ትንቢተ ሚልክያ 1

AMHEVGአማርኛ14 ጥቅሶች3:10 አዳምጥ
አዳምጥ 3:10 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በሚልክያስ እጅ ለእስራኤል የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም ይህ ነው።

2“ወድጃችኋለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር፤¶ እናንተ ግን፦ “በምን ወደድኸን?” ብላችኋል።¶ “ዔሳው የያዕቆብ ወንድም አልነበረምን?” ይላል እግዚአብሔር፤ “ያዕቆብንም ወደድሁ፥

3ዔሳውንም ጠላሁ፤ ተራሮቹንም በረሃ አደረግኋቸው፥ ርስቱንም ለምድረ በዳ ቀበሮች አሳልፌ ሰጠኋቸው።”

4ኤዶምያስ፦ “እኛ ፈርሰናል፥ ነገር ግን የፈረሰውን መልሰን እንሠራለን፡” ቢል፥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እነርሱ ይሠራሉ፥ እኔ ግን አፈርሳለሁ፤ በሰዎችም ዘንድ፦ ‘የበደል ዳርቻና እግዚአብሔር ለዘላለም የተቈጣው ሕዝብ፡’ ይባላል።

5ዓይኖቻችሁም ያያሉ፥ እናንተም፦ ‘እግዚአብሔር ከእስራኤል ዳርቻ ወዲያ ታላቅ ይሁን፡’ ትላላችሁ።”

6“እናንተ ስሜን የምታቃልሉ ካህናት ሆይ፥ ልጅ አባቱን፥ ባሪያም ጌታውን ያከብራል፤ እኔስ አባት ከሆንሁ ክብሬ ወዴት አለ? ጌታስ ከሆንሁ መፈራቴ ወዴት አለ?” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።¶ “እናንተም፦ ስምህን ያቃለልን በምንድር ነው?” ብላችኋል።

7“በመሠዊያዬ ላይ ርኩስ እንጀራ ታቀርባላችሁ።”¶ እናንተም፦ “ያረከስንህ በምንድር ነው?” ብላችኋል።¶ “የእግዚአብሔር ገበታ የተነቀፈ ነው፡” በማለታችሁ ነው።

8“ዕውር መሥዋዕትንም ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? አንካሳውንና የታመመውን ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? ያንን ለአለቃህ አቅርብ፤ በውኑ በአንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ፊትህን ይቀበላልን?” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

9“አሁንም ጸጋን ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔርን ለምኑ፤ ይህ ከእጃችሁ የተሰጠ ሲሆን ከቶ ፊታችሁን ይቀበላልን?” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

10“በመሠዊያዬ ላይ እሳትን በከንቱ እንዳታቃጥሉ ከእናንተ ዘንድ ደጅ የሚዘጋ ሰው ምነው በተገኘ! በእናንተ ደስ አይለኝም፥ ቍርባንንም ከእጃችሁ አልቀበልም፥” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

11“ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፤ በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ፤ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና፥” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።

12እናንተ ግን፦ “የእግዚአብሔር ገበታ ርኩስ ነው፤ ፍሬውና መብሉም የተናቀ ነው፡” በማለታችሁ አስነቀፋችሁት።

13“እናንተ፦ እነሆ፥ ይህ ድካም ነው፡ ብላችሁ ጢቅ አላችሁበት፥” ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤¶ “በቅሚያ የያዛችሁትንም አንካሳውንም የታመመውንም አቅርባችኋል፤ እንዲሁ ቍርባንን ታመጣላችሁ፤ በውኑ ከእጃችሁ ይህን ልቀበለውን?” ይላል እግዚአብሔር።

14“እኔ ታላቅ ንጉሥ ነኝና፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ስሜም በአሕዛብ ዘንድ የተፈራ ነውና በመንጋው ውስጥ ተባት እያለው ለጌታ ተስሎ ነውረኛውን የሚሠዋ ሸንጋይ ሰው ርጉም ይሁን።”

ማብራሪያ

1:1-5 ሁሉም ጥቅሞች፣ ከውጫዊ ሁኔታዎች አንጻርም ሆነ ከመንፈሳዊ መብቶች አንጻር፣ አንዱን ከሌላው ከሚለየው ከእግዚአብሔር ነጻ ፍቅር የመጡ ናቸው። ኃጢአተኞች የሚሰማቸውና የሚፈሩት ክፋቶች ሁሉ ለበደላቸው የሚገባቸው ቅጣት ሲሆኑ፣ ተስፋቸውና መጽናናታቸው ሁሉ ግን ከጌታ ከማይገባት ምሕረት የመጡ ናቸው። ሕዝቡን የመረጣቸው ቅዱሳን እንዲሆኑ ነው። እርሱን የምንወደው ከሆነ እርሱ አስቀድሞ ስለወደደን ነው። ሆኖም ግን ሁላችንም የእግዚአብሔርን ምሕረት የማቃለል እንዲሁም የራሳችንን በደል የማስተባበል ዝንባሌ አለብን።

1:6-14

እዚህ በካህናቱ ላይ የተሰነዘረውን ነቀፋ እያንዳንዳችን በራሳችን ላይ መውሰድ እንችላለን። ከአብና ከጌታችን ጋር ያለን ግንኙነት እሱን እንድንፈራና እንድናከብረው በጽኑ ያስገድደናል። እነርሱ ግን በንቀት የተሞሉ ስለነበሩ ተግሣጽን ያፌዙበት ነበር። ኃጢአተኞች የኅሊናቸውን ግሳጼ ለማምከን በመሞከር ራሳቸውን ያጠፋሉ። የተቀደሱ ሥርዓቶችን በግድየለሽነት ችላ ብለው የሚኖሩ፣ በአክብሮት የማይካፈሉ፣ ያለ ምንም አሳቢነትም ከእነርሱ የሚለዩ፣ በተግባር “የእግዚአብሔር ማዕድ የተናቀ ነው” ይላሉ።

በድርጊታቸው የእግዚአብሔርን ስም ንቀው ነበር።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6