋችኋል፤ የሌዊንም ኪዳን አፍርሳችኋል” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።

9“ስለዚህ በመንገዴ ስላልሄዳችሁና በትምህርታችሁም አድልዎ ስላደረጋችሁ፣ በሰዎች ሁሉ ፊት እንድትናቁና እንድትዋረዱ አድርጌአችኋለሁ።”

10ሁላችን አንድ አባት ያለን አይደለንምን? የፈጠረንስ አንድ አምላክ አይደለምን? ታዲያ እርስ በርሳችን ታማኝነት በማጒደል የአባቶቻችንን ኪዳን ለምን እናረክሳለን?

11ይሁዳ አልታመነም፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌምም አስጸያፊ ነገር ተፈጽሞአል፤ ይሁዳ የባዕድ አምላክ ሴት ልጅ በማግባት እግዚአብሔር የሚወደውን መቅደስ አርክሶአል።

12ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ቢሆን፣ ለእግዚአብሔር ጸባኦት ቊርባን ቢያመጣም እንኳ፣ እግዚአብሔር ከያዕቆብ ድንኳን ያስወግደው።

13ሌላው የምታደርጉት ነገር ደግሞ፣ የእግዚአብሔርን መሠዊያ በእንባ ታጥለቀልቃላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲያ ቊርባናችሁን ስለ ማይመለከትና በደስታም ከእጃችሁ ስለማይቀበል ታለቅሳላችሁ፤ ትጮኻ ላችሁም።

14እናንተም፣ “ለምን ይህ ሆነ?” ብላችሁ ትጠይቃላችሁ። ይህ የሆነው የትዳር ጓደኛህን፣ አጋርህንና የቃል ኪዳን ሚስትህን፣ አታለሃታልና እግዚአብሔር በአንተና በወጣትነት ሚስትህ መካከል ላለው ቃል ኪዳን ምስክር ስለ ሆነ ነው።

15እግዚአብሔር አንድ አላደረጋቸውምን? በሥጋም በመንፈስም የእርሱ ናቸው። ለምን አንድ አደረጋቸው? ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለውን ዘር ይፈልግ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ከወጣትነት ሚስታችሁም ጋር ያላችሁን ታማኝነት አታጓድሉ።

16“ፍችን እጠላለሁ” ይላል የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር፤ ልብሱን በግፍ ድርጊት የሚሸፍነውንም ሰው እጠላለሁ” ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት። ስለዚህ በመንፈሳችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤ ታማኝነታችሁም አይጓደል።

17እግዚአብሔርን በቃላችሁ አታክታችሁታል። እናንተም፣ “ያታከትነው እንዴት ነው?” ትላላችሁ? “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት መልካም ነው፤ እርሱም በክፉዎች ደስ ይለዋል” ወይም “የፍትሕ አምላክ ወዴት ነው?” በማለታችሁ ነው።

ማብራሪያ

2:1-9 እዚህ ስለ ክህነት ቃል ኪዳን የተነገረው ነገር፣ እንደ መንፈሳዊ ካህናት ከሁሉም አማኞች ጋር ለተደረገው የጸጋ ቃል ኪዳንም እውነት ነው። እርሱም የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነው። በዚህ ዓለምም ሆነ በሚመጣው ዓለም ለሁሉም አማኞች ሁሉንም ደስታ ያረጋግጥላቸዋል። የእግዚአብሔር አገልጋዮች መልእክተኞቹ ሆነው መሠራት ክብር ነው። የካህኑ ከንፈሮች እውቀትን ከሕዝቡ ሊከለክሉ አይገባም፤ ይልቁንም ለእነርሱ ሊጠብቁት ይገባል። ሁሉም ሕዝብ የጌታን ፈቃድ ማወቅ ያገባዋል። የተጻፈውን ቃል ብቻ ማማከር የለብንም፤ ይልቁንም የነፍሳችንን ጉዳይ በተመለከተ ከእግዚአብሔር መልእክተኞች ትምህርትና ምክርን መፈለግ አለብን። አገልጋዮች ኃጢአተኞችን ለመመለስ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው፤ ከእስራኤላውያን ተብለው በሚጠሩትም መካከል እንኳ ከበደል ሊመለሱ የሚገባቸው ብዙዎች አሉ። ጤናማ ትምህርትን የሚሰብኩ፣ እናም እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት ቅዱስ ሕይወትን የሚኖሩ እነዚያ አገልጋዮች ብቻ ናቸው ሰዎችን ከኃጢአት ሊመልሱ የሚችሉት። ብዙዎች ከዚህ መንገድ ዞረዋል፤ በዚህም ምክንያት ሕዝቡን አሳስተዋል። ከእግዚአብሔር ጋር በሰላምና በጽድቅ የሚሄዱ፣ ሌሎችንም ከኃጢአት የሚመልሱ እግዚአብሔርን ያከብራሉ።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6