የሉቃስ ወንጌል 22

AMHNIVአማርኛ71 ጥቅሶች9:29 አዳምጥ
አዳምጥ 9:29 · መደበኛ · አስደናቂ በBiblight ይክፈቱ

1በዚህ ጊዜ ፋሲካ የተባለው የቂጣ በዓል ተቃርቦ ነበር።

2የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም ሕዝቡን ይፈሩ ስለ ነበር፣ እንዴት አድርገው ኢየሱስን እንደሚያስወግዱት መንገድ ይፈልጉ ነበር።

3ሰይጣንም ከዐሥራ ሁለቱ ጋር በተቈጠረው የአስቆሮቱ ይሁዳ በተባለው ገባበት፤

4ይሁዳም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ቤተ መቅደሱ ሹሞች ሄዶ ኢየሱስን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጣቸው ተነጋገረ።

5እነርሱም በዚህ ደስ ተሰኝተው፣ ገንዘብ ሊሰጡት ተዋዋሉ።

6እርሱም በነገሩ ተስማማ፤ አሳልፎ ሊሰጣቸውም ሕዝብ የማይገኝበትን ምቹ ጊዜ ይጠብቅ ጀመር።

7ከዚህ በኋላ የፋሲካ በግ የሚታረድበት የቂጣ በዓል ደረሰ።

8ኢየሱስም፣ “የፋሲካን እራት እንድንበላ ሄዳችሁ አዘጋጁልን” ብሎ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው።

9እነርሱም፣ “የት እንድናሰናዳ ትፈልጋለህ?” አሉት።

10እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፤ ወደ ከተማ ስትገቡ የውሃ እንስራ የተሸከመ ሰው ያገኛችኋል፤ እርሱ ወደሚገባበት ቤት ድረስ ተከተሉት፤

11ለቤቱም ባለቤት፣ ‘መምህሩ፣ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር የፋሲካን እራት የምበላበት የእንግዳ ክፍል ወዴት ነው? ይልሃል’ በሉት።

12እርሱም በሰገነት ላይ ያለውን ተነጥፎ የተዘጋጀ ሰፊ አዳራሽ ያሳያችኋል፤ በዚያም አሰናዱልን።”

13እነርሱም ሄደው ልክ ኢየሱስ እንደ ነገራቸው ሆኖ አገኙት፤ ፋሲካንም በዚያ አዘጋጁ።

14ሰዓቱም በደረሰ ጊዜ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር በማእድ ተቀመጠ፤

15እንዲህም አላቸው፤ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን ፋሲካ አብሬያችሁ ለመብላት በጣም ስመኝ ነበር፤

16እላችኋለሁ፤ በእግዚአብሔር መንግሥት የዚህ ትርጒም እስኪፈጸም ድረስ ይህን ፋሲካ ዳግመኛ አልበላም።”

17ጽዋውን ተቀብሎ ካመሰገነ በኋላ እንዲህ አላቸው፤ “እንካችሁ፤ ሁላችሁ ከዚህ ተካፈሉ፤

18እላችኋለሁና፤ ከአሁን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት እስከምትመጣ ድረስ፣ ከዚህ ወይን ፍሬ አልጠጣም።”

19እንጀራንም አንሥቶ አመሰገነ፤ ቈርሶም ሰጣቸውና፣ “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው፤ ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ።

20እንደዚሁም ከእራት በኋላ ጽዋውን አንሥቶ እንዲህ አለ፤ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው።

21ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ በማእድ ከእኔ ጋር ናት።

22የሰው ልጅስ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሄዳል፤ ነገር ግን እርሱን አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ወዮለት።”

23እነርሱም ከመካከላቸው ይህን የሚያደርግ ማን ሊሆን እንደሚችል እርስ በርሳቸው ይጠያየቁ ጀመር።

24ደግሞም ከመካከላቸው ማን እንደሚበልጥ በእነርሱ ዘንድ ክርክር ተነሣ።

25ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ነገሥታት ሕዝቦቻቸውን በኀይል ይገዛሉ፤ በእነርሱ ላይ ሥልጣን ያላቸውም በጎ አድራጊዎች ተብለው ይጠራሉ።

26በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይሁን፤ ይልቁን ከእናንተ ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ፣ ገዥ የሆነም እንደ አገልጋይ ይሁን።

27ለመሆኑ፣ በማእድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያስተናግድ ማን ይበልጣል? በማእድ የተቀመጠው አይደለምን? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አንድ አገልጋይ ነው።

28እናንተም ሳትለዩኝ በመከራዬ ጊዜ በአጠገቤ የቆማችሁ ናችሁ፤

29አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔም ደግሞ በመንግሥቴ እሾማችኋለሁ፤

30ይኸውም በመንግሥቴ ከማእዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ ደግሞም በዙፋን ላይ ተቀምጣችሁ በዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገድ ላይ እንድትፈርዱ ነው።”

31ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፣ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤

32እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።”

33ስምዖንም፣ “ጌታ ሆይ፤ እኔ ከአንተ ጋር ወህኒ ለመውረድም፣ ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” አለው።

34ኢየሱስም፣ “ጴጥሮስ ሆይ፤ ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ፣ አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ እልሃለሁ” አለው።

35ከዚያም ኢየሱስ፣ “ያለ ኰረጆ፣ ያለ ከረጢትና ያለ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ የጐደለባችሁ ነገር ነበርን?” ብሎ ጠየቃቸው። እነርሱም፣ “ምንም አልጐደለብንም” አሉ።

36እርሱም እንዲህ አላቸው፤ “አሁን ግን ኰረጆም፣ ከረጢትም ያለው ሰው ይያዝ፤ ሰይፍ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ይግዛ።

37እላችኋለሁና፤ ‘ከዐመፀኞች ጋር ተቈጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ መፈጸም አለበት፤ ስለ እኔ የተጻፈው ፍጻሜው በርግጥ ደርሶአል።”

38ደቀ መዛሙርቱም፣ “ጌታ ሆይ፤ እነሆ፤ ሁለት ሰይፎች እዚህ አሉ” አሉት። እርሱም፣ “ይበቃል” አላቸው።

39ኢየሱስ እንደ ልማዱ ወጥቶ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።

40እዚያም በደረሱ ጊዜ፣ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ” አላቸው።

41ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ ያህል ርቆ ተንበርክኮ ጸለየ፤

42እንዲህም አለ፤ “አባት ሆይ፤ ፈቃድህ ከሆነ፣ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።”

43መልአክም ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው።

44እጅግ ተጨንቆም በብርቱ ይጸልይ ነበር፤ ላቡም እንደ ደም ነጠብጣብ ወደ ምድር ይፈስ ነበር።

45ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣ፤ እነርሱም ከሐዘን የተነሣ ተኝተው አገኛቸውና፣

46“ለምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ” አላቸው።

47እርሱም ገና እየተነጋገረ ሳለ፣ ብዙ ሰዎች መጡ፤ ከዐሥራ ሁለቱ አንዱ ይሁዳ የተባለውም ሰው ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ተጠጋ።

48ኢየሱስ ግን፣ “ይሁዳ ሆይ፤ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህን?” አለው።

49በኢየሱስ ዙሪያ የነበሩ ሰዎችም ሁኔታውን ተመልክተው “ጌታ ሆይ፤ በሰይፍ እንምታቸውን?” አሉት።

50ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን አገልጋይ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው።

51ኢየሱስ ግን፣ “ተው! እዚህ ድረስም ፍቀዱ” አለ፤ የሰውየውንም ጆሮ ዳስሶ ፈወሰው።

52ከዚያም ኢየሱስ ሊይዙት የመጡትን የካህናት አለቆች፣ የቤተ መቅደስ ሹሞችና ሽማግሌዎችን እንዲህ አላቸው፤ “ወንበዴ እንደሚይዝ ሰው፣ ሰይፍና ቈመጥ ይዛችሁ ወጣችሁን?

53በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እጃችሁን አላነሣችሁብኝም፤ ይህ ግን ጨለማ የነገሠበት ጊዜያችሁ ነው።”

54ከዚህ በኋላ ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤ ወደ ሊቀ ካህናቱም ግቢ አስገቡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተለው ነበር።

55ሰዎቹ በሊቀ ካህናቱ ግቢ ውስጥ እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳለ፣ ጴጥሮስም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ነበር።

56አንዲት የቤት ሠራተኛም ጴጥሮስ እሳቱ አጠገብ ተቀምጦ አየችውና ትኵር ብላ በመመልከት፣ “ይህ ሰው ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ” አለች።

57እርሱ ግን፣ “አንቺ ሴት፤ እኔ ዐላውቀውም” ብሎ ካደ።

58ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ሌላ ሰው አይቶት፣ “አንተም ደግሞ ከእነርሱ አንዱ ነህ” አለው። ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ እኔ አይደለሁም” አለ።

59አንድ ሰዓት ያህል ቈይቶም፣ ሌላ ሰው በርግጠኝነት፣ “ይህ ሰው ገሊላዊ ስለ ሆነ ያለ ጥርጥር ከእርሱ ጋር ነበረ” አለ።

60ጴጥሮስ ግን፣ “አንተ ሰው፤ የምትለውን እኔ አላውቅም” አለ፤ ይህንም ተናግሮ ገና ሳይጨርስ ዶሮ ጮኸ።

61ጌታም መለስ ብሎ ጴጥሮስን ተመለከተው፤ ጴጥሮስም፣ “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ጌታ የተናገረው ቃል ትዝ አለው።

62ጴጥሮስም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።

63ኢየሱስን አስረው ይጠብቁት የነበሩት ሰዎችም ያፌዙበትና ይመቱት ጀመር፤

64ዐይኑንም ሸፍነው፣ “እስቲ ትንቢት ተናገር፤ የመታህ ማነው? እያሉ ይጠይቁት ነበር።

65ሌላም ብዙ የስድብ ቃል እየተናገሩ ያቃልሉት ነበር።

66በነጋም ጊዜ፣ የሕዝብ ሽማግሌዎች፣ የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ተሰበሰቡ፤ ኢየሱስንም በሸንጎአቸው ፊት አቀረቡት።

67እነርሱም፣ “አንተ ክርስቶስ ነህን? እስቲ ንገረን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፤ “ብነግራችሁ አታምኑኝም፤

68ብጠይቃችሁም አትመልሱም።

69ነገር ግን ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ኀይል ቀኝ ይቀመጣል።”

70በዚህ ጊዜ ሁሉም፣ “ታዲያ፣ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህን?” አሉት። እርሱም፣ “መሆኔን እኮ እናንተው ተናገራችሁት” አላቸው።

71እነርሱም፣ “ከእንግዲህ ሌላ ምስክር ምን ያስፈልገናል? ራሳችን ከገዛ አንደበቱ ሰምተናልና” አሉ።

ማብራሪያ

22:1-6 ክርስቶስ ሰውን ሁሉ ያውቅ ነበር፤ ይሁዳን ደቀ መዝሙር አድርጎ በመውሰዱም ጥበብ የተሞላበትና ቅዱስ ዓላማ ነበረው። ክርስቶስን ይህን ያህል ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው እንዴት አሳልፎ ሊሰጠው እንደቻለ እዚህ ተነግሮናል፤ ሰይጣን በይሁዳ ውስጥ ገባ። ለክርስቶስ መንግሥት የበለጠ ጉዳት የሚደርሰው በግልጽ በሚታዩ ጠላቶቹ ኃይል ነው ወይስ በሐሰተኛ ወዳጆቹ ክህደት ለማለት ይከብዳል፤ ነገር ግን የኋለኞቹ ባይኖሩ ኖሮ ጠላቶቹ ይህን ያህል ክፋት መፈጸም አይችሉም ነበር።

፳፪፥፯-፲፰ ክርስቶስ የሕግን ሥርዓቶች፣ በተለይም የፋሲካን ሥርዓት፣ የእርሱን የወንጌል ሥርዓቶች እንድንጠብቅ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የጌታን ኅብረት እንድንጠብቅ ሊያስተምረን ጠበቀ። በክርስቶስ ቃል የሚተማመኑ ሰዎች ተስፋ መቁረጥን መፍራት አያስፈልጋቸውም። እንደተሰጣቸው ትእዛዝ፣ ደቀ መዛሙርቱ ለፋሲካ ሁሉን ነገር አዘጋጁ። ኢየሱስ ይህን ፋሲካ በደስታ ተቀበለው። እርሱ መከራው እንደሚከተል ቢያውቅም እንኳ፣ የአባቱን ክብርና የሰውን ቤዛነት ለማስገኘት ሲል ወደደው። ከሁሉም ፋሲካዎች ተሰናበተ፤ ይህም የመሥዋዕታዊውን ሕግ ሥርዓቶች ሁሉ እንደሚያስቀር ሲያሳይ ነበር፤ ከእነዚህም ውስጥ ፋሲካ ከጥንቶቹና ከዋነኞቹ አንዱ ነበር። ያ ጥላ ተወገደ፣ ምክንያቱም አሁን በእግዚአብሔር መንግሥት እውነተኛው ነገር መጥቶአል።

22:19,20 የጌታ እራት፣ አስቀድሞ የመጣውና በመሞት ያዳነን የክርስቶስ ምልክት ወይም መታሰቢያ ነው። ሞቱ በዚያ ስርዓት ውስጥ በልዩ ሁኔታ ከፊታችን ቀርቧል፤ በእርሱም ሞቱን እናስታውሳለን። የክርስቶስ አካል ለእኛ መሥዋዕት ሆኖ መሰበሩ፣ እንጀራው በመሰበሩ አማካኝነት ወደ ትዝታችን ይቀርባል። ለነፍስ ከክርስቶስ የኃጢአት ቤዛነት ትምህርት እንዲሁም በዚያ ቤዛነት ድርሻ እንዳለን ከመተማመን የበለጠ ገንቢና የሚያረካ ነገር የለም። ስለዚህ ይህንን የምናደርገው ለእኛ የሞተልን ጊዜ ያደረገልንን በማሰብ ነው፤ እንዲሁም እኛ ራሳችንን ከእርሱ ጋር በዘላለም ቃል ኪዳን በማያያዝ የምናደርገውን ለማስታወስ ነው። ቤዛነት የተፈጸመበት የክርስቶስ ደም መፍሰስ፣ በጽዋው ውስጥ ባለው ወይን ይወከላል።

22:21-38

በዓለም ታላቅ የመሆን ምኞት፣ የባሪያን መልክ የያዘውንና እስከ መስቀል ሞት ራሱን ያዋረደውን ኢየሱስን ለሚከተል ሰው ባሕርይ ምን ያህል የማይገባ ነው! ወደ ዘላለም ደስታ በሚወስደው መንገድ፣ በሰይጣን እንድንጠቃና እንድንነፍግ መጠበቅ አለብን። ሊያጠፋን ባይችል፣ ሊያሳፍረን ወይም ሊያሰቃየን ይሞክራል። ክርስቶስን እንደሚከተል በይፋ በሚናገር ሰው ላይ፣ ከራስ መተማመን፣ ማስጠንቀቂያዎችን ከመናቅና አደጋን ከመናቅ የበለጠ ውድቀትን በእርግጥ የሚያመለክት ነገር የለም። ሁልጊዜ ካልተጠነቀቅንና ካልጸለይን በቀር፣ በማለዳ በጽኑ ተቃውመን ወደቆምንባቸው ኃጢአቶች በቀኑ ሂደት ውስጥ ልንሳብ እንችላለን። ምእመናን ለራሳቸው ቢተዉ፣ ይወድቃሉ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኃይልና በክርስቶስ ጸሎት ይጠበቃሉ።

ጌታችን አሁን ስለሚመጣው እጅግ ታላቅ የሁኔታ ለውጥ አስቀድሞ አስታወቀ። ደቀ መዛሙርቱ ወዳጆቻቸው በፊት እንደነበሩላቸው ደግ እንደሚሆኑላቸው መጠበቅ የለባቸውም ነበር።

ሙሉ ማብራሪያውን ያንብቡ ድምፅ፣ ሙሉ ማብራሪያ እና ከመስመር ውጭ ንባብ

ትርጉሞች8 · 6